ዶናልድ ትራምፕ ግብር ያጭበረብሩ እንደነበረ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አጋለጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ ግብር ያጭበረብሩ እንደነበረ ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ አጋለጠ።
በፌዴራል የገቢ ግብር ሰነድ መሠረት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ የግብር ማጭበርበር ፈጽመዋል ይላል ይህ ዝነኛ ጋዜጣ፣ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ፡፡
ለምሳሌ እንደ አውሮጳዊያኑ በ2016 ትራምፕ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት በሚወዳደሩበት ጊዜ ማለት ነው፣ ከዚያም ዋይት ሐውስ ከገቡ በኋላ በነበረው የመጀመርያ ዓመት ሰውየው ለፌዴራል ገቢዎች የከፈሉት የገቢ ግብር 750 ዶላር ብቻ ነው፡፡
ጋዜጣው የዶናልድ ትራምፕን የ20 ዓመት ሒሳብ ደብተር እጄ ገብቷል ይላል፡፡
በዚህ መረጃ መሠረት ትራምፕ ላለፉት 10 ዓመታት አንዳችም የገቢ ግብር ከፍለው አያውቁም፡፡
ጋዜጣው አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት ትራምፕ በየዓመቱ የገቢ ግብር ላለመክፈል ኪሳራ ሪፖርት ያደርጋሉ፣ የተለያዩ የማጭበርበሪያ ዘዴዎችንም ይጠቀማሉ፡፡
ትራምፕ በሰጡት ምላሽ የኒው ዮርክ ታይምስን ዘገባ ‹‹ሐሰተኛ ዜና› ብለውታል፡፡ 'ፌክኒውስ!'
‹‹በእርግጥ ግብር ከፍያለሁ፡፡ በቅርቡ የግብር ደረሰኜን ስታዩ የምታረጋግጡት ይሆናል፡፡ አሁን ሂሳቤን የተመሰከረላቸው የሒሳብ አዋቂዎች ኦዲት እያደረጉት ነው፡፡›› ብለዋል ትራምፕ፡፡ ይህን ያሉት ኒው ዮርክ ታይምስ ዜናውን እሑድ ካሰራጨ በኋላ በሰጡት መግለጫ ነው፡፡
‹‹ድሮም ቢሆን የአገር ውስጥ ገቢዎች አገልግሎት ቢሮ (ኢንተርናል ሬቨኒው ሰርቪስ) በደንብ አያስተናግዱኝም፡፡ ያንገላቱኛል፡፡ ጥሩ መስተንግዶ ተደርጎልኝ አያውቅም›› ብለዋል ትራምፕ በዚህ መግለጫቸው፡፡
ቢሊየነሩ ትራምፕ የገቢ ደረሰኞቻቸውንና የግብር ሰነዶቻቸውን በመደበቅ ድሮም ቢሆን ይተቻሉ፡፡
ከ1970 ጀምሮ አንድም የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የግብርና ገቢ ደረሰኙን ለሕዝብ ይፋ ያላደረገ የለም፤ ከትራምፕ በስተቀር፡፡
ሆኖም አንድ ፕሬዝዳንት የገቢና ወጪ ሰነዱን ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ በሕግ አይገደድም፡፡
ኒው ዮርክ ታይምስ የትራምፕን የግብር መረጃ ያገኘሁት መረጃዉን በሕጋዊ መንገድ ማየት ከሚችል ግለሰብ ነው ብሏል፡፡
ይህ መረጃ ትራምፕ ከተቀናቃኛቸውና እሳቸው እንቅልፋሙ ባይደን ብለው ከሚሰድቧቸው ከእጩ ጆ ባይደን ጋር የቀጥታ የቴሌቪዥን ክርክር ለማድረግ በሚሰናዱበት ወቅት ነው፡፡
ትራምፕ ጥቅምት 24 በሚካሄደው ምርጫ ዋይት ሐውስ ለመቆየት ይፋለማሉ፡፡
