ትግራይ፡ ኢትዮጵያ በ76 ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ አወጣች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
76 ወታደራዊ መኮንኖች ከህወሃት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት ህዳር 9/2013 ዓ.ም እንዳሳወቀው 76 ጄኔራሎች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች "ከህወሃት ጋር በመተባበር የሃገር ክህደትን ፈፅመዋል" በሚል የመያዣ ትዕዛዝ እንደወጣባቸው አስታውቋል።
ከነዚህም መካከል በጡረታ የተገለሉ እንደሚገኙበትም ተገልጿል።
ወታደራዊ መኮንኖቹ በሃገር መከላከያ ሰራዊት በስራ ላይ ያሉና በጡረታ የተሰናበቱ ጄኔራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የበታች ሹማምንቶች "ከህወሃት ጋር በመተባበር የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ጥለዋል" በሚል ለህግ ለማቅረብ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንደተቆረጠባቸው ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍል የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በብሄራቸው ምክንያት እየታሰሩ ነው የሚሉ ሪፖርቶች መውጣታቸውን ተከትሎ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃለ አቀባይ ቢልለኔ ስዩም በብሄራቸው እንዳልታሰሩ ገልፃለች።
በርካቶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የምትናገረው ቢልለኔ ይህም "ከወንጀል ኔትወርኮች" ብላ በጠራቸው አባልነት ጋር የተያያዘ እንደሆነም ለቢቢሲ አስረድታለች።
ከቀናት በፊት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተፈላጊ ናቸው ባላቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችንና አባላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በ96 ግለሰቦች ላይ ማውጣቱ ይታወቃል።
ፖሊስ መያዣ ትዕዛዙን ያወጣው ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ "በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል" ያላቸውን ግለሰቦች አድኖ በመያዝ ለሕግ ለማቅረብ መሆኑ መግለፁ ይታወሳል።
በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ከሁለት ሳምንት በላይ ያስቆጠረ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል፤ በአስር ሺዎችም የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንም ተፈናቅለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በትግራይ ክልል ተሰልፈው ያሉ የልዩ ኃይልና ሚሊሻ አባላት ለአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በሠላም እጃቸውን እንዲሰጡ የተቀመጠው የሦስት ቀናት ቀነገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ ተከትሎ የፌደራል ሰራዊቱ ሽረንና ራያን ተቆጣጥሯል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የፌደራል ሰራዊት ከተሞቹን እንደተቆጣጠረ አረጋግጠው "ጊዜያዊ ድል ነው" እንዲሁም "ድል እንደሚቀናጁም" ቃል ገብተዋል።
ኢትዮጵያን በትግራይ ክልል በኩል ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው ድንበር የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ተፈናቃዮች ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ሲሆን እስካሁንም 36 ሺህ ደርሰዋል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥት አገሪቷ "ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ ይገጥማታል" በማለት እያስጠነቀቀ ይገኛል።
"ከፍተኛ የሆነ መፈናቀል በትግራይ ክልል ያጋጥማል ይህ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል። በተቻለም መጠን ለዚህ ቀውስ ለመዘጋጀት እየሞከርን ነው" በማለት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ቃለ አቀባይ ጄንስ ላርክ ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ግጭቱን ፈርተው ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችልም ተመድ አስጠንቅቋል። ከትግራይ ክልል እየተሰደዱ ያሉ ዜጎችን ለመድረስ እንዲችል ያለገደብ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጠር ጠይቋል።
ጎረቤት አገራት ኬንያና ኡጋንዳ ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን አቁመው ወደ ሰላማዊ ድርድር እንዲመጡ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ከህወሃት ጋር ድርድር እንደማይኖር አሳውቋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የህወሃትና የብልፅግና፤ የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት ወደማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ወደ ወታደራዊ ውጊያ ተቀይሯል።
በተለይም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሆነ ፓርላማው ምርጫው በሕገ መንግሥት ትርጓሜ እንዲራዘም ያፀደቀ ቢሆንም የትግራይ ክልል ምርጫ ማድረጉ የበለጠ ነገሩን አክርሮታል።
ምክር ቤቱ ስልጣኑን የሕገ መንግሥት ትርጉም በመስጠት ማራዘሙ ሕገ መንግሥታዊ መሰረት እንደሌለውም የትግራይ ክልል ይጠቅሳል።
የፌደራል መንግሥቱ ደግሞ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ባለው ምርጫም ህወሓት አብላጫ ድምፅ አግኝቶ ሕጋዊ መንግሥት መስርቻለሁ፤ እንዲሁም ዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤልንም የክልሉ ፕሬዚዳንት አድርጌ ሰይሜያለሁ ብሏል።
ሆኖም በትግራይ ክልል የተካሄደው ስድስተኛ ክልላዊ ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠርና ተፈፃሚ የሌለው ነው በማለትም የፌዴሬሽን ምክርቤት ውሳኔ አሳልፏል።
ክልሉ በበኩሉ መስከረም 25/2013 ዓ.ም የፌደራል መንግሥቱ ስልጣን ማብቂያ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፓርላማው ሕጋዊ ስልጣን የላቸውም በማለት፤ ተወካዮቹ በፌዴሬሽንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያላቸውን ውክልናና ኃላፊነት እንዲያነሱ ባቀረበው መሰረት ውክልናቸውን አንስተዋል።
በምላሹም የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንዳያደርግና የፌደራል መንግሥት የትግራይ ሕዝብን የልማትና መሰረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎትን ማዕከል በማድረግ የከተማና፣ ወረዳና ቀበሌ አስተዳደሮችና በክልሉ ከሚገኙ ሕጋዊ ተቋማት ጋር የሥራ ግንኙነት እንደሚያደርግም ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ተግባራዊ እንዲሆን ያወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በህዝብ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል።
ከአስራ ሁለት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የትግራይ ልዩ ኃይል በክልሉ የሚገኘውን የመከላከያ ሰሜን ዕዝ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "አገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትዕዛዝ ተሰጥቶታል" ብለዋል።
የትግራይ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስነዋል ማለቱ ይታወሳል።
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጦርነቱ ውስንና በተወሰኑ የህወሃት አባላት ላይ ያነጣጠረና ህገ መንግሥትን ለማስከበር እየተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልፀው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅ መግለፃቸው ይታወሳል። የትግራይ ክልል በበኩሉ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ጦርነት እንደተከፈተበትና ህዝቡም ላይ ያነጣጠረ ነው ይላል።












