ትግራይ ፡ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ተጠየቀ

የተፈናቀሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት ሁለት ሳምንት ያለፈውን በኢትዮጵያ መንግሥት ሠራዊትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ግጭት ለማስቆም የሚያስችል አስቸኳይና ጊዜያዊ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠየቁ።

ጄኔቫ ላይ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም ዩኤንኤችሲአር ቃል አቀባይ ባርባር ባሎች "በአስቸኳይ ተግባራዊ የሚደረግ ተኩስ አቁምና የሚያስፈልገው የሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስችል መተላለፊያ ለማዘጋጀት ነው" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።

ግጭቱ ባለበት አካባቢ በመድረስ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ማድረግ ያለመቻላቸውን የጠቀሱት ተቋማቱ ከተኩስ አቁሙ በተጨማሪ ለሰላማዊ ሰዎች የእርዳታ አቅርቦት ለመድረስ የሚያሰችል መተላላፊያ እንዲመቻችም ጠይቀዋል።

የእርዳታ ድርጅቶቹ እንደሚሉት አስቸኳይ የተኩስ ማቆም ከተደረገና የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር ከተከፈተ በግጭቱ ሳቢያ መውጫ አጥተው ለሚገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ድጋፍ ለማቅረብ እንደሚረዳቸው ገልጸዋል።

እስካሁን ቢያንስ 33 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች ከኢትዮጵያ የሱዳንን ድንበር ተሻግረው መግባታቸው የተነገረ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ እንደሚለው ግጭቱ የሚቀጥል ከሆነ በቀጣዮቹ ስድስት ወራት አስከ 200 ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች ወደ ሱዳን ሊገቡ ይችላሉ።

የመንግሥታቱ ድርጅት ወደ ግጭቶቹ አካባቢዎች የመድረስ ዕድል እንደሌላቸው ገልጸው፤ ነገር ግን አስካሁን ባለው ሁኔታ በቀውሱ ሳቢያ በመቶዎች ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀሩ ስጋት አላቸው።

ወደ ሱዳን እየገቡ የሚገኙት ስደተኞች በፍርሃት ውስጥ ያሉና የተራቡ ሲሆኑ ግማሽ የሚሆኑት ደግሞ ህጻናት እንደሆኑ ተነግሯል።

ቀደም ብሎ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ተሰደው የመጡ በርካታ ሰዎችን የሚረዳው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ እየጨመረ የመጣው የስደተኞች ቁጥር በሱዳን መረጋጋት ላይ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል የሚል ስጋት አለው።

የእርዳታ ድርጅቶች ወደ ሱዳን እየገቡ ላሉት አዲስ ስደተኞች የምግብና የመጠለያ ድጋፍ ለማድረግ የ50 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋቸው ጥሪ አቅርበዋል።

በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በትግራይ ኃይሎች መካከል እተካሄደ ያለው ግጭት ሦስተኛ ሳምንቱን የያዘ ሲሆን፤ ይህንን በመሸሽ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ወደ ሱዳን እየገቡ መሆናቸውን የእርዳታ ድርጅቶች እገለጹ ይገኛሉ።