እውን የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ማካሄድ ይችላል?

አንዲት ሴት ድምጻቸውን ሲሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ድምጽ የሰጡ ሴት

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ በነሐሴ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረው አገር አቀፍ ምርጫ እንዲራዘም መደረጉ ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ አገራዊው ምርጫ በጊዜው እንዲካሄድ ሲጠይቅ የነበረው ህወሓት፤ የ2012 አገራዊ ምርጫ በማንኛውም ሁኔታ መካሄድ አለበት፤ ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ እናካሂዳለን የሚል ይዘት ያለው የአቋም መግለጫ ከአምስት ወር በፊት አስነብቦ ነበር።

ይህንኑ አቋሙን ሰሞኑን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ በድጋሚ አስነብቧል። በዚህም የተነሳ በእርግጥ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ማካሄድ ይችላል? የሚለው የበርካቶች ጥያቄ ሆኗል።

የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ነጋ ተገኝ፤ ይህ ቀደም ብሎ የነበረ አቋም መሆኑን በመግለጽ አዲስ የተወሰነ ውሳኔ መኖሩን እንደማያውቁ ይናገራሉ።

"በቅርቡ በዚህ ጉዳይ ላይ አልተነጋገርንም፤ ቀደም ብሎ የወሰድነው አቋም ነው" ያሉት አቶ ነጋ ምናልባት የሥራ አስፈፃሚው አባላት ተነጋግረው ጽሑፉ በፌስ ቡክ ላይ እንዲወጣ አድርገው እንደሆነ መረጃው እንደሌላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት ግን አገሪቷ ላይ ምርጫ የማይደረግ ከሆነ እኛ እናካሂዳለን የሚል አቋም በመያዝ ምርጫውን እንዴት ማስፈፀም ይቻላል በሚለው ላይ በደንብ መወያየት እንዳለባቸው መነጋገራቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

"በዚህ ወቅት ግን በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ በዚህ ጉዳይ አልተነጋገርንም" ያሉት አቶ ነጋ ህወሓት ምርጫው መካሄድ እንዳለበት የያዘው አቋም ከስምንት ወራት በፊት የነበረ መሆኑን ያስታውሳሉ።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የፓርቲው ሚዲያ እና ኮሚኒኬሽን ተጠሪ ጋር ብንደውልም ኃላፊውን ማግኘት ሳንችል ቀርተናል።

በርግጥ የወሓት የምርጫ አካሄዳለሁ አቋም ሕጋዊ መሰረት አለው?

ዶ/ር አደም ካሴ በኔዘርላንድስ የአስተዳደር እና ዲሞክራሲ አማካሪ ናቸው። ምርጫን የማካሄድ፣ የምርጫ ሕግን የማውጣት፣ የወጣውን ደግሞ ማስተዳደር ሥልጣን ያለው የፌደራሉ መንግሥቱና ምርጫ ቦርድ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ከዚያ ውጪ የህወሓት አመራሮች ሕጉን ተከትለው ካልተቃወሙ በስተቀር በራሳቸው ዝም ብሎ መሄድ ስልጣኑም የላቸውም ይላሉ።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ደግሞ የሕግ አማካሪው አቶ ኤፍሬም ታምራት ናቸው። አቶ ኤፍሬም "ምርጫን በሚመለከት ሊጠሩ የሚገቡ ነጥቦች አሉ ብዬ አስባለሁ" ካሉ በኋላ ምርጫ በዋናነት አላማው ዜጎች በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ራሳቸው በቀጥታ ወይንም በተወካዮቻቸው አማካኝነት የመሳተፍ መብት ከሚለው እሳቤ መመንጨቱን ያስረዳሉ።

በዚህም የተነሳ የምርጫ ሥርዓት መዘርጋቱን፣ ዜጎችም መምረጥና የመመረጥ መብት እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ።

"መንግሥት የሕዝቦች ፈቃድ ነው ስለሚባል ዜጎችን በመምረጥና በመመረጥ ማሳተፍ ብቻ ሳይሆን ምርጫው ነፃና ገለልተኛ መሆን አለበት" የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ በዚህም የተነሳ በሕገ መንግሥቱ ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ መቋቋሙን ይናገራሉ።

