ትግራይ፡''የለም የማያውቁ ህጻናት ይዘን እየተራብን ነው''-ኢትዮጵያውያን ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, EBRAHIM HAMID
በፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል መካከል የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በየቀኑ አራት ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ተፈናቅለው ወደ ሱዳን እየተሰደዱ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከሁለት ሳምንት በላይ ያስቆጠረው ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ህይወት ቀጥፏል፤ በአስር ሺዎችም የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ተፈናቅለዋል።
ኢትዮጵያን በትግራይ ክልል በኩል ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሲሆን እስካሁንም 36 ሺህ ደርሰዋል ተብሏል።
በድንጋጤ የተዋጡ፣ እራፊ ጨርቅ ላያቸው ላይ ጣል ያደረጉና በፍርሃት የተሞሉ ተፈናቃዮች ወደ ሱዳን ያቀኑ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ታዳጊዎች እንደሆኑም መረጃዎች ይጠቁማሉ።
ከአራት ልጆችዋ እና ከባለቤትዋ ጋር ከሁመራ አካባቢ ተፈናቅላ የተከዜን ወንዝ ተሻግራ ሀምዳይት በሚባል የሱዳን ግዛት የምትገኝ እናት መጥፎ በሚባል ሁኔታ ላይ እንዳለች ለቢቢሲ ገልጻለች፡፡
''ድብደባ ሲጀመር ልብሳችን እንኳን ሳንይዝ ከሁመራ ሀምዳይት ተብሎ ወደሚጠራ የሱዳን መሬት ተሻገርን። ድበደባው ሲበዛ ድልድይ ስር ተደበቅን፤ ባጠገባችን ነበር የሚይወድቀው'' ብላለች።
በተጨማሪ ''እዚህም ከደረስን በኋላ በጣም ተቸግረናል'' በማለት ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጻለች፡፡
ኢትዮጵያዊትዋ ስደተኛ ሱዳናውያን የቻሉትን ያህል ለማገዝ ጥረት ቢያደርጉም ከስደተኛው መብዛት የተነሳ ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ነው የምትናገረው፡፡
"ሱዳኖች በመልካም ሁኔታ ተቀብለው እያስተናግዱን ነው። ዱቄትና ምስር ሰጥተውናል፤ ሰው ስለበዛ ግን ከአቅማቸው በላይ ሆኗል፡፡ እነሱ ተመዝግባችሁ ወደ ሱዳን ውስጥ ግቡ ነው የሚሉን፡፡ እኛ ግን ሽማግሌዎች ትተን ሸሽተን ስለመጣን እዚህ ሀምዳይት ነው ያለነው'' ብላለች፡፡
አሁን ባረፉበት አካባቢም በአማካኝ እስከ አስር ሺህ የሚደርሱ ስደተኞች እንዳሉ ነው የምትናገረው፡፡
ከሁመራ ተነስተው ሀምዳይት የሚባለው የሱዳን ግዛት እስኪደርሱ ብዙ ችግሮች እንዳጋጠሙዋቸው የምትናገረው ስደተኛዋ እናት ''መንገድ ላይ ያለ ሀኪም መንታ ልጆች የወለዱ አሉ፤ አራስ ልጆች ሳያስጠምቁ አብረውን የመጡም አሉ'' በማለት ለቢቢሲ ገልጻለች።
በተጨማሪም ህመምተኛ ህፃናት እና ሽማግሌዎች አብረዋቸው እንዳሉና ከገቡበት ችግር እንዲወጡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ተማጽናለች፡፡
ከአምስት የቤተሰብዋ አባላት ከሁመራ ወደ ሀምዳይት የገባች ሌላ እናትም ''በረሃ ውስጥ አስር ቀን ሆኖናል፤ ከቤታችን ምንም ነገር ሳንይዝ ወጥተን ዛፍ ስር ነው ተበታትነን ያለነው'' ብላለች፡፡
ከህጻናት ልጆቻቸው ጋር በረሃብ እየተሰቃዩ እንዳሉ የምትናገረው ኢትዮጵያዊትዋ ተፈናቃይ ''የለም የማያውቁ ህጻናት ይዘን እየተራብን ነው'' ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች፡፡
ከትግራይ ወደ ሱዳን ያለማቋረጥ ስደተኛ እየተጓዘ እንዳለ የሚገልጽ ሌላ ወጣት በተመሳሳይ ሰው ባዶ እጁ እንደሚመጣ እና እዚያ ከደረሰም የሚሰጠው እርዳታ በቂ አለመሆኑን በመግለጽ ''በተለይ ህጻናት እየተራቡብን ነው'' ብሏል፡፡
የተባበሩት መንግሥት በበኩሉ ግጭቱ እያስከተለውን ሁኔታም በማየት አገሪቷ "ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ይገጥማታል" በማለት እያስጠነቀቀ ይገኛል።
"ከፍተኛ የሆነ በትግራይም ክልል ትልቅ የውስጥ መፈናቀል አለ፤ ይህ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል። በተቻለም መጠን ለዚህ ቀውስ ለመዘጋጀት እየሞከርን ነው" በማለት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቃለ አቀባይ የንስ ላርክ ተናግረዋል።
በትግራይ ውስጥ ያለው መፈናቀል ወደ ሱዳን ከሚሰደዱት በብዙ እጥፍ ሊሆን በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችልም ተመድ አስጠንቅቋል። ከትግራይ ክልል እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን ለመድረስ እንዲችል ያለገደብ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል።
ወደ ትግራይ የሚወስዱ መንገዶች በመዘጋታቸው ምክንያት እርዳታ የሚጠብቅ ስደተኛ እና ሕዝብ ችግር ውስጥ እንዳሉም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በኩል ከትግራይ ክልል ጋር የምትዋሰነው ሱዳን በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች እየተቀበለች እንደሆነ በሱዳን የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጀት በበኩሉ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ታሳቢ ተደርገው የተሰሩ መጠለያዎች በሺዎች በሚቆጠሩ ስደተኞች መጣበባቸው ገልጿል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጦርነቱ ውስንና በተወሰኑ የህወሓት አባላት ላይ ያነጣጠረና ሕገ መንግሥትን ለማስከበር እየተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ መግለፃቸው ይታወሳል።
የትግራይ ክልል በበኩሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጦርነት እንደተከፈተበትና ሕዝቡም ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል።












