ፔሩ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ሶስት ፕሬዚዳንቶችን አየች

ፍራንቺስኮ ሳጋስቲ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የፔሩ ምክር ቤት አዲስ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት መርጧል- ይህም ከሳምንት ባነሰ ወቅት የመጡ ሶስተኛ ፕሬዚዳንት ናቸው።

የ76 አመት ዕድሜ ባለፀጋው የምክር ቤት አባል ፍራንቺስኮ ሳጋስቲ አገሪቷ ልታደርገው ካቀደችው የመጪው አመት ምርጫም ድረስ ይመራሉ ተብሏል።

ግለሰቡ መሃንዲስና ምሁር ናቸው።

ባለፈው ሳምንት የአገሪቷ ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራ በሙስና ወንጀል ተዘፍቀዋል በሚል ከስልጣናቸው ተነስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ ወንጀሉን አልፈፀምኩም ብለው ቢክዱም በመላው አገሪቷ ተቃውሞ እንዲቀጣጠል ሆኗል።

በዚህም ተቃውሞ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ በርካቶች ተጎድተዋል።

አዲሱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ፍራንቺስኮ ሳጋስቲ የተመረጡት ከሚያስፈልጋቸው ውስጥ ትንሹን 60 ድምፅ ማግኘታቸውን ተከትሎ ነው።

ፓርቲያቸው ባለፈው ሳምንት ከስልጣናቸው የተነሱትን ፕሬዚዳንት በመቃወም ድምፅ የሰጠው ብቸኛው ፓርቲ አባል ናቸው።

"በአሁኑ ወቅት ለፔሩ ዋነኛው ነገር መረጋጋት እንዲፈጠርና ይህ ቀውስም እንዲቆም ነው" በማለት የፓርላማ አባሉ አልበርቶ ደ ቤላውንዴ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ድምፅ ከመሰጠቱ በፊት ተናግረዋል።

ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ፍራንቺስኮ ሳጋስቲ ከመሾማቸው በፊት ፔሩ የፓርላማውን የቀድሞ አፈ ጉባኤ ማኑኤል ሜሪኖን በፕሬዚዳንትነት መርጣ ነበር።

በሙስና ተዘፍቀዋል የተባሉትን ፕሬዚዳንት ማርቲን ቪዝካራን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ አገሪቷን እንዲመሩ ቢመረጡም በስልጣን የቆዩት ከሳምንት ያነሰ ጊዜ ነው።

ለዚህም ምክንያቱ ግለሰቡ ቀውሱን ለማረጋጋት ኃላፊነታቸውን አልተወጡም በሚል የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ ፖለቲከኞች ከስልጣን እንዲወርድ በመጠየቃቸው ነው።

በርካታ ወጣቶችን ያካተተ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንት ቪዝካራ ከስልጣን እንዲወርዱ ተከታታይ ሰልፎችን አድርገዋል።

በተለይም ቅዳሜ እለት በሊማ የነበረው የተቃውሞ ሰልፍ ሰላማዊ ቢሆንም ከአመሻሹ በፖሊስና በተቃዋሚዎች መካከል ግጭት ተፈጥሯል ተብሏል።

ፖሊስ አስለቃሸ ጋዝ በመርጨትም ሰልፈኞቹን ለመበተን ሞክሯል። በዚህም ግጭት ሁለት ተቃዋሚዎች ተገድለዋል።

ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን መወገዳቸውን ተከትሎ የመጡት ፕሬዚዳንትም ቀውሱን ከማረጋጋትና ከፖሊስ ጭካኔ ጋር በተያያዘ በተነሳባቸው ተቃውሞ እሁድ እለት ከስልጣን ተነስተዋል።

በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት የምጣኔ ኃብቷ የተዳከመው ፔሩ የማትወጣበት የፖለቲካዊ ቀውስ እንዳትገባ ፍራቻ አለ።