ጥቁር ሰው በነጭ ፖሊስ ጉልበት ተደፍቆ ሲሞት ማየት እንዴት ይቻለኛል?

ፊቷን በእጆቿ የሸፈነች ጥቁር ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በሚኒያፖሊስ አንድ ነጭ ፖሊስ በሦስት ባልደረቦቹ ታግዞ ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድን እጁ ከኋላ እንደተጠፈረ አንገቱን ከመሬት ላይ አጣብቆ በጉልበቱ ደፍቆ ሲገድል የሚያሳየው ቪዲዮ ዓለምን አስደንግጧል።

መረበሽና መጨነቅ ፊቱ ላይ የሚታይበት ጆርጅ ፍሎይድ የመጨረሻ እስትንፋሱም ስትወጣ፤ ህቅታውንም ዓለም ግድያውን በማየት ምስክር ሆኗል።

"መተንፈስ አልቻልኩም" እያለ ሲለምን፤ የሞቱትን እናቱን እንዲደርሱለት ሲማፀን የነበረው ጆርጅ "እባክህ፣ እባክህ፣ እባክህ" በማለት ህይወቱ እንዲተርፍም ነጩን ፖሊስ ጠየቀ።

ጆሮ ዳባ ልበስ ያለው ፖሊስም አልሰማም ለዘጠኝ ደቂቃ ያህልም በጉልበቱ እንደተንበረከከበት ቆየ፤ በመጨረሻም የጆርጅ ፍሎይድ ህይወት አልባው ሰውነቱ ተወሰደ።

የቴክኖሎጂ ሁለት ገፅታ፤ ግድያን ወደድንም ጠላንም በአይናችን ሲያሳየን በሌላ መልኩ ግፉንም አጋልጧል። የጆርጅ ፍሎይድ መማፀን የብዙዎችን ልብ ሰብሯል፤ ይህንን ቪዲዮ ለቀረፀችው ለአስራ ሰባት ዓመቷ ታዳጊስ በወቅቱ ምን ተሰምቷት ይሆን?

ለጆርጅ ፍሎይድ ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ወዳጅስ የህይወቱን መጨረሻ በቪዲዮ ማየት የሚፈጥረው ስሜት በቃላት መግለፅ ይቻል ይሆን?

ይህንን ቪዲዮ አላይም ያሉም በርካታ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ጥቁሯ ጋዜጠኛ ሳንድሪን ሉንጉምቡ አንዷ ናት ለምን ቪዲዮውን እንደማትመለከት በእራሷ አንደበት ትተርካለች። የሌሎችንም ልምድ ታጋራለች።

Presentational white space

እንደ ጥቁር ሴት ይህንን ቪዲዮ ማየት አልችልም። መሳሪያ ያልያዘ አንድ ጥቁር ሰው በነጭ ፖሊስ ጉልበት ተደፍቆ ሲሞት ማየት እንዴት ይቻለኛል? አድካሚ ነው፤ የማያቋርጥ ቅዠት፣ ህመምን ይፈጥራል።

ቪዲዮው ግፍን በማጋለጡ፤ ለዘመናት የሰፈነውን ማኅበራዊና መዋቅራዊ ዘረኝነት እውነታም ይፋ በማድረጉ ልደሰት እንደምገባ ብዙዎች ነግረውኛል። እንዲህ ዝም ብዬ ሳስበው ለአንድ ጋዜጠኛ ከእውነት በላይ ምን አለ?

ነገር ግን በዓመታት ውስጥ እንዲህ አሰቃቂ እውነታን በማጋለጥና የአዕምሮዬን ጤና በመጠበቅ መካከል ልዩነት እንዳለ ተረድቻለሁ። በተለይም ከራሴ ማንነት፣ ልምድ ጋር በፅኑ የተቆራኘ ከመሆኑ ጋር እንዴትስ መነጠል ይቻላል?

