ምርጫ፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትግራይ ክልል የጻፈው ደብዳቤ ወዴት ያደርሳል?

የፎቶው ባለመብት, HoF
የትግራይ ክልል ምርጫ ለማካሄድ ኮሚሽን አቋቁሞ በምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎችንና ግለሰቦችን መዝግቧል። በቅርብ ቀንም ምርጫ የሚካሄድበትን ቀን፣ የመራጮች ምዝገባ መቼ እንደሚሆንና የምርጫ ቅስቀሳ ከመቼ እስከመቼ እንደሚካሄድ እንደሚያስታውቅ ተናግሯል።
በዚህ መሃል የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል መንግሥት ምርጫ ለማካሄድ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ "በአፋጣኝ እንዲያቆም" የሚጠይቅ ደብዳቤ ሐምሌ 21/2012 መጻፉ ተሰምቷል።
ክልሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ በሚጥል ድርጊቱ የሚቀጥል ከሆነ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ እና በሌሎች ሕጎች የተሰጠውን ስልጣን ለመተግበር እንደሚገደድም አስጠንቅቋል።
የሕግ ምሁር የሆኑት አደም ካሴ (ዶ/ር) የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል የሚያካሂደው ምርጫ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ከሆነ ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ እና ሌሎች ሕጎች የተሰጡትን ሥልጣኖች ለመተግበር ይገደዳል ሲል የትኞቹ ሕጎች መጥቀሱ ነው? ስንል ጠይቀናቸዋል።
አደምም (ዶ/ር) ሲመልሱ ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ ዘጠኝ፣ ከዚያም በተጨማሪ ይህንኑ አንቀጽ ለማስፈፀም የወጣው አዋጅ ቁጥር 359 አንቀጽ 12 በግልጽ ጉዳዩን እንደሚያብራሩ ይጠቅሳሉ።
ከዚያም በተጨማሪ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ ላይ ያልተጠቀሰው ነገር ግን፣ የፌደሬሽን ምክር ቤቱን ሙሉ ስልጣንና ሌሎች ነገሮች የሚግዛውም ይህንኑ ለማስፈጸም እንደሚያገለግል ይናገራሉ።
አደም (ዶ/ር) አክለውም አዋጅ ቁጥር 251 መኖሩንም ይገልጻሉ።
በተጨማሪም በምክር ቤቱ ደብዳቤ ላይ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 51 እና 55 (2) መጠቀሳቸውን፣ እንዲሁም ምርጫን በሚመለከት ሕጎችን የማውጣት ስልጣን ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን መደንገጉን መጠቀሳቸውን ያነሳሉ።
ምርጫ የማካሄድ ስልጣን
በፌደራል እና በክልል የሚደረጉ ምርጫዎችን በገለልተኝነት ማካሄድ የሚችለው፤ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ መሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መደንገጉንም በደብዳቤው ላይ መጠቀሱን አደም (ዶ/ር) ገልፀዋል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ የትግራይ ክልል ስድስተኛውን ዙር ምርጫ በክልሉ እንዲካሄድ ወስኖ እየተንቀሳቀሰ ያለው፤ የተጠቀሱትን የሕገ መንግሥት አንቀጾች እና ባለፈው ዓመት የጸደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ በጣሰ መልኩ መሆኑን በደብዳቤ በሚገባ ማስቀመጡን አደም (ዶ/ር) ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አክለውም በደብዳቤው ላይ "ምክር ቤቱ እንደሚለው ሕገ መንግሥቱን ሊያፈርስ የሚችል ሁኔታ አለ ወይ? የሚለው ሁኔታ በሰጠው ትርጓሜ ድምዳሜ ላይ የደረሱ ይመስላል" ሲሉ ይገልጻሉ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ የትግራይ ክልል እርምጃ "ሕገ መንግስቱን የሚቃረን፣ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል እና የኢትዮጵያን የፌደራል ሥርዓት የሚጎዳ አካሄድ" መሆኑን ይገልጻል።
እንደ ሕግ ምሁሩ ማብራሪያ ከሆነ የፌደራል ሥርዓት ዋና መተዳደሪያው፣ የስልጣን ክፍፍሉን በማክበር ላይ የተመሰረተ ነው።
"የፌደራል መንግሥቱ ለክልሎች የተሰጠውን ስልጣን ማክበር፣ ክልሎችም የፌደራሉን ስልጣን ማክበር አለባቸው" ይላሉ። አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ችግር የሚያደርገው በሌላ አገር የሕገ-መንግሥት ፍርድ ቤት በመኖሩ ተጥሷል አልተጣሰም የሚለውን የሚያየው ገለልተኛ ፍርድ ቤት መሆኑን ያስረዳሉ።
ይህ ፍርድ ቤት የክልል መንግሥት የፌደራል መንግሥቱን ስልጣን ወስዷል ወይ የፌደራል መንግሥትስ የክልል ተቀራምቷል የሚለውን የሚወስነው ራሱን የቻለ ነጸ ፍርድ ቤት መሆኑን ይናገራሉ።
በእኛ አገር ያለው ችግር ብለው አደም (ዶ/ር) ሲያስቀምጡ ይህንንም የሚወስነው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑ ነው።
አሁን ግን ሕገ መንግሥቱንም የመተርጎም፤ ማለትም አንድ ክልል የፌደራሉን ስልጣን ወስዷል አልወሰደም የሚለውን መወሰንም ሆነ የዚያን ውጤትም የመወሰን ሥልጣን ያለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት መሆኑ ነገሩን ያጣርሰዋል ሲሉ ያለውን ክፍተት ያሳያሉ።
የፌደሬሽን ምክር ቤት ምን እርምጃ ሊወስድ ይችላል?
