ቴክሳስ: የከተማው ውሃ ጭንቅላትን በሚያጠቃ ገዳይ ተህዋሲ በመበከሉ ነዋሪዎች አትጠጡ ተባሉ

በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት የሌክ ጃክሰን ከተማ ነዋሪዎች የቧምቧ ውሃ እንዳይጠጡ ማስጠንቀቂያ ተላልፎላቸዋል።
ለዚህም ምከንያቱ ገዳይ የተባለና ጭንቅላትን የሚያጠቃ ረቂህ ተህዋሲ በከተማዋ የውሃ አቅርቦት ላይ በመገኘቱ ነው።
በተደረጉ ምርመራዎችም ናይግሌሪያ ፎውለሪ የተባለ ረቂቅ ተህዋሲ በከተማዋ ውሃ ማሰራጫ ጣቢያና በመስመሮቹ ይገኛል ተብሏል።
ይህ ረቂቅ ተህዋሲ አዕምሮን ከመጉዳቱ በላይ ይገድላልም ተብሏል።
ምንም እንኳን በአሜሪካ ውስጥ እንዲህ አይነት ጉዳቶች የተለመዱ ባይሆኑም አይከሰቱም ማለት አይደለም። በጎሮጎሳውያኑ 2009-2018 ባሉት 34 ጉዳቶች ሪፖርት ተደርገዋል።
የሌክ ጃክሰን ባለስልጣናት ውሃውን ለማከም እየሰሩ ቢሆንም ምን ያህል ጊዜ ግን እንደሚወስድ አልታወቀም።
ለዚህም ነው በዚህ ሳምንት አርብ ላይ ለነዋሪው ውሃውን ለሽንት ቤት ካልሆነ ለመጠጥ እንዳይጠቀሙ የተነገራቸው፥
ምንም እንኳን ማስጠንቀቂያው ከሌክ ጃክሰን አልፎ ሌሎች የቴክሳስ አካባቢ ነዋሪዎችንም ደርሷቸው የነበረ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት መጠቀም እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል። ነገር ግን ከ2 ሺህ 700 ነዋሪዎች ባሉባት ሌክ ጃክሰን አሁንም ማስጠንቀቂያው እንዳለ ነው።
የሌክ ጃክሰን ባለስልጣናት ውሃውን እንጠጣለን የሚሉም ካሉ አፍልተው እንዲጠጡ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል። ይህም ብቻ አይደለም ገላቸውን በሚታጠቡበትም ወቅት ውሃው በአፍንጫቸው ወይም በአፋቸው እንዳይገባም ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል ተብለዋል።
በተለይም ህፃናት፣ የእድሜ ባለፀጎችና በሽታን መቋቋም የማይችሉ ነዋሪዎች የበለጠ ተጋላጭ ሊሆኑ እንደሚችሉም የከተማዋ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ እየተናገሩ ነው።
ውሃውን ከመነሻው ለማከም እንዲሁም ለማስወገድ እየሞከሩ እንደሆነ ገልፀው ውሃው ለመጠጥ ከመብቃቱ በፊት በርካታ ምርመራዎችን እናካሂዳለን ብለዋል።
ውሃው ረቂቅ ተህዋሲያን መያዙ የታወቀው የስድስት አመት ልጅ ባለፈው ወር መሞቱን ተከትሎ ሲሆን ከዚያም ጋር ተያይዞ ምርመራ ሲካሄድ ከውሃው ጋር ግንኙነት መኖሩንም የከተማዋ አስተዳዳሪ ሞደስቶ ሙንዶ ለሪፖርተሮች ተናግረዋል።
ናይግለሪያ ፎውለሪ የሚባለ ረቂቅ ተህዋሲ በአለማችን ላይ በተፈጥሮ ውሃዎች ላይም ይገኛል። ያልታከመውን ውሃ የሚጠጡትም ረቂቅ ተህዋሲው ወደ ጭንቅላት ተጉዞም አዕምሮ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል።
የአሜሪካው የበሽታዎች መከላከያና ቁጥጥር ማዕከል (ሲዲሲ) በበኩሉ እንዲህ አይነት ኢንፌክሽኖች የሚያጋጥሙት ሰው በቀላሉ በማያገኛቸው የተፈጥሮ ውሃዎች ላይ በሚዋኙበት ወቅት ነው ይላል። የተበከለውን ውሃ በመጠጣት እንዲህ አይነት ኢንፌክሽን እንደማያጋጥም የሚናገረው ማዕከሉ ከሰው ወደ ሰውም አይተላለፍም ይላል።
በናይግሌሪያ ፎውለሪ የተጠቁ ሰዎች ከፍተኛ ሙቀት፣ ማቅለሽለሽ፣ ትውከት፣ የአንገትና ከፍተኛ ራስ ህመም የሚያጋጥማቸው ሲሆን፤ በርካታዎቹም በሳምንት ውስጥ ይሞታሉ።
በባለፈው አመትም በአሜሪካዋ ግዛት ፍሎሪዳ ተመሳሳይ መበከል አጋጥሞ የነበረ ሲሆን በወቅቱም የጤና ኃላፊዎች ከቧንቧ ውሃ እንዳይጠጡ አስጠንቅቀው ነበር።












