አሜሪካዊያን ከ20 ቀን በኋላ የኮቪድ ክትባት መከተብ ይጀምራሉ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ የኮሮናቫይረስ ክትባት መርሐግብር ቢሮ ኃላፊ የመጀመርያው አሜሪካዊ ተከታቢ በዲሴምበር 11 (ታኀሣሥ 2) ክትባት ሊያገኝ እንደሚችል ጠቆሙ።
ይህም ማለት የመጀመርያው ተከታቢ የኮቪድ ክትባት ለመውሰድ ከ20 ቀናት ያነሰ ጊዜ ነው የቀረው ማለት ነው።
ኃላፊው ዶ/ር ሞንሴፍ ስሎይ ለሲኤንኤን እንደተናገሩት መሥሪያ ቤታቸው እያቀደ ያለው ይህ ክትባት ከሚመለከተው መሥሪያ ቤት ፍቃድ ባገኘ በ24 ሰዓታት ውስጥ ክትባቱን ወደ ጤና ጣቢያዎች ለማጓጓዝ ነው።
ይህም ክትባቱን ወደ ዜጎች ለማድረስ አንዲትም ሰኮንድ እንዳትባክን ለማድረግ ነው።
አሜሪካ በአሁን ሰዓት ታይቶም ተሰምቶም በማይታወቅ ፍጥነት በተህዋሲው ወረርሽኝ እየተጠቃች ነው።
አሁን በተህዋሲው የተያዙት አሜሪካዊያን ቁጥር ከ12 ሚሊዮን ማለፉ ብቻ ሳይሆን በቀን የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 200ሺ አካባቢ መጠጋቱ አገሪቱን አጣብቂኝ ውስጥ ከቷታል።
ወረርሽኙ አሜሪካ ከገባ ወዲህ 255ሺ ዜጎች ሕይታቸውን አጥተዋል።
በዚህን ያህል ቁጥር ተህዋሲው ነፍስ ያጠፋበት ሌላ አገር የለም።
ፋይዘር የተባለው እውቅ የመድኃት አምራች ኩባንያ ከጀርመኑ ባዯንቴክ ጋር በመሆን ላመረተውን መድኃኒት የእውቅና ጥያቄን ለሚመለከተው ክፍል ያቀረበው ባለፈው አርብ ነበር።
ፋይዘርና አጋሩ ያመረቱት የክትባት ዓይነት የፈውስ ምጣኔው 95 ከመቶ ነው ተብሏል።
አንድ ሰው ከኮቪድ ተህዋሲ ለመጠበቅ ይህን ክትባት በተለያየ ጊዜ ሁለት ጠብታ መውሰድ ይኖርበታል። ፋይዘርና አጋሩ እስከዚህ እስከያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት ብቻ 50 ሚሊዮን የሚሆን ጠብታ ለማምረት ሁሉን ዓቀፍ ዝግጅቱን አጠናቋል።
ይህም ማለት የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሊገባደድ አንድ ወር ገደማ ብቻ ነው ስለቀረው በአንድ ወር 50 ሚሊዮን ጠብታ ያመርታል ማለት ነው።
የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት አስተዳደር የአማካሪዎች ምክር ቤት ልዩ ኮሚቴ በዲሴምበር 10 ይህን ክትባት ፍቃድ በመስጠት ጉዳይ ላይ ስብሰባ ይቀመጣል። ይህ ማለት ከ17 ቀናት በኋላ ነው የሚሆነው።
ዶ/ር ስሎይ የሚሉት ታዲያ ይህ ኮሚቴ በተሰበሰበና መድኃኒቱ የምርት ይሁንታን ባገኘ በነገታው ክትባቶች ወደ ጤና ጣቢያዎች ይደርሳሉ።
ሞዴርና የተሰኘው ሌላው የመድኃኒት አምራች በበኩሉ እንደ ፋይዘር ሁሉ የፈውስ ምጣኔው 95 ከመቶ የሆነ ሌላ ክትባት መሥራቱን ይፋ አድርጓል።
ሞዴርና እንደ ፋይዘር ሁሉ በሚቀጥሉት ሳምንታት እውቅናና ፈቃድ እንዲሰጠው ማመልከቻ ያስገባል ተብሎ ይጠበቃል።
ሀብታም አገራት ከነዚህ ሁለት ኩባንያዎች ጋር የመድኃኒት ምርት ስምምነት እያደረጉ ነው። ድሀ አገራት በዚህ ረገድ እጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን ይችላል የሚለው አሁንም እያነጋገረ ነው።
