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰኔ መጨረሻ ላይ ባካሄደው ስብሰባ፤ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል።
ምክር ቤቱ ከውሳኔው ላይ የደረሰው፤ ምርጫ ማራዘምን በተመለከተ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንዲሰጥበት የውሳኔ ሀሳብ ካቀረበለት በኋላ ነበር።
በሰኔ ወር ምርጫን በተመለከተ ምክር ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ትርጓሜ ነው የሚሉት አደም (ዶ/ር) ሕገ መንግሥቱን ማክበር አለባችሁ አለበለዚያ ግን ሕገ መንግስቱ አንቀጽ 62 ንዑስ አንቀጽ ዘጠኝ የሚለውን ስለሚያዛባ የፌደራል ጣልቃ ገብነትን እናዛለን በሚል አስቀምጠውታል ብለዋል።
እንደ አደም ካሴ (ዶ/ር) ከሆነ የፌደራል ጣልቃ ገብነት በተለይ አዋጅ ቁጥር 359 አንቀጽ 12 እና ቀጥሎ ያሉትን በመጥቀስ ሙሉ ዝርዝር ባይኖርም በተለይ ሁለት ነገሮችን እንደሚያወጣ ይናገራሉ።
የፌደራል ፖሊስን ወይም መከላከያ ሠራዊትን ማሰማራት
አንደኛው የፌደራል ፖሊስን ወይንም መከላከያ ሠራዊትን ሊያሰማራ ይችላል ይላል። ከዚያም አልፎ የክልሉን ምክር ቤትና ካቢኔ አውርዶ ጊዜያዊ አስተዳደርን ሊያቋቁም እንደሚችል ይደነግጋል ሲሉ ይጠቅሳሉ።
እንግዲህ ይህ እንደመጨረሻ አማራጭ መቅረቡን የሚናገሩት አደም (ዶ/ር) እነዚህ ነገሮች የግድ መሆን አለባቸው ማለት ግን አለመሆኑን ያሰምሩበታል።
የፌደራል ጣልቃ ገብነት የሚለው ሰፋ ያለ ትርጓሜ ቢኖረውም በአዋጁ ላይ በግልጽ የተጠቀሱት እነዚህ መሆናቸውን ያመለክታሉ።
በሕጉ ማዕቀፍ ዋናው ጥያቄ ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል አልተጣሰም የሚለው መሆኑን በመናገርም፤ በዚህ ሃሳብ ከተስማማን ምን እርምጃ ይወስዳል የሚለው ግልጽ መሆኑን ይናገራሉ።
ነገር ግን በኢትዮጵያ ውስጥ ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል አልተጣሰም ብሎ የሚወስነው አካል የፌደራሉ ፖለቲካዊ ተቋም በመሆኑ ሁኔታውን ፈታኝ እንደሚያደርገው ያስረዳሉ።
ይህ ደግሞ ውሳኔው የተወሰነው ለፖለቲካዊ ጥቅም ተብሎ ነው ወደ ሚል አንድምታ እንደሚወስድ ይጠቅሳሉ።
እንደውም ይላሉ አደም (ዶ/ር) የፌዴሬሸን ምክር ቤት የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ጣልቃ ግባ ብሎ ካዘዘ እምቢ ማለት እንደማይቻልና "ትዕዛዝ" መሆኑንም ይናገራሉ።
ሌሎች አማራጮች
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በትግርኛ ቋንቋ በሰጡት ቃለመጠይቅ ላይ በዚሁ ጉዳይ ተጠይቀው የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ እንደማይገባ እቅዱም ሆነ ፍላጎቱ እንደሌለው መናገራቸውን በማስታወስ ነገር ግን በዚህ አንቀጽ መሰረት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ካዘዘ እምቢ የማለት አማራጭ እንደሌለ ያብራራሉ።
በዚህም ከኃይል እርምጃ ይልቅ ሌሎች አማራቾች ሊኖሩ እንደሚችሉ አደም (ዶ/ር) በመጥቀስ ቀለል ያለው ከፌደራል መንግሥቱ ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማ ማቆም መሆኑን በማብራሪያቸው ላይ ይጠቅሳሉ።
