"ሕዝብን ከማገልገል በላይ ክብር የለም"- አዲሱ የባህርዳር ምክትል ከንቲባ

አዲሱ የባህርዳር ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Amhara mass media agency

በትናንትናው ዕለት፣ ጥቅምት 6፣ 2013 ዓ.ም ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሹመዋል።

የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በስራ አመራርና ፍልስፍና ቻይና አገር ከሚገኘው ኋጁንግ ዩኒቨርስቲ በቅርቡ አጠናቀው የመጡት ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም በአማራ ክልል የምሁራን ተሳትፎና አደረጃጀት ዘርፍ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አማካሪ፣ የምዕራብ ጎጃም ዞን ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ፣ የሕዝብ ግንኙነትና የከተማ አደረጃት አማካሪና በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ ምክትል አስተዳደሪና ግብርና ጽኅፈት ቤት ኃላፊ ሆነው ካገለገሉባቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።

የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በመልክዓምድርና አካባቢ ጥናት ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲና ሁለተኛ ዲግሪ በመልካም አስተዳደርና በአመራር ጥበብ ከኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በተለያዩ የአመራር ቦታዎችም ላይ ሆነው አገልግለዋል።

በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባነታቸውን ሹመት፣ ሊያከናውኗቸው ያሰቧቸውን እቅዶችና ሌሎች ጉዳዮች በተመለከተ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ቢቢሲ፦ በትናንትናው ዕለት ሹመቱን ሲቀበሉ ምን እሰራለሁ? ምን ለውጥ አመጣለሁ ብለው ነው ሹመቱን የተቀበሉት?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደርን በተቀዳሚ ምክትል ከንቲባነት እንድመራ የድርጅትና የመንግሥት ኃላፊነት ሲሾመኝ፣ አንደኛ ይሄ ተልእኮ ነው።

የፓርቲው አባል ነኝ፤ ከፓርቲዬ የተሰጠኝን ተልዕኮ መቀበል የግድ ስለሚል ይህንን የተሰጠኝን ተልዕኮ ተረክቤ ከዚህ በፊት በግንባር ላይ እየሰሩ ካሉ አመራሮች ጋር በመካከር፤ በቀጣይ ባህር ዳር የኢንቨስትመንት መዳረሻ፣ ኢንዱስትሪ የተስፋፋባት፣ ሰላም የሰፈነባት፣ ፍትሃዊነት የተረጋገጠባት እና የሁሉንም ዜጎች ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ ስራዎችን ህዝብ ጋር በመካከር ለመስራት ነው።

የባህር ዳር ከተማ እንድታድግ እንድትበለፅግ የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት ነው። እኔም ይህንን ኃላፊነት የከተማዋን ነዋሪ ፍላጎት ለማሳካት በበኩሌ የሚጠበቅብኝን አስተዋፅኦ ለማበርከት ነው።

በቀጣይ አመራሩ ጋር ተነጋግረን፤ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት አካሂደን ከዚህ በፊት የተጀመሩ ስራዎችን፣ የታቀዱ እቅዶችንና ጅምሮችን ለማስቀጠል እናስባለን። በአዳዲስ የከተማ አስተዳደር ስርአቱን ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ለማዘመን አቅሜ የፈቀደውን ያህል የተጣለብኝን አደራና ለመወጣት ዝግጁነት የያዝኩ ብቻ መሆኔን ነው የማረጋግጠው በዚህ ሰዓት።

ምክንያቱም አሁን ገና ወደ ስራ እየገባሁ ነው። ከዚህ በፊት ይሄ ስራ እንደሚሰጠኝ ባለማወቄ እንዲሁም ይሄ ተልእኮ በመሆኑም ጊዜ ወስጄ ችግሮችን ለይቼ ከአመራሩ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በጋራ ተወያይተን የከተማዋን አጠቃላይ እድገት አንድ ደረጃ ወደፊት የሚያራምድ የአመራር ስርአት ለመዘርጋት ነው በግሌ ለማድረግ ያሰብኩት።

ቢቢሲ፡ በተለያየ የስራ ኃላፊነት ከመስራትዎ አንፃር እንዲሁም ከተማዋን ያውቁታል ብዬ ከማሰብም ከዚህ በፊት በነበሩ ሂደቶች ምን ክፍተት አዩ?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ ከዚህ በፊት የሰራሁባቸው የአመራር ተልእኮዎች በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ውስጥ አይደለም። በምእራብና ምስራቅ ጎጃም የሚባሉ ዞኖች ነው ሳገለግል የቆየሁት፤ በመሃልም የውጭ የትምህርት እድል አግኝቼ ትምህርቴንም ተከታትዬ ነው የተመለስኩት።

