ትግራይ፡ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በ167 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን አስታወቀ

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, PMO

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር)

በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በ167 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ይፋ አደረገ።

ይህ የተባለው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ትናንት በጋራ በሰጡት መግለጫ ነው።

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በመግለጫው ላይ በህውሓት ኃይሎች የተፈጸሙት ተግባራት በአገሪቱ የወንጀል ሕግ አንጻር በከፍተኛ ወንጀል የሚያስጠይቁ ናቸው ብለዋል።

በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸመው ጥቃት 'የመንግሥትን አገሪቱን የመከላከል ኃይል ለማዳከም' በተፈጸመ ወንጀል በሚል የሚያስጠይቅ መሆኑን ጠቁመዋል።

በባሕር ዳር እና ጎንደር ከተሞች ላይ የተፈጸሙትን የሮኬት ጥቃቶች በተመለከተም፤ ድርጊቱ በሽብር ወንጀል እንደሚያስጠይቅ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጌዲዮን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን መናድ፣ ታጥቆ አመጽ መቀስቀስ እና በአገር ክህደት ወንጀሎች የሚያስጠይቁ ወንጀሎች መፈጸማቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ በበርካታ ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ መውጣቱን አስታውሰዋል።

እስካሁን ድረስ በፌደራል ፖሊስ እና በፌደራል ዐቃቤ ሕግ የተለዩ 167 ተጠርጣሪዎች ላይ የእስር ማዘዣ መውጣቱን ተናግረዋል። ከእነዚህም መካከል በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጨምረው አመልክተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ከአገር ውጪ ያሉ ተጠርጣሪዎች ከሚገኙበት አገር ተላልፈው እንዲሰጡ መንግሥት መጠየቁን ጠቅሰው፤ ይህ አይነት አሰራር በባህሪው ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው ሲሉም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ገልጸዋል።

ከግለሰቦቹ በተጨማሪም ከህውሓት ጋር ግነኙነት አላቸው የተባሉ 38 ኩባንያዎች ንብረት እንዳይቀሳቀስ እግድ እንደተጣለባቸው አስታውሰዋል።

እነዚህ ኩባንያዎች በርካታ ሰዎችን ቀጥረው ያሚያስተዳድሩት መሆናቸው ከግንዛቤ በማስገባት የኩባንያዎቹን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለማስቀጠል የፌደራል ፍርድ ቤት እነዚህን ኩባንያዎች የሚያስተዳደር ባለአደራ አስተዳደር ይሰይማል ብለዋል።

የተጣለው እግድ ኩባንያዎቹ ንብረት እና ገንዘብ እንዳይስተላልፉ ወይም ለህወሓት ድጋፍ እንዳደርጉ የሚያደርግ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ተጠርጣሪዎች

ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ህወሓት በአዲስ አበባ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሽብር ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል ከነዋሪዎች ጥቆማ ደርሶናል ያሉ ሲሆን፤ ይህንን ተከትሎ በተደረጉ ምርመራዎች በአዲስ አበባ 343 ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን እና ከእነዚህም መካከል 160 የሚሆኑት በዋስ መለቀቃቸውን ተናግረዋል።

ፖሊስ የሚደርሱትን ጥቆማዎች ተከትሎ በሚያደረገው ፍታሻ ላይ ቅሬታዎች እየደረሷቸው እንደሆነ የጠቀሱት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ፤ "የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው የምንመለከተው፤ የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የፌደራል ፖሊስ ቅሬታ መቀበያ መንገዶችን እየዘረጉ ነው" ብለዋል።

አስተያየት መቀበያ የስልክ መስመሮች እና ዴስኮች ተዘጋጅተዋል። እነዚህም በተቋማቱ ይፋ እንደሚደረጉ ገልጸዋል። ይደረጋሉ" ብለዋል።

የመብት ጥሰቶች ምርመራ ይደረጋል

እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች እና ሌሎች አካላት በሰሜን ኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን ተከትሎ፤ መንግሥት መርማሪዎችን እና ዐቃቤ ሕጎች ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ማስማራቱን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ ጨምረው ተናግረዋል።

ይህ ምርመራ በከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚከናወን አረጋግጠው፤ ምርመራው ሲጠናቀቅ ውጤቱም ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

የፎቶው ባለመብት, PMO

የምስሉ መግለጫ, የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

መቀ ከ50-60 ኪ.ሜ ርቀት ተከባለች

በትናንቱ መግለጫ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው ትላልቅ ከተሞችን ጨምሮ አብዛኛው የትግራይ ክልል መሬት በአገር መከላከያ ሠራዊት ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አክሱም፣ አደዋ እና አዲግራት ከተሞች ደግሞ በቅርቡ ከህወሓት ነጻ የወጡ ከተሞች ናቸው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ የክልሉ መዲና የሆነችውን መቀለን ለመቆጣጠር መከላከያ ሠራዊት ከ50 እስከ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ተከባ እንደምትገኝ ተናግረዋል።

አምባሳደሩ ጨምረው እንደተናገሩት፤ የህወሓት ኃይሎች ለቀው ለመውጣት ሲገደዱ በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እያደረሱ እየሸሹ ነው ብለዋል።

እንደምሳሌም የአክሱም አየር ማረፊያ ላይ ጉዳት እንዲደርስ መደረጉን እንዲሁም ከስድስት ያላነሱ ድልድዮች እንዲፈርሱ መደረጋቸውን እና መንገዶች መቆፈራቸውን ተናግረዋል።

አምባሳደር ሬድዋን "የመቀለ ከተማ ነዋሪ እውነታውን ተረድተው፤ በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የህወሓት መሪዎችን አሳልፎ መስጠት ይኖርበታል" ብለዋል።

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሆኑት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ልዑክ እንደሚልኩ አስታውሰው፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን ልዑክ ተቀብለው የሚያነጋግሩት ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአፍሪካ መሪዎች ካለ አክብሮት የመነጨ መሆኑን አስታውሰው፤ "ከህወሓት ኃይሎች ጋር ግን እንደ ሕጋዊ አካል ቆጥሮ የሚደረግ ውይይት አይኖርም" ብለዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት አምርቶ ሦስተኛ ሳምንቱን ሊደፍን ተቃርቧል።

ባለፉት ሳምንታት በተካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻዎች የመንግሥት ኃይሎች የተለያዩ ከተሞችን መያዛቸው የተነገረ ሲሆን በክልሉ ዋና ከተማ መቀለ አቅራቢያ መድረሳቸውም ተገልጿል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ መቀለ የአገሪቱ ሠራዊት ከመንቀሳቀሱ በፊት ሊደርስ ይችላል የተባለ ጉዳትን ለማስቀረት የትግራይ ክልል ኃይሎችን የህወሓት አመራሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ነገ ረቡዕ የሚያበቃ የ72 ሰዓታት የጊዜ ገደብ አስቀምጠዋል።