ትግራይ ፡ ልዑካኑ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ይነጋገራሉ እንጂ ድርድር አይኖርም ተባለ

ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሰየሟቸው ልዑካን መፍትሔ ለማፈላለግ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ቢገለጽም ድርድር ግን እንደማይኖር ተገለጸ።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ ሦስት ታዋቂ አፍሪካዉያንን በኢትዮጵያ ውስጥ በተከሰተው ግጭት ዙሪያ እንዲያሸማግሉ የአፍሪካ ሕብረት ልዩ መልዕክተኛ አድርገው እንደሰየሙ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ፕሬዝዳንት ራማፎሳ ይህንኑ ጉዳይ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለተጓዙት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እንደገለጹላቸው የተነገረ ሲሆን፤ መልዕክተኞቹ ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ግጭቱ መፍትሔ በሚያገኝበት መንገድ ላይ ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሏል።
ልዩ መልዕክተኞቹ የቀድሞው የሞዛምቢክ ፕሬዝዳንት ዮአኪም ቺሳኖ፣ የቀድሞዋ የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ኤለን ሰርሊፍ ጆንሰንና የደቡብ አፍሪካ የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት ጋሌማ ሞትላንቴ መሆናቸው ይፋ ተደርጓል።
ወደ አዲስ አበባ በቀጣይ ቀናት ያመራሉ የተባሉት እነዚህ ልኡካን፤ በቀዳሚነት ግጭቱን ለማቆም ከሁሉም ወገኖች ጋር በመነጋገር ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣትና "ግጭቱን ባስከተሉት ጉዳዮች ላይ መፍትሔ ለሚያስገኝ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ ውይይት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራሉ" ተብሏል።
ነገር ግን ይህ ማብራሪያ በአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር ትዊተር ገጽ ላይ ከሰፈረ በኋላ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መረጃ የሚሰጠው የመንግሥት አካል የአስቸኳይ ጊዜ የመረጃ ማጣሪያ ጉዳዩን በተመለከተ ባወጣው ምላሽ ድርድር እንደማይኖር አመልክቷል።
የወጣው መግለጫ እንዳለው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ የአፍሪካ ሕብረት የወቅቱ ሊቀ መንበር ሲሪል ራማፎሳ የሚልኳቸውን ልዩ መልዕክተኞች በግል ተቀብለው እንደሚያነጋግሩ ገልጿል።
ሆኖም ግን፤ "የፌደራል መንግሥትንና በህወሓት ውስጥ የሚገኙ ወንጀለኞችን ለማሸማገል" ልዑካን ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ ተብሎ በመሰራጨት ላይ የሚገኘው ዜና ሐሰት ነው" በማለት "ድርድርን አስመልክቶ የፌደራል መንግሥት ያለው አቋም ፈጽሞ ያልተለወጠ ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ውስጥ የሚገኘው የሠሜን ዕዝ ላይ በትግራይ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞ በርካታ የሠራዊቱ አባላት እንደተገደሉና በካምፑ ውስጥ የነበሩ የጦር መሣሪያዎች እንደተወሰዱ በመግለጽ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ ከጀመረ ሦስተኛ ሳምንቱን ይዟል።
ይህንንም ተከትሎ የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ግጭቱ እንዲቆምና ውይይት እንዲጀመር በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ መንግሥት በግዛቱ ውስጥ እየወሰደ ያለው "ሕግን የማስከበር እርምጃ" በመሆኑ ድርድር እንደማይኖር በተደጋጋሚ ገልጿል።
በዚህም መሰረት ተፈጸሙ ላላቸው ወንጀሎች ተጠያቂ የሆኑ የህወሓት አመራሮችን ለፍርድ ለማቅረብ ጥረት እያደረገ በመሆኑ ለድርድር እንደማይቀመጥ አሳውቋል።
በትግራይ በኩል ያሉ ባለስልጣናት ግን እራስን በራስ የማስተዳደር መብታችንን ተጠቅመን ምርጫ በማካሄዳችንና መብታችንን በማስከበራችን የፌደራል መንግሥቱ የከፈተብን ዘመቻ ነው ሲሉ ይከሳሉ።
በትግራይ ክልል የተከሰተው ቀውስ አሁን ካለበት ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት የህወሓት ባለስልጣንት የአፍሪካ ሕብረትና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት ጣልቃ ገብተው እንዲያሸማግሏቸው ሲጠይቁ እንደነበር ይታወሳል።
በትግራይ ውስጥ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት ተጠናክሮ መቀጠሉን ሁለቱም ወገኖች የገለጹ ሲሆን፤ ትናንት አክሱምና አድዋ ከተሞችን መቆጠጠሩንና ዘመቻው ወደሌሎች ከተሞች መቀጠሉን መንግሥት አስታውቋል።















