ቢሊየነሩ ማርክ ዙከርበርግ በኤሎን መስክ ተበለጠ

ኤሎን መስክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከአማዞኑ ጄፍ ቤዞስ እና ከማይክሮሶፍቱ ቢል ጌትስ ቀጥሎ በ3ኛ ደረጃ የሚገኘው ኤሎን መስክ ሆኗል። ይህ ደረጃ የፌስቡክ ፈጣሪው ማርክ ዘከርበርግ የተያዘ ነበር።

ዘከርበርግ በኤሎን መስክ የተበለጠው ከሰሞኑ ነው፣ በድንገት።

መስክ የግል ሀብቱ ከሰሞኑ በከፍተኛ ሁኔታ ተመንድጓል። በድንገቴ ያገኘው ጭማሪ ሀብት ብቻ 15 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል። ለዚህም ነው 3ኛውን ደረጃውን ያለተቀናቃኝ ሊቆናጠጥ የቻለው።

ለዚህ ድንገተኛ የሀብት ጭማሪ ምክንያት የሆነው ክስተት ከስቶክ ገበያ ጋር የተያያዘ ነው።

ባለፈው ሰኞ ዕለት የኤሌክትሪክ መኪና አምራች ኩባንያው ቴስላ በአሜሪካ ዋናው የስቶክ ማርኬት ውስጥ መግባቱና ሽያጩ 12 በመቶኛ እድገት በማሳያቱ የተነሳ ነው።

የኤለን መስክ "ስፔስ ኤክስ" የተሰኘው ሌላኛው ኩባንያው 4 የስነ ፈለክ ተመራማሪዎችን ወደ ጠፈር ማሳፈሩን ተከትሎ የተሰማ ዜና ነው።

ኤሎን መስክ በቅርቡ የኮቪድ 19 ተህዋሲ ተገኝቶበት ትልቅ ዜና ሆኖ ነበር። አሁን በማገገም ላይ ይገኛል።

ኤሎን መስክ በቴክኖሎጂና ፈጠራ የሚታወቅ ሲሆን የኤሌክትሪክ መኪና አምራቹን ቴስላን እንዲሁም ወደ ጠፈር የሚያመላልሰውን የሮኬት ታክሲ "ስፔስ ኤክስ"ን የመሠረተ ሰው ነው።

በቴስላ ኩባንያ አሁን የኤሎን መስክ ድርሻ 20 ከመቶ ብቻ ቢሆንም ይህ መኪና አምራች ኩባንያ በስቶክ ገበያ እጅግ ስኬታማ በመሆኑ ሀብቱን 117 ቢሊዯን ተኩል አድርሶለታል።

የኤሎን መስክ ሀብት 90 ቢሊዮን ዶላርን የተሻገረው በዚህ ዓመት የቴስላ ኩባንያ ሼር መመንደጉን ተከትሎ ነበር።

ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ኤለን መስክ መጠነኛ የኮቪድ ምልክቶችን እያሳየ እንደሆነ በትዊተር ሰሌዳው ገልጿል።

ኤሎን መስክ በፈጠራት የጠፈር ታክሲ "ስፔስ ኤክስ" 4 የስነ ፈለክ ተመራማሪዎች ወደ ዓለም አቀፉ የጠፈር ጣቢያ የተሳፈሩት ባለፈው ሳምንት ነበር።

ኤሎን መስስ ተወልዶ ያደገው በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ ሲሆን በ17 ዓመቱ ወደ ካናዳ ካቀና በኃላ ለትምህርት በልውውጥ የስኮላርሺፕ ፕሮግራም ወደ አሜሪካ ፔኒሲልቬኒያ ዩኒቨርስቲ ገባ።

በዚያው አጋጣሚ ነው አሜሪካ የቀረው።

አሁን ነዋሪነቱ በአሜሪካ ሎሳአንጀለስ ካሊፎርኒያ ውስጥ ነው። 49 ዓመቱ ሲሆን የ7 ልጆች አባትም ነው።