እንዲህ አይነት ቪዲዮዎችን ለሚመለከት ለማንኛውም ሰው አስጨናቂ ቢሆንም እንደእኔ ላሉት ጥቁር ሰዎች ደግሞ ከአስደንጋጭም በላይ ነው። ሌሎች ህመሞችን ይቀሰቅሳል።

የጆርጅ ፍሎይድ ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማያቋርጥ ቅዠት

ኒያ ዱማስ ገና ሃያ ዓመቷ ነው፤ ሩጣ ያልጠገበች፤ ነገር ግን ጥቁር መሆን ከዕድሜ በላይ ያደርጋል።

ከነጮች እኩዮች በላይ ማደግን፣ መብሰልን እንዲሁም መጠንቀቅን ይጠይቃል። የጆርጅ ፍሎይድንም ግድያ ካየች በኋላ አልቅሳ አላባራችም፤ ስታዋራኝም ሳግ እየተናነቃት ነበር።

"ካየሁት በኋላ ቢያንስ በቀን አራት ጊዜ አለቅሳለሁ። መቼም ቢሆን ከህሊናዬ አይጠፋም" ትላለች።

በክሊቭላንድ ኦሃዮ ያደገችው ኒያ ለግድያም ሆነ ለግጭቶች አዲስ አይደለችም። በህፃንነቷም ወቅት ጥቁሮች ሲሞቱ ማየት የህይወቷ አካልም ነበር።

"ጆርጅ ፍሎይድ ባይሆን ሌላም ጥቁር ይገደላል። ዋናው ጥቁር ሆኖ መገኘት ነው። ጥቁር መሆን ወንጀል ይመስል፤ ለጭንቅላትም ከባድ ነው። የማያቋርጥ ቅዠት" ትላለች።

የጆርጅ ፍሎይድም መገደል በነጭ የአካባቢ ጥበቃ ህይወቱ የጠፋውን ታዳጊውን ትሬይቮን ማርቲንን አሟሟት አስታወሳት። "ትሬይቮን ሲገደል አስራ አንድ አመቴ ነበር። ከዚያ በኋላም ለዓመታት በርካታ ጥቁሮች ሲገደሉ አይቻለሁ። ደክሞኛል። አሞኛል" ብላለች።

የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ኒያ ዱማስ በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ነዋሪ ናት

የፎቶው ባለመብት, NIA DUMAS

የምስሉ መግለጫ, የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ኒያ ዱማስ በአሜሪካ ኦሃዮ ግዛት ነዋሪ ናት

'ብላክ ላይቭስ ማተር' [የጥቁሮች ህይወት ዋጋ አለው] እንቅስቃሴ በአሜሪካ ሳይወሰን በመላው ዓለም ለሚገኙ ጥቁሮችም የፀረ ዘረኝነት እንቅስቃሴን አቀጣጥሏል።

ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ ትግልን መቀጠል ለብዙዎች አድካሚ ነው። የ27 ዓመቱ ቶኒ አዴፔግባ ዘረኝነት ካደከሙት ውስጥ አንዱ ነው።

ጥቁር እንግሊዛዊው ቶኒ በተለይ የዚህ ወር ጫናው ከብዶታል። "የተፈተንበት ወር ነው። አህመድ አርበሪ ግድያን ቪዲዮ በቅርቡ አየን፤ ቀጠለ ሌላ ጥቁር ሰው ጆርጅ ፍሎይድ ተከተለ።"

የ25 ዓመቱ አህመድ አርበሪ ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ በወጣበት ወቅት ነው በዘረኛ አባትና ልጅ ጥይት ህይወቱ የጠፋው።

ለቶኒ በተለይ የጆርጅ ፍሎይድን የመጨረሻ እስትንፋስና መማፀንን ማየት ከዘግናኝም በላይ ነው።

"የተሰማኝን ህመም በቃላት መግለፅ ይከብደኛል። መንፈሴ እንደተሰበረ ይሰማኛል። ጥቁር ሰው መሆን ብቻ ኢላማቸው መሆኑ ጋር ተያይዞ እኔም እሆን ነበር። አድካሚ ነው" ብሏል።

