ሚሊዮኖችን የጨፈጨፉ፣ የባርያ ፈንጋዮችና የዘረኞች ሃውልቶች መገርሰስ

የንጉስ ሊዮፖልድ ሁለተኛ ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ንጉስ ሊዮፖልድ ሁለተኛ አስር ሚሊዮን የሚሆኑ ኮንጎዎችን ጨፍጭፏል።

የጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በነጭ ፖሊስ እጅ መሞቱን ተከትሎ የተቀጣጠለው ተቃውሞ በምዕራባውያን ዘንድ ትልቅ ስፍራ የሚሰጣቸው አሳሾች፣ ጦረኛ ነገሥታት ሃውልቶችን እንዲገረሰሱ አነሳስቷል።

ምንም እንኳን እነዚህ ሰዎች ለምዕራባውያኑ ትልቅ ቢሆኑም በአፍሪካውያንም ሆነ በደቡቡ ዓለም ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያና መደፈርን ሌሎች አሳፋሪ ታሪኮችን የፈፀሙ ናቸው።

የቤልጅየሙ ንጉሥ ሊዮፖልድ ኮንጎ ላይ አስር ሚሊዮኖችን ጨፍጭፏል፣ እጅ ቆርጧል፣ ሰቅሏል። አሳሹ ክርስቶፎር ኮሎምበስም እንዲሁ ቀደምት አሜሪካውያንን ጨፍጭፏል፤ ከምድረገ ፅም እንዲጠፉ ብዙ ጥሯል። ሌሎችም ስመ ጥር የሆኑ ምዕራባውያን በርካታ ናቸው።

አውሮፓና አሜሪካ በባርያ ደም እንዲሁም በቅኝ ግዛት በተዘረፈ ንብረት ከመገንባታቸው አንፃር፤ የሚኩራሩበት "ስልጣኔም" ሆነ በጀግንንት የሚያሞካሿቸው ሰዎች ጭቆናን በተጸየፉ የዓለም ሕዝቦች "ዝርፊያና ጭፍጨፋ ስልጣኔ አይደለም" በሚል ተጋልጠዋል።

በአፍሪካ ላይ የደረሰውን ጭፍጨፋም ሆነ ጭቆና ከታሪክ መዛግብት ለመፋቅና አዲስ ትርክት ለመፍጠር ቢሞከርም አልተቻለም። ባርያዎችን በማጋዝ የሚታወቁ፣ በቅኝ ግዛት ወቅት ጭፍጨፋን የፈጸሙ ምዕራባውያን ሃውልቶች በአሁኑ ወቅት እየተገረሰሱና እየወደሙ ይገኛሉ።

ከሰሞኑ ከተገረሰሱትና ጉዳት ከደረሰባቸው ሃውልቶችና ከሃውልቶቹ ጀርባ ያሉትን ሰዎች ታሪክ እንቃኝ፦

በአስራ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን የባርያ ነጋዴ የነበረው እንግሊዛዊው ኤድዋርድ ኮልስተን ከ80 ሺህ በላይ አፍሪካውያንን ወደ አሜሪካ አግዟል። ከሰሞኑም ከፍተኛ ግፍ የፈፀመውን የኤድዋርድን ሃውልት ተቃዋሚዎች ከትውልድ ቦታው ብሪስቶል በመገርሰስ ውሃ ውስጥ ከተውታል።

እንግሊዝም ሆነ የትውልድ ከተማው ብሪስቶል በባርያ ንግድ ሃብትን አከማችታለች፤ በአፍሪካውያን ጫንቃ፣ ላብና ደም በልጽገዋል።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የሃውልቱ መገርሰስን ተከትሎ የእንግሊዝ መንግሥት ድርጊቱን ቢያወግዝም ተቃዋሚዎች ግን የለውጥ ምልክት ነው ብለዋል።

