ትግራይ፡ ኬንያ የኢትዮጵያ መንግሥት ለተፈጠረው ችግር ሰላማዊ መፍትሄን እንዲሻ ጠየቀች

የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

የፎቶው ባለመብት, WPA Pool

በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጉብኝት እያደረጉ ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ የገቡት ትናንት ነበር።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከአቶ ደመቀ ጋር በነበራቸው ውይይት በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር በሰላም የሚፈታበት መላ እንዲበጅ ሐሳብ ማንሳታቸውን የፕሬዝዳንቱ ጽሕፈት ቤት ገልጧል።

ኡሁሩ ህወሓት ሁኔታዎችን እንዲያረግብም ጥሪ ማቅረባቸውም ተነግሯል፡፡ "ይህ ጦርነት ኢትዮጵያ በአካባቢው የነበራት የኢኮኖሚ እምርታ የሚሸረሽር ነው" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

አቶ ደመቀ መኮንን ሰኞ ኬንያ ከመግባታቸው ቀደም ብሎ ከዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ጋር በተለያዩ አገራዊና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ስለመወያየታቸውን ዘገባዎች መውጣታቸው ይታወሳል።

የ X ይዘትን ይለፉት
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?

ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።

ማሳሰቢያ፡ የሦስተኛ ወገን ይዘቶች ማስታወቂያ ሊኖራቸው ይችላል

የ X ይዘት መጨረሻ

ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ በህወሓትና በመንግሥት መካከል ድርድር ለማድረግ እየሞከሩ ነው የሚሉ ዜናዎች መውጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ዘገባ ሐሰት ነው ሲል ማስተባበሉ አይዘነጋም።

ሙሴቬኒ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ያደረጉት ውይይት "ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ካለው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ" ጋር የተገናኘ እንደሆነ በገጻቸው አስፍረው ነበር።

ሙሴቬኒ አክለውም "እኔ ብሔር ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን አልደግፍም። ትኩረት መስጠት ያለብን ለአንድነትና ለተመሳሳይ ፍላጎት ነው። ይህ ብቸኛው የምንበለጽግበት መንገድ ነው" ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ማስታወሻ አስፍረዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የናይጄሪያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኦባሳንጆ በመንግሥትና በህወሓት መካከል ድርድር ለማስጀመር ወደ አዲስ አበባ እያቀኑ ነው ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የዘገበው ትናንት ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት በኦባሳንጆ ወደ አዲስ አበባ ማቅናት ጉዳይ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።

ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት ለችግሩ ሠላማዊ መፍትሄ እንዲሻ ዓለም አቀፍ ጥያቄዎች እየበረከቱ መምጣታቸውን ከቅርብ ቀናት ወዲህ የሚወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ።

በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረውን ችግር በመቀረፍ ሠላም እንዲወርድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ላደረጉት ጥረት ባለፈው ዓመት ሽልማልት ያበረከተላቸው የኖቤል ኮሚቴ በትግራይ ውስጥ የተከሰተው ግጭት እንዳሳሰበውና ሠላም እንዲወርድ ጠየቁን ሮይተርስ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት እስካሁን የሚቀርቡለትን የድርድር ጥያቄዎች ውድቅ እያደረገ ያለው "ሕግ የማስከበር ውስጣዊ የመንግሥት ተግባር ላይ ነኝ" በሚል ነው።

ይህ በእንዲህ እያለ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ለጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኡመር ጊሌ ማድረሳቸውን የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

መንግሥት ሕግን የማስከበር ዘመቻ ባለው በዚህ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ ሂደት ዙርያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕወሓት ኃይሎች እጃቸውን እንዲሰጡ መንግሥት ያስቀመጠው የሦስት ቀናት የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ዛሬ ማለዳ በፌስቡክ ገጻቸው አስፍረዋል።

ፌደራል መንግሥቱ ትግራይ ውሰጥ ባለው ሠራዊቱ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መሰንዘሩን ገልጾ ወታደራዊ ዘመቻ ማካሄድ ከጀመረ እነሆ ሁለት ሳምንት ሊሞላው ነው።