ዶናልድ ትራምፕ ቻይና በጆ ባይደን ላይ ምርምራ ትጀመር ሲሉ ጠየቁ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስልጣን እንዲወርዱ ጥያቄ ባስነሳው የዩክሬንና የጆ ባይደን ጉዳይ ሳይላቀቁ በድጋሚ ቻይናም የባይደን ምርመራ ላይ እንድትሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ትራምፕ እንዳሉት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫው ተፎካካሪ የሆኑት የዴሞክራቲክ ፓርቲው ጆ ባይደንና ወንድ ልጃቸው ላይ ቻይና እና ዩክሬን ምርመራ መጀመር አለባቸው።

ዴሞክራቶች ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዩክሬን ጆ ባይደን ላይ ጥላሸት ለመቀባት የሚጠቅሙ መረጃዎችን እንድትፈልግና በምላሹ ወታደራዊ እርዳታ እንደምታገኝ ቃል ገብተዋል በማለት ይከስሷቸዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ እና የዩክሬኑ አቻቸው ዜሌንስኪ በወርሃ ሐምሌ ያደረጉት የስልክ ልውውጥ በተቺዎቻቸው እንዲብጠለጠሉ አድርጓቸዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንት ትራምፕ እሳቸውን ከስልጣን ለማስነሳት የተጀመረውን ሂደት 'የማይረባ' ሲሉ አጣጥለውታል። አክለውም ''ፕሬዝዳንት እንደመሆኔ ሙስናን የመመርመር ሃላፊነት አለብኝ፤ ለዚህ ደግሞ የሌሎች ሃገራትን ሃሳብና እርዳት መጠየቅ እችላለሁ'' ብለዋል።

ጆ ባይደን እና ወንድ ልጃቸው ሃንተር በዩክሬንና በቻይና ፖለተካዊና ንግድ ነክ ጉዳዮች ላይ ሙስና ፈጽመዋል ሲሉ ፕሬዝዳንት ክስ ካቀረቡ ሰነባብተዋል።

የጆ ባይደን የ2020 ምርጫ ቅስቀሳ ቃል አቀባይ እንዳሉት ፕሬዝዳንቱ '' በብሄራዊ ቴሌቪዥን ቀርበው የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው እየቀበጣጠሩ ነው። ያልተጨበጠ መረጃ ይዘው ነው የቀረቡት። ታማኝ የመረጃ ምንጮች ያጣጣሉትን ዜና አሁንም ይዘው አልልቅም ብለዋል'' ሲሉ የመልስ ምት ሰንዝረዋል።

ጆ ባይደን በ2013 ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት ወደ ቻይና ተጉዘው ነበር። በጉብኝታቸውም ከቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዢን ፒንግ እና ሌሎች ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ወንድ ልጃቸው ሃንተር ባይደን እና ሴት ልጃቸው ምክትል ፕሬዝዳንቱን ተከትለው ወደ ቻይና ሄደውም ነበር።

ሃንተርም ምንም አይነት የሰራሁት ስህተት የለም፤ ህጋዊ በሆነ መንገድ ነው የቻይና ባለስልጣናትን ያነጋገርኩት ሲል ክሱን እንደማይቀበለው ገልጿል።

ትራምፕ ከዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ጋር በስል ምን አወሩ?

ትራምፕ በስልክ ልውውጡ ወቅት "ስለ ባይደን ልጅ በርካታ የምንነጋገረው ነገር አለ። ባይደን ልጁ እንዳይጠየቅ አቃቤ ሕጉ ማድረጉን በርካቶች ማወቅ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ከጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጋር ማንኛውንም ነገር ብታደርግና ጉዳዩ ቢታይ መልካም ነው።

ባይደን ልጁን ከተጣያቂነት ስለማስመለጡ በአደባባይ ጉራውን ይቸረችራል፤ ስለዚህ ጉዳዩን ብታየው. . . ለኔ መቼም እንዲህ አይነት ነገር ዘግናኝ ነው" ብለዋል።

የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ "በመከላከያ ረገድ እያደረጉት ስላለው ድጋፍ ላመሰግን እወዳለሁ። በቀጣዮቹ እርምጃዎች ላይ ለመተባበር ዝግጁ ነን። ለመከላከያ ኃይላችን ተጨማሪ ፀረ ታንክ ለመግዛት ዝግጁ ነን" ብለዋል።

ትራምፕ በምላሹም "አንድ ውለታ እንድትውልልኝ ልጠይቅህ እፈልጋለሁ። ምክንያቱም አገራችን በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ ማለፏን ዩክሬንን መቼም አይጠፋትም" ብለዋል።

በዚህ የስልክ ምልልስ ፕሬዝዳንት ትራምፕ በግልፅ የሌላ አገር ፕሬዝዳንትን ውለታ ጠይቀዋል ይላሉ ተንታኞች። ነገር ግን በምላሹ ምን እንደሚሰጡ ግልፅ አይደለም በማለትም ከዚህ የስልክ ምልልስ ቀደም ብሎ የተከናወነ ድርጊትን ያጣቅሳሉ።