"የሃውልቶች መቆም የሚያመላክተው ታላላቅ ሥራዎችን ላበረከቱ ነው። ኤድዋርድ ግን የባርያ አጋዥና ነፍሰ ገዳይ ነበር፤ ለእሱ ምልክት መቆሙ አይገባውም በማለት" የታሪክ አዋቂው ዴቪድ ኦሉሶጋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሄንሪ ዱንዳስ

የሄንሪ ዱንዳ ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, ባርነት እንዳይቆም የታገለው የሄንሪ ዱንዳ ሃውልት

በስኮትላንድ መዲና ኤደንበራ ባርነት እንዲወገድ ጥያቄ ቢቀርብም በእምቢተኝነቱ ፀንቶ ያዘገየው ፖለቲከኛ ሄንሪ ዱንዳስ ሃውልት ቆሞለታል።

ከሰሞኑም ሃውልቱን በቀለም በመርጨት ጆርጅ ፍሎይድና ብላክ ላይቭስ ማተርስ የሚሉ ቃላቶችም ተፅፈውበታል።

በቅዱስ አንድሪው አደባባይ የሚገኘው ሃውልት 46 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በጎርጎሳውያኑ 1823 ነው የቆመው።

በ18ኛው እና በ19ኛው ክፍለ ዘመን ተፅእኖ ፈጣሪ የነበረው ፖለቲከኛ "ያልተቀባው ንጉሥ" የሚል ስያሜም እንዲሰጠው አድርጎታል።

የባርያ ንግድን የሚያስቆም ረቂቅ ሕግ በጎርጎሳውያኑ 1792 ቢቀርብም ፖለቲከኛው ለአስራ አምስት ዓመታት አዘግይቶታል ተብሏል።

በሃውልቱ ላይ ተቃውሟቸውን ሲገልፁ

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ሃውልቱ እንዲገረሰስ ፊርማ አሰባስበዋል።

ምንም እንኳን ተቃውሞዎች ቢበረክትም ሃውልቱ ላይ ከተማዋ ከባርያ ንግድ ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚያንፀባርቅ መግለጫ እንደሚጨመርና፤ ሃውልቱ እንደሚቆይ ገልፀዋል።

"በዓለም ታሪክ ውስጥ ኤደንብራ የነበራትን አስተዋፅኦ መንገር አለብን። የምንኮራበትን ታሪክ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ሁላችንንም የሚያሳፍሩ ታሪኮችም ይፋ ሊወጡ ይገባቸዋል" በማለት የከተማዋ ኃላፊ አዳም ማክቬሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ንጉሊዮፖልድ ሁለተኛ

ንጉስ ሊዮፖልድ ሁለተኛ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ንጉስ ሊዮፖልድ ሁለተኛ አስር ሚሊዮን የሚሆኑ ኮንጎዎችን ጨፍጭፏል።

ቤልጅየምን ለረዥም ዘመናት የገዛው የንጉሥ ሊዮፖልድ ሁለተኛ ሃውልት እንዲገረሰስ ጥያቄዎች እየቀረቡ ነው።

በተለያዩ ድረ ገፆች ላይ የይገርሰስ ፊርማዎች የተሰባሰቡ ሲሆን እስካሁንም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ፈርመዋል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ ጥያቄ ከመጠየቅ አልፈው ሃውልቱን በቀይ ቀለም የረጩት ሲሆን እንዲሁም የሃውልቱን ጭንቅላት በጨርቅ ሸፍነውታል። ጨርቁም ላይ በነጭ ፖሊስ በግፍ የተገደለውን የጆርጅ ፍሎይድ ቃላትን "መተንፈስ አልቻልኩም" ተፅፎበታል።

በአንትወርፕ ከተማ የሚገኘው የቅኝ ገዥው ንጉሥ ሌላኛው ሃውልትም ተቃዋሚዎች በእሳት ያነደዱት ሲሆን ባለስልጣናቱም እንዲነሳ አድርገው ወደ ሙዚየም አስገብተውታል።

