ቤንሻንጉል ጉሙዝ፡ በአውቶብስ ላይ በተፈጸመ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች ተገደሉ

ቤኒሻንጉል ጉሙዝ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ ሰዎችን ይዞ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ።

ኮሚሽኑ እሁድ ዕለት ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳስታወቀው በክልሉ ቅዳሜ በደባጤ ወረዳ ከወንበራ ወደ ቻግኒ በመጓዝ ላይ በነበረ አውቶብስ ላይ "ዘግናኝ" ያለው ጥቃት ተፈጽሞ ቢያንስ 34 ሰዎች መገደላቸውን ገልጾ የሰለባዎቹ ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል።

በመግለጫው በተፈጸመው ጥቃት የተሰማውን ሐዘን የገለጹት ኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ "ይህ ጥቃት ሁላችንም በጋራ የተሸከምነውን የሰው ሕይወት ክፍያ ዛሬም በአሳዛኝ ሁኔታ የሚያሻቅብ ነው። የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት ጥቃቱ የበለጠ እንዳይባባስ እርምጃ መውሰዳቸው አበረታች ነው" ብለዋል።

ከዚህ ጥቃት ቀደም ብሎም በክልሉ መተከል ዞን ድባጤ ወረዳ "ያምፕ ቀበሌ" የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ አንድ ነዋሪ ሲገደል ሁለት የክልሉ የፖሊስ አባላት እንዲሁም የወረዳው አስተዳዳሪ መቁሰላቸውን የክልሉ ኮሙኑኬሸን ኃላፊ አቶ መለሰ ቅዳሜ ዕለት ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

"አካባቢው ከዚህ ቀደም የተረጋጋ ነበር" የሚሉት ኃላፊው፣ በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ታጣቂዎች ገብተው ጥቃት ማድረሳቸውንና በነዋሪው ላይ ስጋት መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

የክልሉ ፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት ከመከላከያ ኃይል ጋር ተባብረው በአካባቢው የተፈጠረውን ለማረጋጋት በሚሞክሩበት ወቅት ነበር ታጣቂዎቹ ከወንበራ ተሳፋሪዎችን ጭኖ ቡለንና ዲባጤን በማቋረጥ ወደ ግልገል በለስ የሚሄድ አውቶብስ ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ብለዋል።

ታጣቂዎቹ በርካታ ሰዎችን አሳፍሮ በመጓዝ ላይ የነበረን አውቶብስ አስቁመው በፈጸሙት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና የተረፉም እንዳሉ ኃላፊው ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የመከላከያ ሠራዊት በታጣቂዎቹ ላይ ተከታታይ እርምጃ መውሰዱን የገለጹት አቶ መለሰ በጥቃቱ የደረሰውን አጠቃላይ ጉዳትና በታጣቂዎቹ ላይ ስለተወሰደው እርምጃ ውጤት ሙሉ ማጣራት ከተደረገ በኋላ እንደሚገለጽ ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱልአዚም መሐመድ ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዕሁድ ዕለት እንደገለጹት፤ የመከላከያ ሠራዊት፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በወሰዱት እርምጃ ጥቃቱን ፈጽመዋል የተባሉ 16 ታጣቂዎች "ተደምስሰዋል" ብለዋል።

በተጨማሪም ከጥቃት ፈጻሚዎቹ መካከል ሁለቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና የቀረቱም ላይ እርምጃ ለመውሰድ ክትትል እየተደረገ መሆኑን ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።

ኢሰመኮ ጥቃቱን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በሲቪል ሰዎች ላይ የሚደርሰው ጥቃት መቀጠሉን አመልክቶ በፌዴራልና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ተመሳሳይ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል "የተሻለ ቅንጅት" እንደሚያስፈልግ ገልጿል።

ኮሚሽነሩ ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ጨምረውም "የፌዴራልና የክልሉ የፀጥታና የፍትሕ አካላት ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመሆን እነዚህን ጥቃቶች ሊያስቆም የሚችል አዲስ ክልላዊ የፀጥታ ስትራቴጂ ሊነድፉ ይገባል" በማለትም አሳስበዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተለያዩ ስፍራዎች ከባለፈው ዓመት ማብቂያ ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት በታጣቂዎች በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ላይ ግድያና ጥቃት ሲፈጸም መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፤ ይንንም ተከትሎ የየክልሉና የፌደራል መንግሥቱ የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ጥቃት ፈጻሚዎችን እንደገደሉና እንደያዙ ሲናገሩ ቆይተዋል።

በክልሉ ባለስልጣንት "ጸረ-ሠላም" ኃይሎች ተብለው በሚጠሩትና ማንነታቸው በውል ባልተለየው ታጣቂዎች በሚፈጸመው ጥቃት በነዋሪዎች ዘንድ ስጋት ያለ ሲሆን በዚህም ሳቢያ ከወራት በፊት ጀምሮ አንዳንድ የክልሉ ወረዳዎች በጸጥታ አካላት በሚመራ ኮማንድ ፖስት ሰር እንዲተዳደሩ መወሰኑ ይታወሳል።