ትግራይ፡ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በክልል እና በዞን ደረጃ አዲስ አመራሮች እንደሚሾም አስታወቀ

በትግራይ ክልል እንዲቋቋም የተወሰነው ጊዜያዊ አስተዳደር ከተሰጡት ኃላፊነቶች አንዱ በክልሉ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማስቻል መሆኑ ተገለጸ።
የትግራይ ክልል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው የተሾሙት ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ፤ በትግራይ ክልል ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲካሄድ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ይደረጋል ብለዋል።
"ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነቶች አንዱ በምርጫ ቦርድ መርህ መሠረት በክልሉ ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ እንዲከናወን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው። ሕዝቡ በነፃነት መሪዎቹን ይመርጣል" ብለዋል።
በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የክልሉን አስተዳደር መልሶ እንደሚያዋቅር ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።
"ህወሓት ሕገ ወጥ ምርጫ ነው ያካሄደው። ይህም በፌደሬሽን ምክር ቤት እውቅና አልተሰጠውም። ስለዚህም የክልሉ ምክር ቤት እውቅና የለውም። በክልሉ አመራር ደረጃ ያለውም እውቅና የለውም" ብለው፤ በክልል እና ዞን ደረጃ አዲስ አመራሮች እንደሚሾሙ አስረድተዋል። የመሠረተ ልማት አገልግሎት የሚሰጡ የወረዳ እና ቀበሌ መዋቅሮች ግን ባሉበት ይቀጥላሉ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ለክልሉን እቅድና በጀት ፍቃድ የመስጠት፣ ሕግና ደንብን የማስከበር እንዲሁም የክልሉን ነዋሪዎች መብት የማስጠበቅ ኃላፊነት እንደተሰጠው ተገልጿል።
"አስተዳደሩ እነዚህን ኃላፊነቶች እንዴት እንደሚተገብር ረቂቅ እየነደፈ ነው። የአስተዳደር መዋቅሩ ሲለወጥ ምን መርህ መከተል አለበት የሚለው በረቂቁ ይካተታል" ብለዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሙሉ (ዶ/ር)።
በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሲመረጡ እና ሌሎች ሂደቶች ሲከናወኑን ሕዝቡን እንደሚያማክሩ አያይዘው ገልጸዋል።
በክልሉ ሰላም፣ መረጋጋትና ጸጥታ ማስፈን ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ሲሉም ተናግረዋል።
"ሌላው ኃላፊነት ፍትሕ ማስፈን ነው። የትግራይ ሕዝብ ፍትሕ እና መልካም አስተዳደር በማጣት ተሰቃይቷል። ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህ እንዲለወጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል" ብለዋል።
በሌላ በኩል በግጭቱ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉትን ለመመለስ ከፌደራል ተቋሞችና የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪዎች ጋር እንደሚሠሩ አስረድተዋል።
ትምህርትን ጨምሮ ሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአግባቡ እንዲሰጡ እንደሚያደርጉና በክልሉ የፖለቲካ ምህዳሩን እንደሚያሰፉም ተናግረዋል።
"ጠባብ የፖለቲካ ምህዳርና ዴሞክራሲ ማጣት የክልሉ ችግሮች ነበሩ። የፖለቲካ ምህዳሩን በማስፋት ሁሉንም የክልሉን ፓለቲካዊ ፓርቲዎች እናሳትፋለን" ሲሉ ገልጸዋል።
በትግራይ ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት አገር ኤርትራ ጋር ሰላም ማውረድ እንደሚሹም ጠቁመዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ ሌላው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነት "የፖለቲካ እስረኞችን ጉዳይ የሚመረምር ግብረ ኃይል አቋቁመን እንዲለቀቁ ማድረግ ነው" ብለዋል።
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት በትግራይ ውስጥ በነበረው ሠራዊቱ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ ሕግን ማስከበር ባለው ውሳኔ በክልሉ ኃይሎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰድ መ፥ጀመሩን ተከትሎ በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ ይታወሳል።
በተጨማሪም የአገሪቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የነበረውን የትግራይ ክልል መስተዳደር ሕገወጥ በማለት ከበተነው በኋላ አዲስ ጊዜያዊ አሰተዳደር እንዲመሰረት መወሰኑ ይታወሳል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ የትግራይ ክልልን በሚመለከት ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የሚሰራ ሲሆን፤ በአሁኑ ጊዜ በመንግሥት ሠራዊት በተያዙ አካባቢዎች ያለውን መዋቅር ለማቋቋም ጥረት እያደረገ መሆኑ ተገልጿል።
















