የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት

የፎቶው ባለመብት, HOF ETH

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ጣልቃ እንዲገባና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወሰነ።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ጥቅምት 28/2013 ዓ.ም ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋምና ሌሎች ውሳኔዎችን መወሰኑን አስታውቋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ክልል በክልሉ የሚገኘው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በማድረስና በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሁ ጉዳት በማድረሱ ህገ መንግሥቱን ማስከበር አስፈላጊ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም መሰረት የፌዴራል መንግሥት በክልሎች ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓት ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/95 መሰረት ተፈፃሚ እንደሚሆንም አሳውቋል።

የፌደራል መንግሥት በአዋጁ መሰረት በክልሉ ጣልቃ የሚገባባቸው ተብለው የተጠቀሱት "በትጥቅ የተደገፈ የአመጽ እንቅስቃሴ ማድረግ፤ከሌላ ክልል ወይም ከሌላ ክልል ብሔር፣ ብሄረሰብ ወይም ሕዝብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮችን ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ መፍታት የሚሉ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም የፌዴራሉን ሰላምና ጸጥታ ማናጋት ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደሆነ" ጠቅሷል።

"የትግራይ ክልል መንግስት ሕገመንግስታዊ እና የፌዴራል ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ድርጊት በመፈጸም የፌዴሬሽኑን ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ስለሆነ ይህንን ድርጊት ማስቆም ተገቢ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ " ብሏል

ምክር ቤቱ በአንድ ክልል ውስጥ "ሕገመንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ ወድቋል" ብሎ ሲያምን የፌዴራሉ መንግስት ተገቢና ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ ማዘዝ እንደሚችል በህገ መንግሥቱና በአዋጆቹ የተሰጠውን ስልጣን በመጠቀም የፌደራል መንግሥቱ ጣልቃ መግባት አስፈላጊ መሆኑን ተናግሯል።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁም ጋር በተጣጣመ መልኩ የፌደራል ፖሊስን ወይም የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ወይንም ሁለቱንም በክልሉ እንዲያሰማራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ እንደተሰጠም መግለጫው አክሏል።

የትግራይ ክልል ምክር ቤት እና የክልሉ ከፍተኛ የህግ አስፈፃሚ አካል እንዲታገድና ለፌደራል መንግሥቱ ተጠሪ የሆነና ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲቋቋም ወስኗል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚኖረውንም ስልጣን ያስቀመጠ ሲሆን እነዚሀም

  • አስፈፃሚ አካሉን ይመራል፤ ያስተባብራል
  • የጊዜያዊ አስተዳደሩን ኃላፊዎች ይመድባል፤ ህግና ሥርዓት መስፈኑን ያረጋግጣል፤
  • አግባብ ባለው ህግ መሰረት በክልሉ ምርጫ የሚከናወንበትን ሁኔታ ያመቻቻል
  • የክልሉን እቅድና በጀት ያፀድቃል።
  • በፌደራል መንግሥት የሚሰጡ ሌሎች ተግባራትን ያከናውናል።

የክልሉ መንግሥት መስከረም 25/2013 ዓ.ም የፌደራል መንግሥቱ ስልጣን ማብቂያ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፓርላማው ሕጋዊ ስልጣን የላቸውም በማለቱ፤ የትግራይ ክልል ተወካዮች በፌዴሬሽንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ያላቸውን ውክልና ኃላፊነት መልቀቃቸው የሚታወስ ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሻከረ የመጣው የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥት ግንኙነት የማይታረቅ ደረጃ ደርሶ ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ህወሃት በትግራይ የሚገኘው የመከላካያ ካምፕ ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልፀው ጦርነት መከፈቱን አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ቀርበው የመከላከያ ሠራዊት በኮማንድ ፖስት እየተመራ "ሀገሩን የማዳን ተልዕኮውን እንዲወጣ ትእዛዝ ተሰጥቶታል" ብለዋል።

የትግራይ ክልል በበኩሉ በክልሉ የሚገኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላትና አዛዦች ከትግራይ ክልል መንግሥት ጎን ለመሰለፍ ወስነዋል ብሏል።