በመዲናዋ ብራስልስ የሚገኘው ሃውልት ደግሞ "ነፍሰ ገዳይ" ተብሎ ተፅፎበታል።

በጎርጎሳውያኑ 1865- 1909 ቤልጅየምን የገዛው ጨካኙ ንጉሥ በኮንጎ በፈፀመው ግድያና ጭፍጨፋ ይታወሳል።

ኮንጎን እንደ ግል ግዛቱ በመውሰድም ዜጎቿን ጎማ እንዲያመርቱ የባርያ ማዕከላትን መስርቷል።

ባርነትን እምቢ ያሉት ደግሞ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፤ የተገደሉትንም ሰዎች እጅ እየተቆረጠም መዘባበቻ አድርጓል። በአስር ሚሊዮን የሚቆጠሩ የኮንጎ ዜጎችን ጨፍጭፏል። ግፉ ተቆጥሮ የማያልቀው ንጉሥ የኮንጎ ዜጎችን ወደ ቤልጅየም በመውሰድ እንደ እንስሳ ፓርክ ውስጥ በማስገባት እንዲጎበኙ አድርጓቸዋል።

ምንም እንኳን የኮንጎ የንጉሡ ቅኝ ተገዢነት በጎርጎሳውያኑ 1908 ቢያበቃም አገሪቱ ከቤልጅየም ነፃ የወጣችው በጎርጎሳውያኑ 1960 ነው።

በቤልጅየም ሃውልቱ እንዳይወገድ የሚቃወሙ አንዳንዶች እንደ ምክንያትነት የሚጠቅሱትም ቤልጅየም የበለፀገችው በንጉሡ ወቅት መሆኑን በመጥቀስ ነው፤ በደም የበለፀገች መሬት።

ሮበርት ኢ ሊ

የሮበርት ኢ ሊ ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ግዛት ዘረኛ የሚባለውንና ባርነትን ይደግፍ የነበረው የኮንፌደሬት የጦር ጄኔራል ሮበርት ኢ ሊን ሃውልት ለማስወገድ ወስናለች።

የጆርጅ ፍሎይድ ግድያን ተከትሎ በተነሳው ተቃውሞ ሃውልቱ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

በጎርጎሳውያኑ 1890 የቆመው ሃውልት አስራ ሁለት ቶን (አስራ ሁለት ሺህ ኪሎ ግራም) የሚመዝን ሲሆን የቨርጂኒያ አስተዳዳሪ ራልፍ ኖርታም "ሐሰተኛ የታሪክ ትርክት ይበቃናል" ብለዋል።

አክለውም "ይህ ሃውልት ለረዥም ዘመናት ቆይቷል። የዚያን ጊዜም መተከሉ ስህተት ነበር፤ አሁንም ስህተት ነው። ስለዚህ እንገረስሰዋለን" ብለዋል።

በአካባቢውም አምስት የኮንፌደሬት ሃውልቶች የሚገኙ ሲሆን ከሰሞኑ በተከሰተው ተቃውሞ የተለያዩ ቀለሞች ተረጭቶባቸዋል፤ የነጭ የበላይነት ይቁም የሚሉም መልዕክቶች ተፅፎባቸዋል።

ሮበርት ኢ ሊ በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ባርነት አይቁም በሚል ሲዋጋ የነበረው የደቡባዊው ግዛቶች ጥምረት የሆነው የኮንፌደሬት የጦር አበጋዝ ነበር።

የጦር አበጋዙ በቨርጂኒያ ውስጥ የሚታወቁ በባርያ አሳዳሪነት የበለፀጉ ቤተሰቦች ልጅ ሲሆን ያገባው፤ ከጦሩ ከወጣም በኋላ የባርያ አሳዳሪ ነበር።

ለነፃነት የሚታገሉ ባርያዎችን በመደብደብም ይታወቃል። የባርያ ቤተሰቦችን በመነጣጠልም ብዙ ግፍ ፈፅሟል።

ለበርካታ ጥቁሮች የጦር አበጋዙ የአገሪቱ የባርነት ታሪክና የዘረኝነት ጭቆና ተምሳሌት ነው። ሌሎች እንዲሁ የኮንፌደሬት ሃውልቶች በተቃዋሚዎች ዘንድ ከጥቅም ውጪ ሆነዋል።

