የአሜሪካ ምርጫ ፡ በመጀመሪያው የዶናልድ ትራምፕ እና የጆ ባይደን ክርክር ማን የበላይ ሆነ?

ትራምፕ እና በይደን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ትራምፕና ባይደን በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ለ90 ደቂቃ ተናንቀዋል። በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ።

ክርክሩ እንደተፈራው ነበር የሆነው። ትራምፕ ባይደንን ብቻ ሳይሆን የክርክሩን አጋፋሪ እያቋረጡ መናገር፣ እኔን ብቻ ስሙኝ ማለት አብዝተው ነበር።

እምብዛምም የይዘት ከፍታ አልነበረውም። መዝናኛነቱ ያይላል ቢባል ይቀላል።

Section divider

ትራምፕና ባይደን የተከራከሩባቸው አበይት ነጥቦች በጤና መድኅን፣ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሹመት፣ በኮሮና ተህዋሲ፣ የአሜሪካ ምጣኔ ሀብት፣ ዘረኝነትና የምርጫ ሂደትና የምርጫ ገለልተኝነት ነበሩ።

ትራምፕ ባይደንን የክፍልህ ሰነፉ ተማሪ ነበርክ፣ አሳፋሪ ነህ ሲሉ፤ ባይደን በበኩላቸው አሜሪካ እንዳንተ የከንቱ ከንቱ መሪ አይታ አታውቅም ሲሉ መልሰዋል።

ባይደን ትራምፕን ‹ቀጣፊ› ብለዋቸዋል። ወደ ካሜራው በቀጥታ በመዞርም ‹ይህ ሰውዬ የሚላችሁን ታምኑታላችሁን?› ሲሉ የአሜሪካን ሕዝብ ጠይቀዋል።

ይህ ክርክር ከመካሄዱ በፊት ብዙዎች ትራምፕ ጆ ባይደንን በነገር እየሸነቆጡ ንግግር ይነሷቸው ይሆናል ሲሉ ሰግተው ነበር።

ባይደን ትንሽ ዘገም የማለት ሁኔታ ስላለባቸውና ትራምፕ ግልብ ቃላትን፣ ግልብ ሀሳብን፣ መደዴ የክርክር ነጥቦችን አዘውትረው ስለሚጠቀሙ ሰውየውን አያናግሯቸው ይሆናል ሲባል ነበር።

ባይደን ግን እንደተፈራው ያን ያህል ችግር ውስጥ አልገቡም። አልፎ አልፎ ቃላት አልታዘዝ ሲሏቸው ቢታይም በርካታ ቁምነገር አንስተዋል።

በኮሮናቫይረስ ዙርያ ባደረጉት ክርክር ሁለቱም አንዱ ሌላውን ሲከስ ተስተውሏል።

ትራምፕ ‹‹እንኳንም እኔ ፕሬዝዳንት ሆንኩኝ እንጂ ባይደን በዚህ ጊዜ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ቢሆን ኖሮ አሜሪካዊያን ሞተው ያልቁ ነበር፣ ሚሊዮኖች ይሞቱ ነበር›› የሚል ይዘት ያለው ሐሳብ ሲያሰሙ፣ ባይደን ወደ ካሜራው በቀጥታ በማየት በበሽታው የሞቱባቸውን አሜሪካዊያንን ልብ ለማሸነፍ ‹‹ስንቶቻችሁ በዚህ ሰዓት ሐዘን ላይ እንዳላችሁ ይገባኛል፣ ስንቶቻችሁ አባታችሁን፣ እናታችሁን፣ እህታችሁን…እንዳጣችሁ ይሰማኛል›› እያሉ የብዙ አሜሪካዊያንን አንጀት ለመብላት ሞክረዋል።

የክርክሩ መሪ የፎክስ ኒውሱ ክሪስ ዋለስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የክርክሩ መሪ የፎክስ ኒውሱ ክሪስ ዋለስ

ክርክሩ ገና ከመጀመሩ ትራምፕ ባይደንን ‹‹ፈዛዛ ነህ›› ሲሏቸው ባይደን ትራምፕን ‹‹አሻንጉሊት ነህ፣ መሳቅያ መሳለቅያ ነህ›› ብለዋቸዋል።

ጆ ባይደን የትራምፕ ጣልቃ ገብነት ከመጠን በላይ በሆነባቸው ቅጽበትም፣ ‹‹አንተ ሰውዬ፣ እባክህን አፍህን ዝጋ›› ብለዋቸው ነበር።

የክርክሩ አጋፋሪ የፎክስ ኒውሱ ክሪስ ዋለስ ትራምፕን ለመግራት የተቻለውን ሞክሯል። ሆኖም ትራምፕ በጄ አላሉም።

እንኳን ባይደን ሲናገር ይቅርና የአከራካሪውን ክሪስ ዋለስንም ሐሳብ የሚያስጨርሱ አልሆኑም። ማይክራፎኑን ሊያሳርፉት አልቻሉም።

ኮሮናቫይረስ

አንድ ቦታ ላይ እንዲያውም የክርክሩ አጋፋሪ ክሪስ ዋለስ እንዲህ አለ፤ ‹‹ለሚቀጥሉት ሁለት ተኩል ደቂቃዎች ሁለታችሁም የምታወሩት ስለ ኮሮና ብቻ ይሆናል። ማንም ማንንም ማቋረጥ አይችልም››

