የትግራይ ምክር ቤት አምስት የምርጫ ኮሚሽን አመራሮችን ሹመት አጸደቀ

መምህር ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም

የፎቶው ባለመብት, ABEL GUESH

የትግራይ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ዛሬ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ ነሐሴ መጨረሻ ላይ ይካሄዳል ለተባለው 6ኛ ክልላዊ ምርጫ የሚያስፈጽሙ የምርጫ ኮሚሽን አመራሮች ሹመት ሰጠ።

በዚህ መሰረት፤ አቶ ሙሉወርቅ ኪዳነማርያም፣ የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ሆኖው ሲሾሙ፤ ወይዘሮ ጽጌሬዳ ዲበኩሉ ደግሞ ምክትል ሆነዋል።

አቶ መረሳ ጸሃየ፣ አቶ መሀመድ ስዒድ ሐጎስና ዶክተር ጸጋ ብርሃነ ደግሞ፣ የኮሚሽኑ የስራ አመራር በመሆን ተመርጠዋል።

በትግራይ በሚካሄደው ክልላዊ ምርጫ፤ ገዢው ድርጅት ህወሐት ጨምሮ ሌሎች በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

6ኛ አገር አቀፍ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ምክንያት እንደተራዘመ ይታወሳል።

በኮቪድ -19 ምክንያት አገራዊ ምርጫ ቢራዘምም የትግራይ ክልል ግን ክልላዊ ምርጫ ለማካሄድ በመወሰን ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር ይታወሳል።

ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑን በመግለጽ ማስፈፀም እንደማይችል መግለፁን ተከትሎ ክልሉ የራሱን ኮሚሽን ለማቋቋም ሲንቀሳቀስ ነበር።

ከባለፈው ሳምንት ቅዳሜ እስከ ማክሰኞ ድረስም ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የኮሚሽኑ አባላት ይሆናሉ የተባሉ ሰዎች ሲጠቆሙ ቆይተዋል።

ከተጠቆሙት 776 ሰዎች መካከል አስር ተመርጠውም በትናንትናው እለት ከክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጋር ሶስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀምጠው አስር ግለሰቦችን ለኮሚሽነሩ የቦርድ አባልነት በእጩነት መርጠዋል።

ከ776 በቅድሚያ 177 ሰዎች መጣራታቸውን በመቀጠልም ከእነዚህ መካከል አስሩ መመረጣቸው በትናንትናው እለት ተገልጿል።

የተመረጡት ሰዎች በመቀለ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን፣ የታሪክና ሕግ ምሁራን መሆናቸው ተገልጿል።

በትግራይ ክልል በሚካሄደው ቀጣይ ምርጫ ህወሃትን ጨምሮ ሶሰት ፓርቲዎች እንደሚሳተፉ የታወቀ ሲሆን፣ አረና እና ትግራይ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ግን እንደማይሳተፉ አስታውቀዋል።

በትግራይ ክልል በምርጫ ለመሳተፍ እየተዘጋጁ ከሚገኙት ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ሳልሳይ ወያነ፣ የትግራይ ብሔራዊ ሸንጎ እና ውናት የተባሉት ፓርቲዎች ይገኙበታል።

ትናንት በነበረው ውይይት ከተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመነጋገር የተመረጡ አምስት የኮሚሽኑ አመራሮችን ለክልሉ ምክር ቤት ያቀረበው ህወሓት መሆኑም ተገልጿል።