በማያቋርጠው የዘረኝነት ትግልም በዚያኑ ሳምንት በኒው ዮርክ ሴንትራል ፓርክ ወፎችን ሊያይ የመጣ አንድ ጥቁር ሰው አንዲት ነጭ ግለሰብን እፅዋትን እንዳያበላሽና ወፎቹንም እንዳያስደነብር 'ውሻሽን እሰሪ' በማለቱ ለፖሊስ እደውላለሁ "ጥቁር አሜሪካዊ ለህይወቴ እያሰጋኝ ነው እላለሁ" በማለት ማስፈራቷንም አይቷል ።

ግለሰቧ ፖሊስ ያለውን ጭካኔ ለጥቁሮች ምህረት እንደሌለው በማወቅ እንደ መሳሪያነትም ልትጠቀም ማሰቧ ከፍተኛ ውግዘትን አስከትሎባታል።

በእንግሊዝ ነዋሪ የሆነው ቶኒ አዴፔግባ

የፎቶው ባለመብት, TONI ADEPEGBA

የምስሉ መግለጫ, በእንግሊዝ ነዋሪ የሆነው ቶኒ አዴፔግባ

"በጣም ነው የሰቀጠጠኝ። በቆዳዋ ቀለም ያላትን የበላይነት ታውቃለች። ያንን በመጠቀምም የጥቁሩን ህይወት አደጋ ውስጥ መክተት እንደሚቻል ተረድታዋለች። ከዚህም በላይ ያለውን የኃይል ተዋረድ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው" የሚለው ቶኒ።

"ግለሰቡን በአንድ ስልክ ማሳሰርም ሆነ ማስገደል እንደምትችል ታውቃለች" ብሏል።

ከፍተኛ ግፍና ስቃይ በጥቁሮች ላይ ማየት ያደከመው ቶኒ የጆርጅ ፍሎይድንም ሙሉውን ቪዲዮ ለማየት አንጀቱ አልቻለም።

"መጀመሪያ እንዲሁ ተቀንጭቦ ሳየው ለምንድን ነው ቆመው የሚያዩት የሚል ጥያቄን አጫረብኝ" ነገር ግን ብዙዎቹ በእሱ ቦታ ሊሆኑ እንደሚችሉ ስለተረዱ ነው።

በቅርብ ሳምንታት እነዚህን ቪዲዮዎች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ማጋራት ላይ ስላለው ፋይዳም የተለያዩ ውይይቶችን አድርጌያለሁ።

የዘር ግንዷ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚመዘዘውና ፓሪስ የተወለደችው የ28 ዓመቷ ላይቲታ ካንዶሎም ብትሆን በመጀመሪያ ቪዲዮውን ማየት አልቻለችም።

"በርካታ ስሜቶች ተፈራረቁብኝ እናም ዜናውን ስሰማ ላለማየት ወስኜ ነበር። ከሰዓታት በኋላ ግን ቪዲዮውን ሲቀባበሉት እኔም አየሁት። እርዳታ የሌለው ሰው ነበር። እኔም እንደሱ እርዳታ ቢስ እንደሆንኩ ተሰማኝ።"

ላይቲታ ካንዶሎ

የፎቶው ባለመብት, LAETITIA KANDOLO

የምስሉ መግለጫ, ፈረንሳይና ኮንጎ የምትሰራው ላይቲታ ካንዶሎ

"ዘረኞችን ሥራቸው የሚጋለጥበትን ተግባር ሁሉ ማከናወን አለብን" የምትለው ላይቲታ "እንደዚህ አይነት ቪዲዮዎች በቆዳቸው ቀለም የተለየ ቦታ ያገኙ ሰዎችን ቆም አድርጎ የሚያሳስባቸው ከሆነ ለሕዝብ ይፋ መሆን አለባቸው።"

"ማስታወስ ያለብን ነገር ነጮች እነዚህን ቪዲዮዎች ያያሉ፤ ለእኛ ግን የየቀኑ የህይወታችን አካል ነው" በማለት ታስረዳለች።

በተለይም ጥቁር ያልሆኑ ሰዎች እነዚህን ቪዲዮዎች በተለያዩ ሚዲያዎች ሲያጋሩ ማየት የጥርጣሬ መንፈስን ያሰፍናል።

ኒያ በተለያዩ ድረገፆች ላይ ያለው ድጋፍ ላይ ከፍተኛ ጥርጣሬ አላት። በተለይም እነዚህ ድጋፎች መዋቅራዊ የሆነውን ዘረኝነትን የመንካት ሚናቸው ምን ያህል ነው በሚልም ጥያቄ ታነሳለች።