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደሚለው ከሆነ ቢሊየነሩ ትራምፕ በ2016 እና በ2017 የከፈሉት የገቢ ግብር 750 ዶላር ብቻ ነው፡፡ ካለፉት 15 ዓመታት ውስጥ ደግሞ አስሩን ዓመት አንድ ብር እንኳ የትርፍ ግብር ገቢ አልከፈሉም፡፡
የገቢ ግብር የማይከፍሉት ደግሞ ኪሳራ ውስጥ ነኝ በሚል ነው፡፡ አላተረፍኩም በኪሳራ ነው የምንቀሳቀሰው የሚሉት ግብር ለመደበቅ ነው ይላል ሪፖርቱ፡፡
ከገቢ ይልቅ ወጪ ያለበት ኩባንያ የገቢ ግብር ለመክፈል ስለማይገደድ ይህንኑ ዘዴ ግብር ለመደበቅ አውለውታል ሲል ይከሳል ጋዜጣው፡፡
ትራምፕ ፕሬዝዳንት ከመሆናቸው በፊት እውቅ የቢዝነስ ሰው ነበሩ፡፡ ጋዜጣው እንደሚለው ግብር ላለመክፈል ወጪያቸውን ለማብዛት አላስፈላጊ ቅጥር ያደርጉ ነበር፡፡
ትራምፕ ከዚህ በፊት በአንድ ንግግራቸው በ2018 ብቻ $434.9 ሚሊዮን ዶላር ማትረፋቸውን ተናግረው ነበር፡፡
ጋዜጣው ግን የገቢ ግብር ሰነዱን አገላብጦ እንዳስነበበው በዚህ ዓመት ትራምፕ ለገቢዎች ሚኒስቴር ያስገቡት ሰነድ መክሰራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ ኪሳራውም $47.4 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡
የትራምፕ ኩባንያ አለቃ የኒው ዮርክ ዘገባ ባመዛኙ ሐሰት ነው ብለዋል፡፡ ትራምፕ የገቢ ግብር ይከፍሉ እንደነበረም አውስተዋል፡፡
ኒው ዮርክ ታይምስ እንደዘገበው የትራምፕ የጎልፍ መጫወቻ መዝናኛዎችና ሆቴሎቻቸው ከዓመት ዓመት ኪሳራ ላይ ነን እያሉ ሐሳዊ የሒሳብ መዝገብ ለገቢዎች ሚኒስቴር ያቀርቡ ነበር፡፡ ከሰርን የሚሉትም በመቶ ሚሊዮኖች ነበር፡፡
ኒው ዮርክ ታይምስ አገኘሁት ባለው ሰነድ ትራምፕ ዋይትሐውስ ከገቡ በኋላ በነበሩ 2 ዓመታት ብቻ በውጭ አገር ከሚገኙ ኩባንያዎቻቸው 73 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አጋብሰዋል፡፡
ይህም አብዛኛው አየርላንድና ስኮትላንድ ከሚገኘው የጎልፍ መጫወቻ ማዕከል የተገኘ ነው፡፡
ትራምፕ የቴሌቪዥን ትእይንት አቅራቢ በነበሩበት ጊዜ አፓረንሲስ ከተሰኘው ዝነኛ የቲቪ ትእይንታቸው እንዲሁም ስማቸውን ለንግድና ማስታወቂያ ለመጠቀም የተፈራረሙት ገቢን ጨምሮ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን ለገቢዎች ያስመዘገቡት ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ ነው፡፡
ትራምፕ የገቢ ግብር ላለመክፈል የሚጠቀሙበት ሌላወ ዘዴ አንድን ኩባንያ ሲገዙ ኪሳራውን አብሮ ገዝቶ ከቀጣይ ዓመታት ገቢ ግብር እፎይታን የማግኘት ዘዴ ነው ይላል ጋዜጣው፡፡
ለምሳሌ ትራምፕ በ2018 እርሳቸው በባለቤትነት የያዙት ትልቁ ማያሚ የሚገኘው ናሽናል ዶራል ጎልፍ ክለብ 162 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራን አውጇል፡፡ በተመሳሳይም በስኮትላንድና አየርላንድ የገዙት ጎልፍ በድምሩ 63 ሚሊዮን ዶላር ኪሳራ ሪፖርት አድርጓል፡፡













