ትራምፕ ወታደሮቻቸውን ከአፍጋኒስታንና ከኢራቅ ሊያስወጡ ነው

የአሜሪካ ወታደሮች በኢራቅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ወታደሮችን ከኢራቅና ከአፍጋኒስታን ያስወጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የአሜሪካ ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው።

በአፍጋኒስታን ከሚገኙት 5ሺህ ወታደሮች ቢያንስ ግማሹ ተመላሽ እንደሚደረጉ ባለሥልጣናት ጠቁመዋል።

በኢራቅ ደግሞ ከ3ሺህ ወታደሮች ውስጥ ቢያንስ 500 ያህሉ ተቀናሽ ተደርገው ይመለሳሉ። 2ሺ 500ዎቹ እዚያው ይቆያሉ።

ትራምፕ በተደጋጋሚ ሁሉም ወታደሮች ከገና በፊት ለአገራቸው ይበቃሉ ሲሉ ተደምጠዋል። ሆኖም ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም።

ከአራት ዓመታት በፊት በምርጫ ቅስቀሳ ወቅትም ውጭ አገር የሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮችን 'ለእናት አገራቸው አበቃቸዋለሁ' ሲሉ ቃል ገብተው ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ አሁን በጆ ባይደን በማያሻማ ሁኔታ ቢሸነፉም ሽንፈታቸውን ተቀብለው ለአሸናፊው ፕሬዝዳንት እጩ እንኳን ደስ ያለህ ለማለት በተቸገሩበት ወቅት ነው ወታደሮችን እንደሚያስወጡ የገለጹት።

አሁን ከኢራቅና አፍጋኒስታን ይለቃሉ የተባሉት አሜሪካዊ ወታደሮች በ'ጃንዋሪ' 15 ተጠቃለው አገራቸው ይገባሉ ተብሏል።

ይህም ማለት ወታደሮቹ የሚመለሱት ከጆ ባይደን ወደ ዋይት ሐውስ መግቢያ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ነው።

ይህ የትራምፕ እርምጃ ባልተለመደ መልኩ ከሪፐብሊካን ሴናተር ሚች መከኔል ተቃውሞ ገጥሞታል። ምክንያቱ ደግሞ እርምጃው በአፍጋኒስታንና በኢራቅ የሚገኙ አማጺዎችንና አክራሪ ኃይሎችን የሚያበረታታ ነው በሚል ነው።

ትራምፕ በበኩላቸው የአሜሪካዊያን ወታደሮች በውጭ አገር መቀመጥ አገራቸውን ለከፍተኛ ወጪ የሚዳርግ ነው ይላሉ።

ባለፈው መስከረም ፔንታገን በኢራቅ ከሚገኙ ወታደሮቹ አንድ ሦስተኛውን እንደሚያስወጣ ይፋ አድርጎ ነበር።

ይህም በሳምንታት ውስጥ እንደሚፈጸም ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል።

እዚያ የሚገኙት የተወሰኑ መታደሮች የኢራቅን መከላከያ በማሰልጠን ደረጃ እንደሚወሰኑም ተገልጾ ነበር።

የአሜሪካ ወታደሮች ኢራቅ ከተወረረችበት ከ2003 ጀምሮ በኢራቅ ይገኛሉ። ከ2001 ጀምሮ ደግሞ በአፍጋኒስታን ቆይተዋል።