"ይህ ምርጫ ቦርድ የፌደራል የዲሞክራሲያዊ ተቋም ነው። በክልል ጽህፈት ቤቶች አሉት። አገር አቀፍ ምርጫ ባልተደረገበት በክልል ምርጫ እንደርጋለን ማለት፣ የፌደራል ዲሞክራሲያዊ ተቋም ባልተሳተፈበት፣ ባልታዘበበት ምርጫ ማድረግ የምርጫውን ሕጋዊነት፣ ነፃና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል" በማለትም ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ህወሓት፤ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያብራራሉ።

"ምርጫ ሲባል ዝም ብሎ አንድ ቀን ሄዶ መምረጥ አይደለም" የሚሉት ዶ/ር አደም በበኩላቸው "በቅድሚያ የምርጫ ወረዳዎች መወሰን አለባቸው። ያለውን እንኳ ይጠቀማሉ ቢባል ያም እንደገና መወሰን አለበት። ከዚያም ሲያልፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገብ ያስፈልጋቸዋል" በማለት ሂደቱን ያብራራሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመዘገቡ በኋላ ምልክታቸውን ማሳወቅ፣ መራጮች መመዝገብ፣ ቅስቀሳ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ በማስታወስ ህወሓት "ሁሉን ነገር የማድረግ የሕግ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን በተግባር አቅምም፤ ተቋማዊ ዝግጅትም አለው ብዬ አላስብም" ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም በበኩላቸው ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫውን ሲያራዝም አገሪቱ በኮሮናቫይረስ ውስጥ ስላለች ነው በማለት "አሁን ባለንበት ሁኔታ የተለያዩ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ይገደባሉ" ይላሉ።

እነዚህ መብቶች መካከል ደግሞ የመመረጥና የመምረጥ መብት እንደሚገኝበት በመግለጽ ይህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረ፣ ምርጫ ቦርድም በሕገ መንግሥቱ መነሻነት ያንን ውሳኔ ማሳለፉን ይገልፃሉ።

"ስለዚህ ሁኔታዎች ተሻሽለው ወደ መደበኛው ሕይወት እስክንመለስ ድረስ ስለምርጫ የምናወራበት ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ያለን አይመስለኝም" ይላሉ።

ዶ/ር አደም በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ወይንም ህወሓት ምርጫውን አደርጋለሁ ብሎ እርምጃ ቢጀምር ያ ተቋም ነፃነት አለው ወይ? በሌሎቹ ይታመናል ወይ? እንደምርጫ ቦርድ ሆኖ የሚያገለግል ተቋማዊ መዋቅር ይኖረዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት "እኔ ግን አለው ብዬ አላምንም" ይላሉ።

መፍትሔው ታዲያ ምንድን ነው?

የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬምም ሆኑ የአስተዳደርና ዲሞክራሲ አማካሪው ዶ/ር አደም ለተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመግባባት ከመነጋገር የተሻለ ሌላ አማራጭ አይታያቸውም።

"የዚህ ችግር ምንጩ በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲና በህወሓት ወይንም በነባሩ ኢህአዴግ መካከል ያለ የፖለቲካ ግጭት ነው" የሚሉት ዶ/ር አደም "የተወሰዱ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ሕጉን ይጥሳሉ ወይም ይቃረናሉ የሚሉ ከሆነ፤ አይ እኔ ምርጫ አካሄዳለሁ ማለት ሳይሆን . . . ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ፣ ከዚያም አልፎ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሄዶ ለመፍታት መሞከር ይሻላል" በማለት ይመክራሉ።

"ምናልባት እነርሱ ሕጉን ጥሰዋል እኛም ሕጉን እንጥሳለን ከሆነ፤ የአንድ ጥሰት ሌላኛውን ጥሰት ትክክል አያደርገውም" በማለትም እንዲህ አይነት ቅራኔ ምንጩ ፖለቲካዊ ግጭት በመሆኑ ከሕግ ይልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ጉዳዩ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና የቦርዱ ቃል አቀባይ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።