ትግራይ፡ በባሕር ዳር ከተማ ላይ ለሦስተኛ ጊዜ ጥቃት መፈጸሙ ተነገረ

ባሕር ዳር

ዛሬ ንጋት 12፡20 አካባቢ በባሕር ዳር ከተማ ላይ በሁለት ሳምንት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ከባድ የፍንዳታ ድምጽ መሰማቱን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ሦስት ፍንዳታ መስማታቸውን ሲናገሩ ሌላኛው ነዋሪ ደግሞ ሁለት የፍንዳታ ድምጽ መስማታቸውንና ከዚህ ቀደም ከተፈጸሙት የሮኬት ጥቃቶች ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ ንጋት ላይ ቢያንስ ሁለት ከባድ የፍንዳታ ድምጽ በከተማዋ መሰማቱን አረጋግጧል።

በጉዳዩ ላይ እስካሁን የክልሉ መንግሥትም ሆነ የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ያሉት ነገር የለም።

ቢቢሲ የዛሬ ጠዋቱ ፍንዳታ የሮኬት ጥቃት ስለመሆኑና ጥቃቱ ዒላማ ምን እንደነበረ እንዲሁም የደረሰ ጉዳት መኖር አለመኖሩን እስካሁን ማረጋገጥ አልቻለም።

ከዚህ ቀደም የሮኬት ፍንፍንዳታዎቹን ተከትሎ የተኩስ ድምጽ ይሰማ እንደነበረ ያስታወሱት ነዋሪዎቹ፤ ዛሬ ንጋት ላይ ካጋጠመው ፍንዳታ በኋላ ግን ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ አለመሰማቱን ተናግረዋል።

ጥቃቱን በተመለከተ ከአማራ ክልልም ሆነ ከፌደራል መንግሥቱ የተሰጠ ምንም መግለጫ የሌለ ሲሆን፤ ሰኞ ከሰዓት በኋላ በትግራይ ቴሌቪዝን ላይ ጥቃቱ የባሕር ዳር አውሮፕላን ማረፊያን ኢላማ አድርጎ በህወሓት መፈጸሙን ተገልጿል።

ከዚህ ቀደም ኅዳር 05 እና ባለፈው ሳምንት ማብቂያ አርብ ኅዳር 11/2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ኃይሎች የሮኬት ጥቃቶች በከተማ ላይ ተፈጽመው የነበረ ሲሆን ዛሬ ንጋት ላይ የተፈጸመው ፍንዳታ በከተማዋ ውስጥ ሲያጋጥም ለሦስተኛ ጊዜ መሆኑ ነው።

ከዚህ ቀደም በባሕዳር ከተማ ላይ ሁለት ጊዜ እንዲሁም በጎንደር ከተማ ላይ አንድ የሮኬት ጥቃት የተፈጸመ ሲሆን ከሁለቱ ከተሞች በተጨማሪም ወደ ኤርትራ መዲና አሥመራም ሮኬት ተተኩሶ እንደነበረ ይታወሳል።

ከዚህ በፊት በባሕር ዳር ከተማ ላይ የተፈሙት ሁለት የሮኬት ጥቃቶች ጉዳት አለማድረሳቸው የተገለጸ ሲሆን ኢላማ ያደረጉትም በከተማዋ የሚገኘውን አየር ማረፊያ ነበር ተብሏል።

ለእነዚህ የሮኬት ጥቃቶች የህውሓት ከፍተኛ አመራሮች ኃላፊነቱን ወስደዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሜጀር ጀነራል ይልማ መርዳሳ በሮኬት ጥቃቱ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን በሚመራው ህወሓት መካከል ለወራት የቆየው አለመግባባትና መካሰስ ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በተናጠል የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መባባሱ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ በክልሉ ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማዘዛቸውን ተከትሎ ፍጥጫው ወደ ግጭት አምርቶ ሦስተኛ ሳምንቱን ሊደፍን ተቃርቧል።