ትግራይ ፡ የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ስለኢትዮጵያ 'ውይይት' የፃፉትን መልዕክት አነሱ

የፎቶው ባለመብት, @KagutaMuseveni
የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ኢትዮጵያ ውስጥ የተቀሰቀሰውን ግጭት ለማርገብ ሁለቱንም አካላት የሚያወይይ መኖር አለበት ብለው የፃፉትን አነሱ።
ሙሴቬኒ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት ይህ የማይሆን ከሆነ "አላስፈላጊ የነብስ ጥፋት ያስከትላል፤ የአገሪቱንም ምጣኔ ሃብት ይጎዳል" ብለው ነበር።
ሙሴቬኒ ይህንን መልዕክት በትዊተር ገፃቸው ያሰፈሩት ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ኡጋንዳ ውስጥ ከተገናኙ በኋላ ነው።
ነገር ግን ትዊተር ገፃቸው ላይ ካሰፈሩት ተከታታይ መልዕክት [ትሬድ] መካከል ስለ ውይይት የፃፉትን ቆየት ብለው አጥፍተውታል።
ሙሴቬኒ ይህንን ሃሳብ ለምን እንዳጠፉት ይፋ ባይሆንም የኢትዮጵያ መንግሥት ከህወሓት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ዓይነት ውይይት እንደማይቀበል በተደጋጋሚ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይ ክልል ውስጥ "ሕግ የማስከበር ዘመቻ ላይ ነኝ" ማለቱ አይዘነጋም።
በጦርነቱ ሳቢያ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሱዳን እየተሰደዱ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደሞቱ ተነግሯል።
ትግራይ ክልል ውስጥ የበይነ መረብና የስልክ አገልግሎት በመቋረጡ ምክንያት ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ከባድ ሆኗል።
ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ በሁለቱ ኃይሎች መካከል ድርድር ለማድረግ እየሞከሩ ነው የሚሉ ዜናዎች መውጣታቸውን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ዘገባ ሐሰት ነው ሲል አስተባብሏል።
ሙሴቬኒ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ ጋር ያደረጉት ውይይት "ኢትዮጵያ ውስጥ እየተስተዋለ ካለው የሰላምና የፀጥታ ጉዳይ" ጋር የተገናኘ እንደሆነ ጽፈዋል።
ሙሴቬኒ አክለውም "እኔ ብሔር ላይ የተመሠረተ ፌዴራሊዝምን አልደግፍም። ትኩረት መስጠት ያለብን ለአንድነትና ለተመሳሳይ ፍላጎት ነው። ይህ ብቸኛው የምንበለጽግበት መንገድ ነው" ብለዋል።
በሌላ በኩል የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝደንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሓት መካከል ድርድር ለማስጀመር ወደ ኢትዮጵያ ሄደዋል ሲል ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል ዘግቧል።
ድርድርን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋም አሁንም ባይቀየርም ኦባሳንጆ አዲስ አበባ ገብተዋል ይላል ኤኤፍፒ።
"ድርድር ለማድረግ መሞከር ተጠያቂ ያለመሆንና ሕገ ወጥነትን የሚያበረታታ ነው" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታና የአስቸኳይ ጊዜ ቃል አቀባይ ሬድዋን ሁሴን ተናግረዋል።
"የትኛውም አገር ሮኬትና ሚሳዔል አለኝ ከሚልና ጥቃት ለመሰንዘር ከሚዝት ኃይል ጋር ቁጭ ብሎ አይወያይም" ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታው።
ኦባሳንጆ ወደ አዲስ አበባ እያቀኑ መሆኑን ለፈረንሳዩ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ ያሳወቁት ቃል አቀባያቸው ኬሂንዴ አኪንዬሚ ናቸው።
"ወደዚያ ያቀኑት ለድርድር ነው" ከማለት ውጪ ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሠሜናዊውን የአገሪቱን ክልል የሚመራው ህወሓት ጋር ከውዝግብ አልፎ ወደ ጦርነት ከገባ ሁለት ሳምንታት ሊሆነው የተቃረበ ሲሆን፤ ከተለያዩ ወገኖች የድርድር ሐሳብ ቢቀርብም መንግሥት የሚወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ሕግ የማስከበር ሂደት ስለሆነ ከቡድኑ ጋር ውይይት እንደማይኖር በተደጋጋሚ ማሳወቁ ይታወቃል።