ባይደን በዚህ ጊዜ ወደ ክሪስ ዋላስ ዞረው እንዲህ ሲሉ ቀለዱ።

‹‹ይቅናህ ወንድሜ!››

እንደቀደለዱትም ትራምፕ ገና ከመጀመሩ ክርክሩን ማቋረጥ ቀጠሉ። ይህም ሳቅን ያጫረ ክስተት ነበር።

ትራምፕ '200ሺህ አሜሪካዊያ መሞታቸው እኔ በመሆኔ ነው ባይደን ፕሬዝዳንት ቢሆን አሜሪካዊያን ያልቁ ነበር። ይሄ ቻይና የላከችብን በሽታ ነው። እኔ ግን ቶሎ ብዬ ድንበር በመዝጋቴ ሟቾቹ ትንሽ ሊሆኑ ችለዋል። ዶ/ር ፋውቺ አድንቆኛል። መስክሮልኛል። በጊዜ ድንበር በመዝጋቴ ነው አሜሪካዊያንን የታደኩት' የሚል ሁልጊዜም በጋዜጣዊ መግለጫ የሚሉትን በክርክሩም አንስተዋል።

በዚህ ጊዜ ነበር ባይደን ወደ ትራምፕ ወይም ወደ ዋላስ መዞር ትተው በቀጥታ ወደ ካሜራ በማየት ‹ይህን ሰውዬ የሚለውን ታምኑታላችሁ ብለው የጠየቁት። ይህን የምሽቱ የባይደን ስኬታማ ደቂቃ ተደርጎ ተወስዷል።

ትራምፕ የነጭ አክራሪዎችን፣ የጥቁር ጠሎችን እንዲያወግዙ በክርክር መሪው ዋለስም ሆነ በባይደን ቢጠየቁም ይህን ሊያደርጉ አልደፈሩም።

ትራምፕ ባይደንን ከፍና ዝቅ ባደረጉበት በዚህ የክርክር ጊዜ ይህንን ብለዋል። ‹‹ለ47 ዓመት በአሜሪካ ፖለቲካና አስተዳደር ቆይተሃል፣ ምንም ያሳካሀው ነገር የለም። አንተ በ47 ዓመት ያላሳከሀውን እኔ በ47 ወራት ሰርቼዋለሁ›› ብለዋል።

ባይደን ለዚህ ምላሽ የሰጡት ዘግየት ብለው ነው። ‹‹ባንተ ጊዜ አሜሪካ ድሀ፣ ደካማ፣ የተከፋፈለችና የታመመች ሆናለች›› ብለዋል።

Section divider

ባይደን ስለ ገቢ ግብር

ከሰሞኑ ኒው ዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ስለ ትራምፕ ያጋለጠው ምስጢር አስደንጋጭ ነበር። ትራምፕ ለዐሥር ዓመታት ግብር አለመክፈላቸው ዓለምን አነጋግሯል። ይህንን ጉዳይ ባይደን በማንሳት ተቀናቃኛቸውም በአሜሪካዊያን ዘንድ ያዋርዷቸዋል ተብሎ ተጠብቆ ነበር።

ርእሰ ጉዳዩ በክርክር አጋፋሪው ዋላስ ሲነሳ ትራምፕ ቶሎ ብለው የገቢ ግብር እንደሚከፍሉና ትንሽ ገንዘብ የመክፈላቸው ምስጢር ግን የግብር ሕጉ የሚሰጣቸውን እድል በብልሀት በመጠቀማቸው እንደሆነ ይህም ወንጀል እንዳልሆነ አብራርተዋል።

ባይደን እድሉ ሲሰጣቸው ትራምፕን በቀጥታ ከመቀጥቀጥ ይልቅ የሪፐብሊካን የታክስ ማሻሻያ ሐሳብ ላይ ተንከባለዋል።

ትራምፕ ከአንድ አስተማሪ በታች ነው ግብር የከፈሉት የሚል አረፍተ ነገር ከመናገራቸው ባሻገር ተቀናቃኛቸውን ብዙ ነጥብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን እድል አምክነዋል።

ክርክሩ የነገ ሳምንት በምክትሎቹ ማይክ ፔንስና ካመላ ሐሪስ መካከል ይቀጥላል።

የምርጫውን ውጤት በጸጋ መቀበል

በመጨረሻ ዋላስ ለሁለቱ እጩዎች ያቀረበላቸው ጥያቄ ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ደጋፊዎቻችሁ የምርጫውን ውጤት በጸጋ እንዲቀበሉ ትማጸናላችሁ ወይ? የሚል ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው አካሄድ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው፣ ሊጭበረበር ስለሚችል ደጋፊዎቻቸው ነቅተው እንዲጠብቁ፣ በየምርጫ ጣቢያው የሚሆነውን በቅርብ እንዲከታተሉ አደርጋለሁ ብለዋል።

ባይደን ቀበል አድርገው ‹‹ይሄ ሰውዬ የሚናገረውን አያውቅም›› ሲሉ ትራምፕን ተችተዋል።

ባይደን የምርጫውን ውጤት በጸጋ እንደሚቀበሉ አረጋግጠዋል። ካሸነፍኩ ፕሬዝዳንት የምሆነው ለዲሞክራቶች ብቻ አይደለም፣ ለአሜሪካውንያ በሙሉ እንጂ ሲሉም አክለዋል።