ዘረኝነት፡ በፓሪስ የባሪያ ንግድን ለተቃወመችው ሴት ሐውልት ሊቆምላት ነው

ዘረኝነት፡ በፓሪስ የባሪያ ንግድን ለተቃወመችው ሴት ሐውልት ሊቆምላት ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ስር በነበረችው የካሪቢያን ደሴት 'ጉዋድሎፕ' ውስጥ በአውሮፓውያኑ 1802 የባሪያ ንግድን በመቃወምና አመጽ በመቀስቀስ ለምትታወቀው ጥቁር ሴት ፓሪስ ውስጥ ሐውልት ሊቆምላት እንደሆነ ተገልጿል።

ይህች ጀግና ሴት 'ሶሊትዩድ' በሚል ስም ብቻ የተጠቀሰች ሲሆን ምናልባትም በወቅቱ ከተያዘች በኋላ ሳትገደል እንዳልቀረች ይታመናል።

በዝች ሴት ስም የተሰየመውን የሕዝብ መዝናኛ ቅዳሜ ዕለት መርቀው የከፈቱት የፓሪሷ ከንቲባ አን ሂዳልጎ ሶሊትዩድ ''ጀግኒት'' እና ''ጠንካራ ተምሳሌት'' በማለት አሞካሽተዋታል።

በአሜሪካ የተጀመረውን የ'ብላክ ላይቭስ ማተር' እንቅስቃሴን ተከትሎ በፈረንሳይም ከዚህ በፊት ከነበራት የቅኝ ግዛት ታሪክ ጋር በተያያዘ በርካታ ጥያቄዎች መጠየቅ ጀምረዋል።

በቅርቡም የፈረንሳይን የቅኝ ግዛት አካሄድ እንዳረቀቀና ለቅኝ ግዛት መስፋፋት ብዙ እንደሰራ የሚነገርለት ዦን ባፕቲስት ኮልበርት እንዴት ፓሪስ ውስጥ በሚገኘው የአገሪቱ ፓርላማ ውጪ ላይ ሐውልት ይቆምለታል በሚል ተቃውሞ ተነስቶ ነበር።

ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ደግሞ እንደዚህ አይነት ሐውቶችን ማፍረስ ተገቢ አይደለም በማለት ተከራክረዋል። እንደ ዦን ባፕቲስት ኮልበርት ያሉ በ17ኛው ክፍለ ዘመን ለባሪያ ንግድ አስተዋጽ ያደረጉ ሰዎች ሐውልትና ማስታወሻዎች መኖራቸው የኋላውን ታሪካችንን ጠንቅቀን እንድናውቅና እንድንማርበት ይረዳልም ማለታቸው አይዘነጋም።

በዩኔስኮ መዝገብ ላይ በተገኘ መረጃ መሰረት ሶሊትዩድ የተቀላቀለ ዘር ያላት ሲሆን በወቅቱ በፈረንሳይ አብዮት እንዲወገድ ተደርጎ የነበረውን የባሪያ ንግድ ናፖሊዮን ቦናፓርቴ እንደገና መልሶት ነበር።

ሶሊትዩድም የባሪያ ንግድን በመቃወም የሽምቅ ውጊያ በማድረግ ላይ ሳሉ በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል አንዷ ነች።

ከተያዘችም በኋላ በሞት እንድትቀጣ ተደርጓል። ነገር ግን በተጻፈው ታሪኳ ላይ ከመገደሏ በፊት ልጅ እንድተወልድ ተደርጋ ነበር ይላል። በፈረንሳይኛ ይህ ቃል ሌላ ትርጉም አለው። ምናለባትም ከመሞቷ በፊት እንደ ግርፊያ ባለ የማሰቃያ መንገድ እንድትሰቃይ ተደርጋ ነበር ማለትም ሊሆን ይችላል።

ሶሊትዩድ በአውሮፓውያኑ 1972 በታዋቂው የፈረንሳይ ጸሀፊ አንድሬ ሽዋርትዝ ባርት ተጠቅሳ የነበረ ሲሆን ጉዋድሎፕ ውስት ደግሞ በስሟ ሐውልት ቆሞላታል።

አሁን ደግሞ በፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ሐውልት ሊቆምላት ነው።

ምንም እንኳን ፓሪስ ውስጥ ለጥቁር ሴቶች ሐውልት ማቆም የተለመደ ባይሆንም ሶሊትዩድግ ግን ሐውልት ቢቆምላት በርካቶች ደስተኛ እንደሚሆኑ ሀሳባቸውን ገልጸዋል።