ትግራይ ፡ እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን ለመድረስ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ተመድ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ክንፍ የሆነው ዩኤንኤችሲአር፤ ከትግራይ ክልል እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን ለመድረስ እንዲችል ያለገደብ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠየቀ።
የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አን ኤንኮንቴ እንደተናገሩት፤ የድርጅቱ እንቅስቃሴ ሳይገታ ስደተኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መርዳት የሚችልበት መንገድ መመቻቸት እንዳለበት አመልክተዋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ በፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ የሚገኘውን ግጭት ሸሽተው እየተሰደዱ ካሉት ሰዎች መካከል ግማሹ ሕፃናት እንደሆኑና አብዛኞቹ ያለ ወላጆቻቸው ወይም ሌላ ጠባቂ እንደሚሰደዱ ተናግረዋል።
ከግጭቱ ጋር በተያያዘ ወደ ጎረቤት አገራት የሚሰደዱ ዜጎችን ለመቀበልና ወደ ቀያቸው በመመለስ ለማቋቋም የኢትዮጵያ መንግሥት ዝግጁ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከቀናት በፊት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ መንግሥት የተሰደዱ ንጹሃን ዜጎችን ንብረታቸውን ለመጠበቅ፣ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰብዓዊ ድጋፍ ለማቅረብ እና ሲመለሱም ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
አን ኤንኮንቴ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት፤ ድርጅቱ ውሃ፣ የንጽህና መጠበቂያ እንዲሁም ሌሎችም መሠረታዊ ቁሳቁሶችን ለማቅረብ የተቻለውን እየጣረ ቢሆንም፤ በተለይም አራት የስደተኞች መጠለያ ካምፖች በሚገኝበት የሰሜን ምሥራቅ አካባቢ የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ አይደለም ብለዋል።
በእነዚህ አራት የስደተኛ መጠለያ ካምፖች 100 ሺህ ኤርትራውያን ስደተኞች ይኖራሉ።
"ወደ እነዚህ ቦታዎች ደርሶ አገልግሎት ለመስጠት ለሁሉም ሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች በጣም ከባድ ነው። ከስደተኞቹ ግማሾቹ ሕፃናት ናቸው። አብሯቸው የቤተሰብ አባል የለም" ሲሉ አን አስረድተዋል።
በአካባቢው ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ጠቁመው፤ የመገናኛ አገልግሎት መቋረጡ ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙ እንዳገዳቸውም አስረድተዋል።
"አገልግሎት እንድንሰጥ አካባቢው ክፍት መሆን አለበት። ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እርዳታ መስጠት መቻል አለብን። አካባቢው ለሰብዓዊ እርዳታ ክፍት እንዲሆን ብንጠይቅም እስካሁን ምንም ምላሽ አላገኘንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሕዝቡ መካከል 600 ሺህ የሚሆኑት ኑሯቸው በሰብዓዊ እርዳታ ላይ የተመረኮዘ መሆኑን በማስታወስ፤ የድርጅቱ ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ጠይቀዋል።
"የእርዳታ ቁሳቁስ ለማስገባት አካባቢው ክፍት ሊሆን ይገባል። ገበያው ላይ ውስን ምግብ ነው ያለው። ባንክ ለሳምንታት ተዘግቶ ስለነበረ ገንዘብ የለም" ብለዋል።
ድርጅቱ ሰብዓዊ ቀውሱ እንዳሰጋውና በአካባቢው እንዲህ ያለ ሁኔታ ባለፉት ሁለት አስርታት እንዳልገጠመው የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተወካይ አን ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዩኤንኤችሲአር ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ እየተከሰተ መሆኑና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሰደዳቸውም እንዳሳሰበው አስታውቋል።
የድርጅቱ ቃል አቀባይ ባህር ባሎክ፤ "ወደ አካባቢው መግባት ሲቻልና የጸጥታ ሁኔታው አስተማማኝ ሲሆን ትግራይ ውስጥ ድጋፍ ለመስጠት በተጠንቀቅ እየተጠባበቅን ነው" ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት፤ በግጭቱ ሳቢያ ከትግራይ ከተሰደዱት ሰዎች ቁጥር በላይ እዚያው በክልሉ ሳሉ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ሊበልጥ እንደሚችል ይሰጋል።
የድርጅቱ የሰብዓዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ክፍል ቃል አቀባይ የንስ ላርኪ፤ "ትግራይ ውስጥ ብዙ ሰዎች ተፈናቅለው ሊሆን ይችላል። ይህም አሳሳቢ ነው። በቻልነው መጠን ለመርዳት እየተዘጋጀን ነው" ሲሉ አስረድተዋል።
አሁን ላይ ማንኛውም የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ድርጅት ወደ ትግራይ ለመግባት ፍቃድ እንዳልተሰጠው ይነገራል።
ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲካረር የመጣው የትግራይ ክልል እና የፌደራል መንግሥት ውጥረት ወደ ጦርነት ከተሻገረ 15ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፤ ግጭቱን ሸሽተው ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከ30 ሺህ ማለፉ ተገልጿል።
በሱዳን ተጠልለው ከሚገኙ ስደተኞች አንዷ፤ "ለብዙ ዓመታት ሰርተን ያፈራነውን ነው ትተን ወጣነው። ምንም የያዝነው ነገር የለንም። በጀርባችን መያዝ የቻልነው ልብሳችንን ብቻ ነው። ባለቤቴ የት እንደሚገኝ አላውቅም። ለአምስት ቀናት ስፈልገው ነበር። ላገኘው አልቻልኩም" ስትል የሚገኙበትን ሁኔታ ገልጻለች።
ሌላዋ ስደተኛ ደግሞ፤ "ከፍተኛ ግጭት ነበር። ብዙ ሰው ሞቷል። ከዚያ እንድንሄድ ሲነግሩን ወጣን። ሁላችንም ወጣን" ብላለች።
በካርቱም የዩኤንኤችሲአር ድንገተኛ ምላሽ አስተባባሪ የንስ ሄዝማን ግጭቱ ያስከተለው ሰብዓዊ ቀውስ መባባሱን ገልጸው ሁኔታው "አስጊ ነው" ሲሉ ተናግረዋል።