"በርካታ ነጭ ታዋቂ ሰዎች ቀድመው የተዘጋጁ የሚመስሉና ከላይ ከላይ ብቻ ዝም ብለው የሚያወሩ አርቲፊሻል መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ" አያለሁ ትላለች።

የተወሰኑ ሰዎችም እውነተኛ ድጋፍ ማድረጋቸውን ብትወደውም "አሳ ስለዋኘ አታጨበጭብም" በማለት መስራት የሚገባቸውንና ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን የሚያስጨበጭብ ሥራ እንዳልሆነ ታስረዳለች።

"በዘረኝነት ጉዳይ ላይ የሰውየውን አስተሳሰብ፣ አቋምና ለማጥፋትስ ምን እያደረገ ነው የሚለው ነገር ትኩረት ልንሰጠው የሚገባው ጉዳይ ነው። በማኅበራዊ ሚዲያ ፅሁፎችን፣ ቪዲዮዎችን ስላጋራን ድጋፍ የሚመስለን ብዙ አለን። ተሳስተናል። ከእሱ አልፈናል" በማለትም መሰረታዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ትገልፃለች።

በኒውዮርክ ከተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች መካከል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

"ከአዕምሮዬ መቼም ቢሆን አይጠፋም"

ጥቁር ሰዎች እንደነዚህ አይነት ቪዲዮዎችን በሚመለከቱበት ወቅት ራሳቸውን ወይም የቤተሰባቸውን አንድ አካል እንዲሁም ከባርነት ጀምሮ ሲሰቃዩ የነበሩ የቅድመ አያቶቻቸው ምስል ድቅን ይልባቸዋል።

"የአህመድ ቪዲዮ ሲወጣ ብዙ ጊዜ እሮጥ ነበር እናም ስሮጥ ያዩኝ ወንጀል ሰርቼ የምሸሽ መስሏቸው ፖሊስ ጋር ሊደውሉ ይችላሉ የሚለው ሃሳብ በአዕምሮዬ ይመላለሳል። አሜሪካ ብሆን ደግሞ የእሱ እጣ ፈንታ ሊደርሰኝ እንደሚችል አስባለሁ" በማለት ቶኒ የፈጠረበትን ስሜት አጋርቷል።

"እያንዳንዱ ጥቁር ሰው ጥቁርነቱን ሲረዳና እንዲህ አይነት ክስተቶችም በዓለም ላይ ያለው ፀረ- ጥቁርነትና ያለህን ቦታ ያሳዩሃል" የምትለው ላይቲታ በአስራ ስምንት ዓመቷ ወደ ፋሽን ትምህርት ቤት ለመግባት ባቀደችበት ወቅት ከአባቷ ጋር የነበራትን ውይይት ታስታውሳለች።

"አባቴ አንቺ ጥቁር ነሽ፤ እንደ ጥቁርነትሽም በምዕራቡ ዓለም የጥበብ ቦታ ለመግባት ቀላል አይሆንም። ትግል ነው የሚሆንብሽ። ከነጭ እኩዮችሽ በበለጠ መስራት ይጠበቅብሻል የሚለውን እውነታ አረዳኝ። ተሰበርኩኝ ማለት ይቻላል። አለቀስኩ" ብላለች።

"የጆርጅ ፍሎይድ ታሪክ የኔም ነው"

በዓለም ላይ የምንገኝ ጥቁር ሕዝቦች ዘረኝነትን በየቀኑ ነጮች ፊታቸውን ከሚያከፉብን ጀምሮ፣ መዋቅራዊ እንዲሁም ታሪካዊ ዳራውን እንረዳለን።

