ፈረንሳይ የሟቹን መምህር ግድያ አበረታቷል ያለችውን መስጊድ ዘጋች

መስጅድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፈረንሳይ መንግሥት አንድ መስጊድ እንዲዘጋ አደረገ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የታሪክ መምህሩ ሳሙኤል ፓቲ በአሰቃቂ ሁኔታ መገደሉን ነው፡፡

ይህ መስጊድ እንዲዘጋ የተደረገው በዋናነት የመስጊዱ ኃላፊዎች ሟቹ መምህር ሳሙኤል ፓቲ የነብዩ መሐመድን ካርቱን ምሥል ለተማሪዎቹ ካሳየ በኋላ ይህን ድርጊቱን የሚያወግዝ መልእክት በማሰራጨታቸው ነው፡፡

የዚህ መስጊድ ኃላፊዎች በመስጊዱ የፌስቡክ ገጽ ሟች ሳሙኤል ፓቲ ላይ እርምጃ እንዲወሰድበት የሚያበረታታ ይዘት ያለው ጽሑፍና መምህሩ የሚያስተምርበትን አድራሻ አጋርተው ነበር፡፡

መስጊዱ ለድርጊቱ ጸጸት እንደተሰማውና ይቅርታ እንደጠየቀም ተዘግቧል፡፡

ዘ ፓንቲን ተብሎ የሚጠራው መስጊድ የሚገኘው በሰሜን ፓሪስ ሲሆን ለሚቀጥሉት 6 ወራት ለምዕመናን ክፍት እንደማይደረግ የአገር ውስጥ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡

የመስጊዱ ኃላፊዎች አጋሩት የተባለው የፌስቡክ መልእክት የመምህሩን ግድያ ተከትሎ ወዲያውኑ ተሰርዟል፡፡

ባሳለፍነው አርብ ትምህርት ቤት አቅራቢያ አንገቱን ተቀልቶ የተገደለው መምህር ሳሙኤል ፓቲ እጅግ ተወዳጅ መምህር እንደነበር ይነገራል፡፡

ለተማሪዎቹ የነብዩ መሐመድን ካርቱን ምሥል በማሳየት ስለ ፕሬስ ነጻነት ለማስተማር ከሞከረ በኋላ ነበር ይህ ጥቃት የደረሰበት፡፡

የሱን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደል ተከትሎ በፈረንሳይ ከፍተኛ ቁጣ የተቀሰቀሰ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ድርጊቱን ለማውገዝ እሑድ አደባባይ መውጣታቸው ይታወሳል፡፡

እንዲዘጋ የተወሰነበት መስጊድ 1ሺ500 ምዕመናን እየተገኙ የሚያመልኩበት ሥፍራ የነበረ ሲሆን በከተማዋ እምብርት ላይ የሚገኝ ነው፡፡

የ18 ዓመቱ ጥቃት አድራሽ ፈረንሳዊ ስሙ አብዱላሂ ሲሆን ትውልዱ ከሩሲያ ግዛት ቺቺንያ ይመዘዛል፡፡

ይህ ወጣት መምህሩን በአሰቃቂ ሁኔታ ከገደለ በኋላ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በነበረ የተኩስ ልውውጥ ወዲያውኑ ተገድሏል፡፡

ይህን አሰቃቂ ድርጊት ተከትሎ የፈረንሳይ መንግሥት ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በሙስሊም ዜጎች ላይ ከፍተኛ ክትትልና ምርመራ እያደረገች ነው፡፡ አክራሪ የሆነ አተያይ ያላቸው አማኞችና የሪፐብሊኩን ነጻ አስተሳሰብ የሚቃረኑ ቡድኖችን እያደነችም ትገኛለች፡፡

እስካሁን በትንሹ 40 ቤቶች ላይ አሰሳ ተደርጓል፡፡

51 የሚሆኑ ኢስላማዊ ማኅበራትና ድርጅቶች፣ እንዲሁም ግብረሰናይ ተግባር የሚሰሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ኢስላማዊ ተቋማት ተዘግተው ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡

ግድያውን ተከትሎም 15 ፈረንሳዊያን በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የገዳዩ አያትና ቤተሰቦች እንዲሁም ታናሽ ወንድሙ ይገኙበታል፡፡

ገለልተኛ ወገኖች በጥቃት ፈጻሚው ላይ ባለፉት ቀናት ይታዩ የነበሩ እንግዳ ባህሪዎችን ተከትሎ ለፈረንሳይ መንግሥት ቅድመ ጥቆማ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ምንም እርምጃ አለመውሰዱን ክፉኛ እየተቹት ይገኛሉ፡፡