አንዳንዶች የአሜሪካ ታሪክና የደቡብ ባህል አካል በመሆናቸው ሃውልቶቹ ሊፈርሱ ይገባሉ በማለት የሚከራከሩም አልታጡም።

ዊንስተን ቸርችል

በለንደን የሚገኘው የዊንስተን ቸርችል ሃውልት

የፎቶው ባለመብት, PA Media

የምስሉ መግለጫ, "በቀደምት አሜሪካውያን ጭፍጨፋም ሆነ አውስትራሊያ በሚገኙ ጥቁር ህዝቦች መገደል መጥፎ ነገር ተፈፅሞባቸዋል ብዬ አላምንም" ያሉት የዊንሰተን ቸርችል ሃውልት

በእንግሊዝ መዲና የሚገኘው የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችል ሃውልት በተቃዋሚዎች ዘንድ ዘረኛ የሚል ፅሁፍ ከሰሞኑ ተፅፎበታል።

በእንግሊዛውያን ዘንድ አገሪቱን ለሁለተኛ ዓለም ጦርነት ድል ያበቃ መሪ እንዲሁም ድንቅ መሪ፣ ፀሐፊና ተናጋሪ ቢሉትም ከነጭ ዘር ውጪ በነበረው ንቀት አወዛጋቢም ሆኗል።

"ያለምንም ጥርጥር ዊንስተን ቸርችል ዘረኛ ነበር። ነጮች የበላይ ናቸው ብሎ ማመን ብቻ ሳይሆን በግልፅም በተደጋጋሚ ተናግሮታል" በማለት 'ቸርችል ሚይዝስ' የተሰኘ መፅሐፍ እየፃፉ ያሉት የታሪክ አዋቂው ሪቻርድ ቶዬ ተናግረዋል።

"ስለ ህንዳውያን የሚያፀይፍ ነገር ተናግሯል። ህንዶች አራዊት ናቸው፤ የእንስሳ እምነት ነው ያላቸው ብሏል፤ ስለ ቻይናውያንም እንዲሁ። ስለ ሌሎችም የተናገረው ማለቂያ የለውም" ብለዋል።

በጎርጎሳውያኑ 2015 'ቸርችል፡ ዘ ኤንድ አፍ ግሎሪ' ደራሲ ጆን ቻርምሌይ ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ዊንስተን ቸርችል በዘር የደረጃ እርከን ያምን እንደነበር ተናግረዋል።

በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የዘር አከፋፈል መሰረት ከላይ የሚቀመጡት ነጭ ፕሮቴስታንቶች፣ በመቀጠል ነጭ ካቶሊኮች ከዚያም ከአፍሪካውያን በልጠው ህንዳውያን ናቸው። አፍሪካውያን የመጨረሻውን ቦታ ሲይዙም ከሰውም ያነሱ ናቸው ብሎ ያምን ነበር።

በጎርጎሳውያኑ 1937 ዊንስተን ቸርችል ለፍልስጥኤም ሮያል ኮሚሽን እንደተናገረው "በቀደምት አሜሪካውያን ጭፍጨፋም ሆነ አውስትራሊያ በሚገኙ ጥቁር ሕዝቦች መገደል መጥፎ ነገር ተፈፅሞባቸዋል ብዬ አላምንም። በጠንካራ፣ በላቀና በጠራ ዘር ተሸንፈዋል። ቦታቸውንም ተቀምተዋል" ብሏል።

ከዚህም በተጨማሪ በአይሁዶችና በእስልምና ተከታዮችም ላይ በሰጣቸው አስተያቶችም ይወገዛል።

በጎርጎሳውያኑ 1943 ሁለት ሚሊዮን ሰዎችን በገደለው የቤንጋል ረሃብ በሰጠው ሰቅጣጭ አስተያየትም ታሪክ በአሉታዊ ገጹ ያስታውሰዋል።