ኮቪድ-19 የለዋወጠው የዓለም ውድ ከተሞች ዝርዝር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኮሮናቫይረስ አጠቃላዩን የዓለም ሁኔታ በመቀየር የምድራችን ውድ ከተሞች ዝርዝር ላይም ለውጥ አምጥቷል።
አዲስ በወጣ ሪፖርት መሠረት የወቅቱ የዓለም ውድ ከተሞች ሆንግ ኮንግ፣ ዙሪክ እና ፓሪስ ሆነዋል።
አምና ከሆንግ ኮንግ ጋር ተመሳሳይ ደረጃ ላይ የነበሩት ሲንጋፖር እና ኦሳካ ከዝርዝሩ ወርደዋል።
'ዘ ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት' የተባለው ተቋም ነው ይህንን ዓመታዊ የከተሞች የኑሮ ሁኔታ የደረጃ ሰንጠረዥ ያወጣው።
የተቋሙ ኃላፊ ኡፓሳና ደት እንዳሉት፤ ለወትሮው በሰንጠረዡ የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዙት የእስያ አገሮች በኮቪድ-19 ሳቢያ ወደ ታች ወርደዋል።
በቻይና እና አሜሪካ መካከል ያለው ፍጥጫ መካረሩን ተከትሎ ብዙ የቻይና ከተሞች በዝርዝሩ ቀዳሚ ከሆኑት መካከል ተመዝግበዋል።
የቻይና እና የአሜሪካ የቴክኖሎጂ ተቋሞች ፉክክር የተለያዩ ቁሳቁሶች ዋጋ እንዲንር ምንክንያትም ሆኗል።
ባንኮክ በዝርዝሩ 20 ደረጃ ዝቅ ብላ፤ 46ኛ ውድ ከተማ ሆናለች።
የተቋሙ ጥናት ያተኮረው ወደተለያዩ አገሮች ተጉዘው በድጋሚ ወደ ትውልድ አገራቸው የተመለሱ ሰዎች ላይ ነው።
ይህንን የጥናት ውጤት የጉዞ እቅድ የሚያወጡ ሰዎች ወይም ድርጅቶች ይጠቀሙበታል።
በአሜሪካ፣ አፍሪካ እና ምሥራቅ አውሮፓ ከተሞች ኑሮ ከአምና ዘንድሮ ረክሷል። በተቃራኒው በምዕራብ አውሮፓ አገሮች ንረት አሳይቷል።
ከአስሩ ውድ ከተሞች አራቱ ምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ይገኛሉ።
ዙሪክ እና ፓሪስ በመጀመሪያ ደረጃ ሲቀመጡ፤ ጄኔቫ እና ኮፐንሀገን ሰባተኛ እና ዘጠነኛ ሆነዋል።
ይህ የአውሮፓ ገንዘብ በአንጻራዊንት ጠንካራ እንደሆነ ይጠቁማል።
በከተሞች መካከል የኑሮ ውድነት ውድድር ሲካሄድ ማነጻጸሪያው ኒው ዮርክ ናት።
በከፍተኛ ደረጃ ለውጥ የታየው በኢራን መዲና ቴህራን ነው። ካለፈው ጊዜ 27 ደረጃ ከፍ ብላለች። የኑሮ ውድነት ያስከተለው አሜሪካ የጣለችው ማዕቀብ ነው።
ተቋሙ ጥናቱን ሲሠራ መስከረም ላይ በ130 ከተሞች የነበረውን የ138 ቁሳቁሶችን ዋጋ አወዳድሯል።
ጠቅለል ባለ ሁኔታ ሲታይ፤ ዋጋ የቀነሰ ቢሆንም እጅግ አስፈላጊ መገልገያዎች ተወደዋል።
በወረርሽኙ ምክንያት በረራና ሌላም እንቅስቃሴ መገታቱ ለዋጋ ንረት ምክንያት ሆኗል።
ዋጋቸው በጣም ከተወደደ ምርቶች መካከል ሲጋራ ይጠቀሳል። የኮምፒውተር ዋጋም ንሯል። በሌላ በኩል ልብስ ረክሷል።












