ቻይናውያን የኮቪድ -19 ክትባት ተሰልፈው መውሰድ ጀመሩ

በምስራቅ ቻይና ዜሄንጂን ግዛት ውስጥ በምትገኘው ዪዉ ከተማ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቻይናውያን የኮሮናቫይረስ ክትባት ለመከተብ ከንጋት ጀምሮ ተሰልፈው ታይተዋል።
በቻይና መንግሥት ሲበለጽግ የነበረው ይህ የኮሮናቫይረስ ክትባት የመጨረሻው የክሊኒካል ሙከራ ላይ ይገኛል እንጂ ሙሉ ክሊኒካል ሙከራዎችን አላጠናቀቀም። ለህዝብ ጥቅም ላይ እንዲውልም ገና ፍቃድ አላገኘም።
በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ ሮቢን ብራንት ማንኛውም ገንዘብ ያለው ሰው የተጠየቀውን ከፍሎ እና ተሰልፎ ክትባቱን ሲወስድ ተመልክቻለሁ ብሏል።
ክትባቱ 60 የአሜሪካ ዶላር ወይም 2200 ብር ገደማ ይከፈልበታል።
"ንጋት 1 ሰዓት ላይ ሆስፒታሉ ከመከፈቱ በፊት በርካቶች ክትባቱን ለማግኘት ተሰልፈው ነበር። መኪናቸውን እያሽከረከሩ፣ በታክሲ እና በእግራቸው የሚመጡ በርካታ ሰዎችን ተመልክቻለሁ" ይላል ሮቢን።
የተጠየቀችውን ገንዘብ ከፍላ ክትባቱን ለመከተብ ተሰልፋ የነበረች አንዲት ሴትን አነጋግሪያት ነበር ይላል ሮቢን።
"ክትባቱ ክሊኒካል ሙከራዎችን አላለፈም። ደህንነቱ አልተረጋገጠም። ክትባቱን መውሰድ አላሳሰበሽም ወይ? ስል ጠየኳት። 'ዶክተሮቹን አምናችዋለሁ። ክትባቱንም አምናለሁ' ስትል መለሰችልኝ" ይላል።
የቻይና መንግሥት ክትባቱ ለህዝብ የቀረበው የክሊኒካል ሙከራ አካል ሆኖ አይደለም ብሏል። የሚጠየቀውን ገንዘብ መክፈል የሚችል እና ፍላጎት ያለው ክትባቱን መውሰድ ይችላል ብሏል።
ኮሮናቫይረስ ከ10 ወራት ገደማ በፊት በቻይናዋ ዉሃን ከተማ በቅድሚያ ሪፖርት መደረጉ ይታወሳል።
ቻይና ከሌሎች አገራት በተሻለ መልኩ የቫይረሱን ስርጭት መቆጣጠር ችላለች። ይሁን አንጂ በቫይረሱ ምክንያት በመላው ዓለም ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ1.1 ሚሊዮን ተሻግሯል።












