ትራምፕ ዳግም ምርጫውን ሊያሸንፉ የሚችሉባቸው ምክንያቶች

ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ንግግር ሲያደርጉ

ከምርጫ በፊት የሚከናወኑ አስተያየት መሰብሰቢያዎች የትራምፕ ተቀናቃኝ ጆ ባይደን ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ናቸው።

ከምርጫ በፊት የምርጫ ውጤቶችን የሚተነብዩ ተቋማት ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ምርጫን የማሸነፍ እድል ከ83.5 % እስከ 87% ያደርሱታል።

ጥቅምት 24 በሚካሄደው ምርጫ ባይደን የማሸነፋቸው ነገር የማይቀር ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የቢቢሲ የሰሜን አሜሪካ ፖለቲካ ተንታኙ አንቶኒ ዙራከር ግን ታሪክ እራሱን ከደገመ እውነታው ሌላ ሊሆን ይችላል ይላል። ትራምፕ ሳይጠበቁ ምርጫውን ሊያሸንፉ ይችላሉ። የዛሬ አራት ዓመት የሆነውም ይህ ነው ይላል አንቶኒ።

ልክ የዛሬ 4 ዓመት ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ሳምንታት ብቻ በቀሩበት ወቅት የወቅቱ የትራምፕ ተቀናቃኝ ሂላሪ ክሊንተን ትራምፕን እንደሚረቱ ቅድመ ግምቶች ነበሩ። የኋላ ኋላ ነገሮች ተቀያይረው ትራምፕ ምርጫውን አሸንፈዋል።

ትራምፕ ቃለ መሃላ ፈጽመው አሜሪካንን ለተጨማሪ 4 ዓመታት እንዲመሩ ህዝቡ ከፈቀደ ለዚህ ምክንያቶቹ የሚከተሉት ናቸው።

በምርጫ ዋዜማ ያልተጠበቀው ሲከሰት

የዛሬ አራት ዓመት ለምርጫው 11 ቀናት ብቻ ሲቀሩ ሂላሪ ክሊንተን የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ሳሉ የግል ኢሜል ሰርቨርን በመጠም የሥራ ኢሜይል ልውውጥ ስለማድረጋቸው ዳግም ምርመራ በኤፍቢአይ ይጀምራል ተባለ።

የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚይ በሂላሪ ላይ ምርመራ መከፈቱ ለትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ኃይል ሆኖ ነበር።

የዘንድሮ ምርጫ ከመከናወኑ በፊትም ተመሳሳይ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ለትራምፕ የድል በር ሊከፍት ይችላል።

እስካሁን ግን የተከሰቱት ነገሮች ትራምፕን ነጥብ የሚያስጥሉ እንጂ ወደ ዋይት ሃውስ የሚያስገቡ ሆነው አልተገኙም።

ለምሳሌ ኒው ዮርክ ታይምስ ትራምፕ የከፈሉትን የገቢ ግብር መጠን ይፋ ማድረጉ እና በኮቪድ 19 የተሳለቁት ፕሬዝደንት በኮቪድ 19 ምክንያት ሆስፒታል መግባታቸው ለምርጫ ቅስቀሳቸው ውድቀት ነው።

ሃንተር ባይደን እና ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሃንተር ባይደን እና ጆ ባይደን

እአአ 2014-2019 የጆባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን በዩክሬን የሚገኝ አንድ ነዳጅ አውጪ ኩባንያ ቦርድ አባል ሆኖ ሰርቷል።

በወቅቱ ባይደን ደግሞ በፕሬዝደንት ኦባማ አስተዳደር ውስጥ ምክትል ፕሬዝደንት ነበሩ። አባት እና ልጅ አንድ ወቀሳ ይቀርብባቸዋል።

ሃንተር በቦርድ አባልነት የሚያገለግልበት ኩባንያ በዩክሬን መንግሥት የጸረ-ሙስና ምርመራ እንዳይደረግበት ባይደን ስልጣናቸውን ተገን በማድረግ ጫና አሳድረዋል የሚል።

ባይደን ምክትል ፕሬዝደንት ሳሉ ይህን ስለመፈጸማቸው ቢረጋገጥ ታሪክ ቀያሪ ክስተት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።

