ትግራይ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለህወሓት ኃይሎች የመጨረሻ ያሉትን ቀነ ገደብ አስቀመጡ

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL TEWELDE

የአገሪቱ ሠራዊት ወደ መቀለ እየተጠጋ ባለበት በአሁኑ ሠዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በክልሉ ዋና ከተማ ውስጥ ያሉ አመራሮችና ኃይሎች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ የመጨረሻ ያሉትን የሦሰት ቀናት ቀነ ገደብ አስቀመጡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመጨረሻው ምዕራፍ ነው ያሉትና የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ወደ ክልሉ ዋና ከተማ በሚያደረገው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት በሰው ላይና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ለህወሓት አመራሮች፣ ለልዩ ኃይሉና ለሚሊሻ አባላት ጥሪ አቅርበዋል።

ጨምረውም በዘመቻው ነዋሪው ከሠራዊቱ ጋር በመተባበር ሊደርስ የሚችል ጉዳትን እንዲከላከል ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፤ የህወሓት አመራሩና የትግራይ ኃይል እጃቸውን በሰላም እንዲሰጡ የ72 ሰዓታት የመጨረሻ የጊዜ ገደብ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስቀምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከሳምንት በፊት ለልዩ ኃይሉ እና ሚሊሻ አባላት ተመሳሳይ ቀነ ገደብ አስቀምጠው የነበረ ሲሆን ቀነ ገደቡ ሲጠናቀቅ መንግሥት በቀናት ውስጥ የመጨረሻውን ሕግን የማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ መግለጻቸው ይታወሳል።

ይህ አሁን ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ሠራዊቱ ወደ ዋና ከተማዋ መቀለ መቃረቡን ተከትሎ መሆኑን አመልክተው በከተማዋና በነዋሪው ላይ ሊደርስ የሚችልን ጉዳት ለመቀነስ እንደሆነ ገልጸዋል።

በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል ለሳምንታት የዘለቀው ወታደራዊ ግጭት ወደ ሦስተኛው ምዕራፍ መሸጋገሩን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በትግራይ ክልል የጀመርነው ሕግን የማስከበር እርምጃ ሁለተኛ ምዕራፍ ተጠናቅቋል" በማለት የመጨረሻውና ወሳኝ ባሉት በሦስተኛው ምዕራፍ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በሁለተኛ ምዕራፍ ዘመቻ የክልሉን የተለያዩ ቦታዎችን በማስለቀቅ "አመራሩ የመሸገባትን ዋና ከተማዋን መቀለን መክበብ ነበር" በማለት፤ በዚህም ሠራዊቱ ዕቅዱን በማሳካት ወደ ቀጣይ ምዕራፍ መሸጋገሩን ገልጸዋል።

በጥቅምት ወር የመጨረሻ ሳምንት በትግራይ ክልል ውስጥ በሚገኘው የሠሜን ዕዝ ላይ በትግራይ ክልል ኃይሎች ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ በፌደራል መንግሥቱ መውሰድ በጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ በርካታ የትግራይ አካባቢዎችን መቆጣጠሩን ገልጾ ሠራዊቱ ወደ መቀለ ከተማ እያመራ መሆኑ ተነግሯል።

ይህንንም ተከትሎ የዘመቻው ሦስተኛው ምዕራፍ በመቀለ የሚካሄድ እንደሆነና "ሕግ የማስከበር የመጨረሻው እርምጃ ነው" በማለት፤ ይህ ዘመቻ ከፍተኛ ጥበብ፣ ጥንቃቄና ትዕግሥት የሚፈልግ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይ ክልልን በሚያስተዳድረው በህወሓት መካከለው ለወራት የቆየው አለመግባባት ከማይታረቅበት ደረጃ ላይ ደርሶ ወደ ወታደራዊ ግጭት ተሸጋግሮ የመንግሥት ኃይሎች የክልሉን ቁል ከተሞች ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እንደተቆጣጠሩ እየተነገረ ነው።

ሦስተኛ ሳምንቱን ሊደፍን በተቃረበው ወታደራዊ ግጭት ከፍተኛ መጠን ያለው ሞትና ጉዳት እንዳጋጠመ ቢነገርም በትግራይ ክልል ያሉ የስልክና የኢንተርኔት የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው ትክክለኛውን መረጃና አሃዝ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል።

በተጨማሪም ቁጥራቸው ከ30 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ግጭቱን በመሸሽ ወደ ጎረቤት አገር ሱዳን መሰደዳቸውና በችግር ላይ እንደሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች እያሳወቁ ሲሆን፤ መንግሥትም በበኩሉ እነዚህን ሰዎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሆነ አመልክቷል።