ኮሮናቫይረስ፡ በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ከሚያዙት መካከል 63 በመቶው ምልክት አያሳዩም

የፎቶው ባለመብት, Anadolu Agency
በአሁኑ ወቅት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተይዘው የሚገኙ ሰዎች ውስጥ 63 በመቶው ምልክት የማያሳዩ እንደሆኑ ተገለፀ።
ዛሬ የጤና ሚኒስቴርና ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ በሰጡት መግለጫ ላይ እንደተገለፀው አሁን ላይ አዲስ አበባ በስርጭቱ ቀዳሚ ሰትሆን፣ ኦሮሚያና ትግራይ ክልሎች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው ከሐምሌ እና ነሐሴ በላይ አሁን ላይ ወደ ፅኑ ሕሙማን የሚገቡ ታማሚዎች ብዛት እየጨመረ መጥቷል።
በመግለጫው ላይ በኢትዮጵያ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት ለማወቅ በሀገር አቀፍ ደረጃ በተካሄደ የአንድ ወር አገር አቀፍ የምርመራ ዘመቻ ከ73 በመቶ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መለየታቸው ተገልጿል።
1.4 በመቶ የሚሆኑት በሆስፒታል የሚገኙ ታማሚዎች በፅኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ እንደሚገኙም ተመልክቷል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዳይሬክተር አስቻለው አባይነህ እንዳሉት በኢትዮጵያ ሁሉም ወረዳዎች ቢያንስ አንድ በኮቪድ የተያዘ ሰው ሪፖርት አድርገዋል።
በዚሁ መግለጫ ላይ እስካሁን በኢትዮጵያ በቫይረሱ ከሚያዙት 57 በመቶ የሚሆኑት እድሜያቸው ከ15-34 ሲሆን ከሟቾች ውስጥ ደግሞ 51.9 በመቶ የሚሆኑት ዕድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ መሆኑን ተገልጿል።
ምክትል ዳይሬክተሩ አክለው እንደገለፁት በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተይዘው ለህልፈት የሚበቁ ሰዎች ምጣኔ 1.52 በመቶ ነው።
አሁን ላይ የምርመራ መጠን የቀነሰ ቢሆንም ቫይረሱ የሚገኝባቸው እና ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑም ተመልክቷል።
ባለፉት ሁለት ሳምንት ውስጥ እንደአገር ያለው የቫይረሱ ስርጭት 10 ነጥብ 4 በመቶ መሆኑም ተገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማ፣ ኦሮሚያ ፣ ትግራይ ፣ አማራ ፣ ደቡብ እና ሲዳማ ክልሎች በቅደም ተከተል ከፍተኛ የቫይረሱ ተጠቂዎች የተገኙባቸው ስለመሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
የጤና ሚኒስትርዋ ዶ/ር ሊያ በበኩላቸው ርቀትን ሳይጠብቁና ማስክ ሳያደርጉ አገልግሎት መቀበልም ሆነ መስጠት ለቫይረሱ ተጋላጭነትን ስለሚጨምር ህብረተሰቡ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል።
ቸልተኝነት እና መዘናጋት አሁንም በሰፊው እንደሚስተዋል በመግለጽ ይህ ዋጋ ስለሚያስከፍል ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል በቫይረሱ ሊያዝ ስለሚችል ጤናውን ከመጠበቅ ሊዘናጋ እንደማይገባም ነው ሚኒስትሯ ያስጠነቀቁት።
በቫይረሱ የሞት ምጣኔ በኢትዮጵያ 1.52 በመቶ ፣ በአፍሪካ 2.4 በመቶ ፣ በዓለም ደግሞ 2.8 በመቶ መሆኑንም በመግለጫው ወቅት ተገልጿል።
በአጠቃላይ በኢትኦጵያ 89 ሺህ 860 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ሲረጋገጥ፤ የ1,365 ሰዎች ህይወት አልፏል ፤ 43,149 ከበሽታው አገግመዋል።