ከዚህ ባለፈ የመሰረታዊ ፖለቲካዊ መብቶችን ይጥሳል ብሎ የሚል ከሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጋር በጋራ በመሰብሰብ ውሳኔ ሊያሳልፉ እንደሚችሉም ይገልፃሉ።
እንደ ሕግ ምሁሩ ከሆነ ዋናው ጥያቄ 'የትግራይ ክልል ምርጫ ማከናወኑ ወይም ለማከናወን መወሰኑ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ያፈርሳል ወይ?' የሚለውን መመለስ እንዳለበት ያስረዳሉ።
እንደ አገር ሕግ የበላይነትን ማስከበር ላይ የፖለቲካ ሥርዓታችን ጠንካራ ቢሆን ኖሮ ይህ ጥያቄ አያስፈልግም ነበር የሚሉት አደም (ዶ/ር)፤ "አንድ የፖለቲካ ሥርዓት በሕግ በተዘረጋው ሜዳ ላይ የምንጫወተው ጨዋታ ነው" ካሉ በኋላ የፌደራል ሥርዓቱ የሚቆመው በሥልጣን ክፍፍሉ መከባበር ላይ መሆኑን ይናገራሉ።
ያ ካልተከበረ ዛሬ በምርጫ ጉዳይ አይሆንም እንደተባለው ሁሉ በሌላ ጊዜ በሌላ ጉዳይ ላይ አይሆንም ሊባል እንደሚችል ያነሳሉ።
ጨምረውም አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥረዓቱ ከባድ ፈተና ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ የፌዴሬሸን ምክር ቤት ይህንን ማለቱ እንደማስጠንቀቂያ ጥሩ ቢሆንም፤ ነገር ግን ቶሎ ወደ ውሳኔ ከመግባት ይልቅ በመነጋገር ወደ መፍትሄ መምጣት አስፈላጊ መሆኑን ያሰምሩበታል።
የፌዴሬሸን ምክር ቤት አሁን የጻፈውም ደብዳቤ ሆነ በሰኔ መጨረሻ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ከሕግ አንጻር ትክክል እንደሆነ በመጥቀስም፤ የትግራይ ክልል አይሆንም የሚል እንኳ ቢሆን ሕገ መንግሥቱ ይፈቅድልናል፣ ሕገ መንግሥቱ ላይ የቀረበው ትርጓሜ ስህተት ነው በማለት የራሳቸውን ትርጓሜ ማቅረብ መፍትሄ መሆን እንደነበረበት ያነሳሉ።
በመርህ ደረጃ የሕገ መንግሥት የበላይነት፣ የሕግ የበላይነት መከበር አለበት የሚሉት አደም (ዶ/ር) ነገር ግን አስቸጋሪ ውሳኔ መሆኑን አልሸሸጉም።
በፌደራልና በክልሎች መካከል ያለውን የሥልጣን ክፍፍል የሚወስነው የፌዴሬሽነ ምክር ቤት ሲሆን ያንን ደግሞ የሚያስፈጽመው የሚኒስትሮች ምክር ቤት መሆኑን በመጥቀስ ይህንን የምክር ቤቱን ውሳኔ የማስፈፀም ኃላፊነት የእነርሱ መሆኑን ይናገራሉ።
በተለይ ደግሞ ሰኔ ላይ የነበረው ውሳኔ የፌደራል ምርጫን ብቻ ሳይሆን የክልል ምርጫንም እንደሚሸፍን ግልጽ ነበር ደብዳቤውም ይህንን ግልጽ አድርጎታል የሚሉት አደም (ዶ/ር)፤ የትግራይ ክልል በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሥልጣን አለን በሚል የተንቀሳቀሱት የትግራይ ክልል አመራሮች ስህተት መስራታቸውን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደብዳቤ በግልጽ አስቀምጦታል ብለዋል።
ደብዳቤው በግልጽ የሚያሳየው ሕገመንግሥቱን የመተርጎም ስልጣን ያለው የፌደሬሸን ምክር ቤት፣ የምርጫ ሕግ የማውጣት የምርጫ ሕግን የማስፈፀም፣ የምርጫ ቦርድ የማቋቋም የፌደራል መሆኑን በማስቀመጥ የትግራይ ክልል ሕገ መንግስታዊ መብቴ ነው በሚል የወሰደውን እርምጃ ይህንን የሚያፋልስ መሆኑን ያስረዳሉ።















