ፋይዘር አዲሱ ክትባት ከ65 ዓመት በላይ ለሆኑ ሰዎች 94 በመቶ ይሠራል አለ

የኮሮናቫይረስ ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኮሮናቫይረስን የሚከላከል ክትባት እየሠራ ያለው ፋይዘር የተሰኘው ኩባንያ አዲሱ ክትባት ዕድሜያቸው ከ65 ዓመት ላሉ 94 በመቶ እንደሚሠራ አስታወቀ።

ፋይዘርና ባዮቴክ ያበለፀጉት አዲሱ የኮሮናቫይረስ ክትባት ሶስተኛ ደረጃ ሙከራ ላይ የደረሰ ሲሆን ክትባቱ ለሁሉም ዕድሜ፣ ዘርና ጎሳ እኩል እንደሚሠራ ተነግሯል።

አምራቾቹ ኩባንያዎች ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ክትባቱን ለማከፋፈል ከአሜሪካ ባለሥልጣናት ፈቃድ እንደሚጠይቁ አስታውቀዋል።

ክትባቱ በዓለም ዙሪያ ባሉ 41 ሺህ ሰዎች ላይ የተሞከረ ሲሆን በሁለት ደረጃ ነው የተሰጣቸው ተብሏል።

ባለፈው ሳምንት ፋይዘር እና ባዮንቴክ የመጀመሪያ ዙር ጥናታናቸውን ውጤት ይፋ አድርገው ክትባቱ 90 በመቶ የተሳካ እንደሆነ አሳውቀው ነበር።

የክትባቱ ደህንነትም አስተማማኝ እንደሆነ ድርጅቶቹ ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ አሳውቀዋል።

በሌላ በኩል የአሜሪካ ሞደርና የመድኃኒት አምራች ኩባንያ ክትባት አምርቶ አስተማማኝነቱ 95 በመቶ ነው ሲል ከቀናት በፊት አሳውቆ ነበር።

ዛሬ [ረቡዕ] ፋይዘርና ባዮንቴክ የለቀቁት መረጃ አዲሱ ክትባት 95 በመቶ የተዋጣለት እንደሆነ በ170 በጎ ፈቃደኞች ላይ ተሞክሯል ይላል።

ከ170 ሰዎች መካከል ለ8 ሰዎች ነው ክትባቱ እንዲሰጥ የተደረገው።

ኩባንያዎቹ ክትባቱ እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት እንደሌለው አረጋግጠናል ይላሉ። ነገር ግን 2 በመቶ የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ላይ ራስ ምታትና ድካም ተስተውሏል ብለዋል።

ከበጎ ፈቃደኞች መካከል 42 በመቶዎቹ ከተለያዩ ሃገራትና ጎሳዎች ሲሆኑ 41 በመቶዎቹ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ56 እስከ 85 የሚደርስ ነው።

የክትባቱ ሙከራ አሁንም የቀጠለ ሲሆን ለሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የክትባቱን ደህንነትና ብቃት መከታተል እንደሚቀጥሉ አሳውቀዋል።

ክትባቱ አሜሪካ፣ ጀርመን፣ ቱርክ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ብራዚልና አርጀንቲና በሚገኙ 150 ጣቢያዎች እየተሞከረ ይገኛል።

ኩባንያዎቹ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት 50 ሚሊዮን በቀጣዩ ዓመት ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ክትባቶች ለማምረት እንደተዘጋጁ አሳውቀዋል።