በምሥራቅ ለንደን በአፍሪካ ብዝሃ ባህል ከማደጌ አንፃር መጀመሪያ በፍቅር ነው ያደግኩት። ከዚያ ግን ዩኒቨርስቲ ጋዜጠኝነት ለማጥናት ስገባ እውነተኛው ዓለም ምን እንደሆነ ተረዳሁ።

አፍሮ ፀጉሬ የመወያያ ርዕስ ነበር። በፀጉሬም መዘባበት እንዲሁም መወልወያ ይመስላል፤ ሥራም አታገኝም እያሉ ነጮች ቀልደውብኛል።

እንዲህ አይነት ዘረኛ ቪዲዮዎችን ስናይ ለብዙ ጥቁሮች የራሳችንን አስከፊ ትዝታ ወይም ደግሞ እንደ ህዝብ እየደረሱብን ያሉ ግፎችን ይቆሰቁሳሉ።

ፀረ-ዘረኝነት ሰልፎችን የሚያስተባብረው ትሪስተን ቴይለን ለጆርጅ ፍሎይድ ሞት ተቃውሞ ላይ የተሰማውን ስሜት በእንባ ገልፆታል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፀረ-ዘረኝነት ሰልፎችን የሚያስተባብረው ትሪስተን ቴይለን ለጆርጅ ፍሎይድ ሞት ተቃውሞ ላይ የተሰማውን ስሜት በእንባ ገልፆታል

"ለጥቁሮች በሙሉ የጆርጅ ፍሎይድ ታሪክ የእኛ ነው፣ የእኔ ነው። ጥቁሮች በሙሉ በአንድም በሌላ መንገድ የምንጋራቸው በርካታ ነገሮች አሉ" ትላለች ላይቲታ።

"እነዚህ ምስሎችም ሆነ ቪዲዮዎች ታሪካዊ የሆነ ቦታ አላቸው። በቅኝ ግዛት ወቅት ቤልጅየማውያን ኮንጎዎችን ሰቅለዋቸዋል፣ አንቀው ገድለዋቸዋል፣ እጃቸውንም ቆርጠውታል። በሰው ልጅ ላይ ዘግናኝ ነገሮችን ፈፅመዋል።

"ለዘመናትም ገድለውናል፤ ሊገድሉንም እየሞከሩ ቢሆንም አልጠፋ አልናቸው፤ በህይወት አለን። ነገር ግን እንዲህ አይነት ግድያዎች አድካሚ ናቸው። እስከመቼስ ነው የሚቀጥለው? በአዕምሮ ጤናችን ላይ የሚያደርሰውም ጫና ቀላል አይደለም" ብላለች።

ለበርካታ ዓመታትም ማኅበራዊ ሚዲያን በመጠቀም ዘረኝነትን መቃወም፣ የፖሊስ ጭካኔን ብታወግዝም የጆርጅ ፍሎይድ ግድያ ግን ከምትቋቋመው በላይ በመሆኑ ለአዕምሮዋ ጤንነት ቦታ መስጠት እንዳለባት ተሰማት።

"አእምሮ ጤናችን ቅድሚያ ልንሰጠው ይገባል"

የቶኒም ልምድ ከዚህ የተለየ አይደለም አዙሪቱ በማያልቀው የዘረኝነት ትግል ውስጥ መግባትና የአዕምሮ ጤንነቱን መጠበቅን አብሮ ማስኬድ አለበት።

"ጆርጅ ፍሎይድ እንዳይረሳ ማድረግ፤ ስሙንም ማንሳት የእኛ ተግባር ነው። ነገር ግን ለብዙ ጥቁር ሰዎች የምመክረው ቪዲዮውን ለማየት መገደድ የለባቸውም። ማጋራትም አይጠበቅባቸውም። ለአዕምሮ ጤንነታችን ቅድሚያ ልንሰጥ ይገባል" ብሏል።

"ጥቁርና ነጭ መባባል አቁመን እንደ ሰው መተያየት ስንጀምር። የእነሱ ችግር ነው ብለው መጠቆም ሲያቆሙና ሁላችንም የምንረባረብበት ሲሆን ችግር መሆኑ ያቆማል" ብሏል።