በአሜሪካ የጥላቻ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተጠቆመ

በኤልፓሶ የደረሰው ጥቃት

የፎቶው ባለመብት, EPA

በአሜሪካ የጥላቻ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውንና በባለፉት አስር አመታትም ታይቶ በማያውቅ ደረጃ መድረሱን አንድ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።

ሪፖርቱን ያወጣው የአሜሪካው የፌደራል ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ነው።

በጥላቻ የተነሳሱ ግድያዎችም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የሚያሳየው ይህ ሪፖርት በባለፈው አመት 51 ሞቶች እንደተመዘገቡና ይህ ቁጥርም ከሁለት አመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር በእጥፍ ማደጉን ነው።

በባለፈው አመት ነሐሴ በቴክሳስ ኤልፓሶ በሚገኘው የዋልማርት መገበያያ መደብር ውስጥ የሜክሲኮ ዜጎች ላይ ባነጣጠረ ጥቃት 22 ሰዎች ተገድለዋል።

ከጎሮጎሳውያኑ 2014 ጀምሮም የጥላቻ ወንጀሎች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውንም መረጃዎች ያሳያሉ።

በርካታ ተሟጋቾችም አገሪቷ ውስጥ የሰፈነው የዘረኝነትና ሌሎች ጥላቻዎች እንደሚጨምሩም እያስጠነቀቁ ነው።

የኤፍቢአይ አመታዊ የጥላቻ ወንጀሎች ሪፖርት እንደሚያሳየው በባለፈው አመት 7 ሺህ 314 ወንጀሎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ ከሁለት አመት በፊት 7 ሺህ 120 ነበር።

ከፍተኛ የተባለው ቁጥር የተመዘገበው በጎሮጎሳውያኑ 2008 ሲሆን ቁጥሩም 7 ሺህ 783 ነው።

ሪፖርቱ የጥላቻ ወንጀል ብሎ የተረጎመው ወንጀሎች በዘር፣ በብሄር፣ በሃይማኖት፣ በፆታዊ አተያይ፣ በአካል ጉዳተኝነት፣ በፆታዊ ማንነትና ሌሎችም ጉዳዮች ተነሳስቶ ሲፈፀም ነው።

መረጃው እንደሚያሳየው ከሃይማኖት ጋር በተያያዘ ወንጀሎች 7 በመቶ የጨመሩ ሲሆን በተለይም በይሁዲ እምነት ተከታዮችና ተቋማት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነም ተገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ፀረ- ላቲን ወንጀሎችም እንዲሁም በአስር አመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን መረጃው ጠቁሟል።

በኤልፓሶ የተከሰተውና የ22 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት በጥላቻ የተነሳሳ ጥቃትም ተካቶበታል።

ሆኖም ከየትኛውም ቡድን ቢሆን የጥላቻ ወንጀል በትር በከፍተኛ ሁኔታ የሚያርፍባቸው ጥቁር አሜሪካውያን ናቸው።

ምንም እንኳን በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ያነጣጠረው የጥላቻ ወንጀል በትንሽም ቢሆን እንደቀነሰ የኤፍቢአይ ሪፖርት ቢያሳይም ከፍተኛ ቁጥሩን የሚይዙት እነሱ ናቸው።

በኤፍቢአይ ውስጥ በዘር ወይም በብሄር ጥላቻ ምክንያት ከተመዘገቡት 4 ሺህ930 ጥቃት የደረሰባቸው መካከል 48.5 በመቶ በፀረ- ጥቁር ወይም አፍሪካ አሜሪካውያንን ጥላቻ ጋር የተያያዘ ነው።

የኤፍቢአይ ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ በርካታ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መረጃዎች በተጠናቀረ መልኩ እንዲሰባሰቡና የተሻለ ሪፖርት የሚደረግበት ዘዴ እንዲቀየስ ጥሪ አቅርበዋል።

አንዳንድ የኤፍቢአይ ሪፖርት ሙሉ የጥላቻ ወንጀሉን መረጃ አያሳይም ብለዋል።