ፓኪስታን ፡ በካርቱን ስዕል ምክንያት የፈረንሣይ ምርቶችን መጠቀም ልታቆም ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
አንድ የፓኪስታን እስላማዊ ቡድን የጠራውን የፀረ-ፈረንሳይ ተቃውሞን የፓኪስታን መንግሥት የፈረንሳይ ምርቶችን ላለመጠቀም በመወሰኑ ማቋረጡን አሳወቀ።
ሰልፎቹ የተጠሩት ፈረንሳይ የነቢዩ ሙሐመድን ካርቱን የማሳየት መብትን በመደገፏ ነበር።
አንድ መምህር በክፍል ውስጥ በነበረ ውይይት ወቅት የነቢዩ መሐመድን ካርቱን ካሳዩ በኋላ መገደላቸውን ተከትሎ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን አገራቸው በሐይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አትገባም ሲሉ በጥብቅ ተከላክለዋል።
ይህም በሙስሊሙ ዓለም ቁጣን ቀስቅሷል።
የአክራሪው ተህሪክ ኢ-ላባይክ ፓኪስታን (ቲ.ኤል.ፒ) የተሰኘው ቡድን አባላት የፈረንሳይን ምርት ላለመግዛት የቀረበውን ውሳኔ የደገፉ ቢያንስ የሁለት ሚኒስትሮችን ፊርማ ያካተተ የስምምነት ቅጅዎችን አሳይተዋል።
የፓኪስታን መንግስት በጉዳዩላይ በይፋ መግለጫ ካለመስጠቱም በላይ የፈረንሳይ ምርቶችን ያለመጠቀም አድማው እንዴት እንደሚተገበር አላሳወቀም።
በፈረንሣይ እስልምናን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት ማክሮንን ከተቹ የፖለቲካ መሪዎች መካከል የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን አንዱ ናቸው። ተቀዋሚዎቹ አሁንም ተጨማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል።
ደጋፊዎች ከእሁድ ጀምሮ ወደ መዲናዋ ኢስላማባድ የሚወስደውን ቁልፍ መንገድ በመዝጋታቸው ከፍተኛ የእንቅስቃሴ መስተጓጎል አስከትሏል። የቲ.ኤል.ፒ አመራሮች መንግሥት ለጥያቄዎቻቸው ምላሽ መስጠቱን ከተናገሩ በኋላ ተቃውሞው እንዲቋረጥ ተጠይቋል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ የሆኑት ኢጃዝ አሽራፊ ለሮይተርስ እንደተናገሩት "የፈረንሳይ ምርቶችን እንደማይጠቀም መንግሥት በይፋ እንደሚደግፍ ስምምነት ከፈረመ በኋላ የተቃውሞ ሰልፎቻችንን እያቆምንው ነው" ብለዋል።
ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ የተደረገው የስምምነት ሰነድ የሐይማኖታዊ ጉዳዮች ሚኒስትሩን እና የአገር ውስጥ ሚኒስትሩን ፊርማ ይዟል።
የፈረንሣይ አምባሳደር ከአገር እንዲወጡ በማድረግ ዙሪያ ላይ ፓርላማው እንዲወስን መንግሥት ሐሳብ እንደሚያቀርብም ገልጿል። የፓኪስታን መንግሥት በስምምነቱ ላይ የሰጠው አስተያየት የለም።
ቲ.ኤል.ፒ ቀደም ሲል ሐይማኖታዊ ስድብን ምክንያት በማድረግ ተቃውሞ ለማሰማት እጅግ ብዙ ሰዎችን በመሰብሰብ ይታወቃል። በፓኪስታን ሕግ መሠረት ነቢዩ ሙሐመድን በመሳደብ ጥፋተኛ የተባሉ ሰዎች የሞት ቅጣት ሊጣልባቸው ይችላል።
በፈረንሳይ የመንግሥት በሐይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ ያለመግባት የአገሪቱ ዋነኛ መገለጫ ነው።
በትምህርት ቤቶች እና በሌሎች ሕዝባዊ ቦታዎች ሀሳብን በነፃነት መግለጽም የዚህ አካል ሲሆን የአንድን የተወሰነ ሐይማኖት ስሜት ለመጠበቅ የሃሳብ ነጻነቱን መግታት ብሔራዊ መገለጫውን እንደሚያደፈርስ ተደርጎ ይወሰዳል።
'ቻርሊ ሄብዶ' የተሰኘው መጽሔት የነቢዩ ሙሐመድ ካርቱን ይዞ መውጣቱን ተከትሎ እ.አ.አ በ2015 በፓሪስ ውስጥ የጥቃት ዒላማ ቢሆንም የካቶሊክን እና የአይሁድን እምነት ጨምሮ ሌሎች ሐይማኖቶችም የሚያመለክቱ ስዕሎችን ይዞ ወጥቷል።
የፈረንሣይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቀደም ሲል በበርካታ ሙስሊሞች በብዛት በሚገኙባቸው አገሮች ውስጥ የፈረንሳይ ሸቀጦችን ላለመጠቀም የሚደረጉ ጥሪዎችን "መሠረተ ቢስ" ብለው "በአፋጣኝ መቆም" እንዳለባቸውም ገልጸው ነበር።
ባለፈው ወር ለተገደሉት መምህር ክብር የሰጡት ፕሬዝዳንት ማክሮን ፈረንሳይ "ካርቱኑን አታቆምም" ብለዋል።