Link box banner bottom

የቅድመ ምርጫ ግምቶች ስህተት

ሪፐብሊካን ፓርቲን ወክለው ከዴሞክራቱ ጆ ባይደን ጋር አንገት ለአንገት የተናነቁት ፕሬዝደንት ትራምፕ ቁርጣቸውን የሚያውቁት ጥቅምት 24/2013 ነው።

ይሁን እንጂ የአሜሪካ የምርጫ ትንቅንቅ የምርጫ ዕለት ብቻ የሚታይ አይደለም። የቅድመ ምርጫ ምርጫም አለው።

ድምፅ ሰብሳቢ ድርጅቶች የትኛውን ዕጩ ነው የምትመርጡት እያሉ ከአሜሪካውያን የሚሰበስቡትን ድምፅ ይፋ የሚያደርጉበት ነው ቅድመ ምርጫ ማለት።

መግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው በዚህ ቅድመ ምርጫ ጆ ባይደን የማሸነፍ ሰፈ እድል ተሰጥቷቸዋል።

2016 የነበሩት ቅድመ ምርጫ ውጤቶች ግን የምርጫ ውጤት ተገላቢጦሽ ሆነው ነበር የተገኙት። የቅድመ ምርጫ ውጤቶች ሂላሪ እንደሚያሸንፉ ቢያመላክቱም የመጨረሻው ውጤት ግን ድሉን ለትራምፕ አሳልፎ ሰጥቷል።

ቅድመ ምርጫ ውጤቶች ረብ የለሽ እና አሳሳች ሊሆኑ ይችላሉ ይላል የፖለቲካ ተንታኙ አንቶኒ ዙራከር። በ2016 የሆነውም ይሄው ነው።

ምርጫውን ማን ሊያሸንፍ ይችላል ሲባል 'ማን ወጥቶ ድምጹን ሊሰጥ ይችላል?' የሚለውን መገመት ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሁሌም ፈታኝ ነው ይላል።

በኮሮናቫይረስ ስጋት ዘንድሮ መራጮች ድምጽ የሚሰጡት በፖስታ ቤት አማካኝነት ነው። ድምጽ ሰጪዎች የምርጫ ቅጾችን እና የፖስታ አድራሻ በትክክል መሙላት ካልቻሉ ድምጻቸው አይቆጠርም።

Link box banner bottom

ማርሽ ቀያሪ ፕሬዝደንታዊ የፊት ለፊት ክርክሮች

ትራምፕ እና ባይደን ከሳምንታት በፊት ፊት ለፊት በተገናኙ ጊዜ ነጥብ የጣሉት ፕሬዝደንት ትራምፕ ነበሩ።

ቁጡነታቸው፣ ባይደንን እና ጋዜጠኛውን በተደጋጋሚ ማቋረጣቸው በበካታ ድምጽ ሰጪዎች ዘንድ አልተወደደላቸውም።

ትራምፕ ይህን ለመቀየር አንድ እድል አላቸው። በቀጣይ በሚኖራቸው ክርክር ላይ እርግት ብለው የተሻለ ነጥብ የሚያስመዘግቡ ከሆነ የምርጫውን ውጤቱን አቅጣጫ የማስቀየር እድል ይኖራቸዋል ይላል አንቶኒ።

ወሳኝ ግዛቶች ላይ ድምጽ ማግኘት

በዚህ ምርጫ ላይ የበላይነትን በመያዝ ለማሸነፍ ቁልፍ በሚባሉት ግዛቶች ላይ በልጦ መግኘት ያስፈልጋል።

ትራምፕ እንደ ሚቺጋ እና ዊስኮንሲን ያሉ ቁልፍ ግዛቶች ላይ ማሸነፍ የሚችሉ አይምሰሉም።

ይሁን እንጂ እንደ ፔንስያለቫኒያ እና ፍሎሪዳ ያሉ ግዛቶች ላይ የሚያሸንፉ ከሆነ ቀጣይ አራት ዓመታትን በዋይት ሃውስ መሰንበታቸውን ሊያረጋግጡ ይችላሉ።