አሁን ገና ትምህርቴን አጠናቅቄ ከምረቃ በኋላ የተሰጠኝ አዲስ የስራ ስምሪት ነው። በአሁኑ ወቅት ባህርዳር ከተማ ላይ እንዲህ አይነት ጉድለቶች አሉ ብሎ ለመናገር ግምገማ ያላካሄድኩበት በመሆኔ ገና የተሰጠኝን ተልዕኮ ተቀብዬ ወደ ስራ ለመግባት ዝግጅት ላይ ነኝ።

ክፍተቶቹን ወይም ጠንካራ ጎኖች እነዚህ ናቸው ብዬ አሁን ባለሁበት ሰዓት ላይ ልናገር አልችልም። ምክንያቱም ገና ያልተገመገመ ነገር ይዤ በዚህ ላይ አስተያየት መስጠት ይከብደኛል።

ቢቢሲ፡ የድህረ ምረቃዎን ትምህርት የተከታተሉት በቻይና ነው። የተለያዩ የቻይና ከተሞችን ለማየት እድል አግኝተው ከሆነ ከዛ የቀዱት ነገር አለ ወደዚህ ባመጣው ብለው ያሰቡት?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ ቻይና የደረሰችበት የከተማ ልማት እና የኛ አገር ምንም እንኳን ለማወዳደር ልዩነቱ የሰፋ ነው። እዚያ ያየሁዋቸውን አንዳንድ ነገሮች በተለይም የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ላይ፤ የዘመናዊና ቀልጣፋ የአሰራር ስርአት ከመዘርጋት፣ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ የአገልግሎት አቅርቦት ላይ የተሻለ ነገር አይቻለሁ። አቅም በፈቀደ መጠን ከኛ አገር የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ልማት ስርአት ጋር የተገናዘበ የከተማ ስርአት አገልግሎት አቅርቦት ለማድረግ የዩኒቨርስቲ ምሁራንን እንዲሁም በዘርፉ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን በማማከር አሰራርን ለማዘመን ጥረት ማድረግ የሚገባ መሆኑ ይሰማኛል። እዚህ ላይም አቅሜ የፈቀደውን አስተዋፅኦ ለማድረግ ጥረት አደርጋለሁ ብዬ አስባለሁ።

ቢቢሲ፡ ምክትል ከንቲባ ሆነው በትናንትናው ዕለት ተሾመዋል። በስልጣን ላይ ሆኜ እሰራለሁ ብለው ቅድሚያ የሚሰጧቸው ነገሮች ምንድን ናቸው?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ በትናንትናው ዕለት ቃለ መሃላ ከፈፀምኩ በኋላ ለምክር ቤቱ ያቀረብኩት የመክፈቻ ንግግር ነበር። ከአመራሩም ሆነ ህብረተሰቡን በማሰለፍ ብንረባረብባቸው አጠቃላይ የከተማይቱን እድገት ያፋጥናል ብዬ የማምንባቸውን አቅጣጫዎች አቅም በፈቀደ መጠን ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ።

ከነዚህም መካከልም በተለይ በከተማ የመጀመሪያው ስራ- ኢትዮጵያ በሽግግር ላይ ያለች አገር ናት። ፖለቲካዊ ለውጦች እያካሄደችም ትገኛለች።

አሁን ያለው ፓርቲ ከኢህአዴግ ወደ ብልፅግና የተሸጋገረበት፣ አመራሩ ከላይ እስከ ታች በአዲስ እየተደራጀና እየተጠናከረ ያለበት፣ አዳዲስ አስተሳሰቦች ወደ መንግሥት አሰራር የገቡበት ማግስት ላይ ነው ወደ ስራ እየገባሁ ያለሁት።

ከዚህ ጋር የተጣጣመ የትኩረት አቅጣጫ ሊሆኑ ይችላሉ ብዬ የማስባቸውን አስቀምጫለሁ።

ከነዚህም መካከል በተለይም የከተማው አስተዳደር ውስጥ የህግ የበላይነትን ማስፈን፣ ሰላምን ማረጋገጥ የመልካም አስተዳደሮችን ለይቶ በህዝቡ ተሳትፎ መፍታት የሚሉት ይገኙበታል። የከተማዋ ያላትን ስመ ገናናነትና የከተማዋ እድገትን ሊመጥን የሚችል የመሰረተ ልማት ማስፋፋት ስራ ላይ በተለይም የእንጨት ልማት ፕሮጀክቶች ላይ አተኩረን የእለት ተግባራችን አድርገን መንቀሳቀስ ይገባል።

የከተማውን የህብረተሰቡን የመኖሪያ ቤት ችግር፣ ከዚህም የዘለሉ ሌሎች ተደራራቢ ጥያቄዎችን የህዝብ መድረኮች እየፈጠርን በመልቀም እንደ መንግሥት አቅም መፈታት የሚገባቸውን ቅድሚያ እየሰጠን እንሰራለን የሚሉ አቅጣጫዎች ነው ለማስቀመጥ የተሞከረው።

በተለይም የወጣቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ የስራ እድል መስኮችን በመፍጠር ላይ ያተኮረ ስራ እንሰራለን። የስራ እድል ፈጠራ ለሰፊው ህዝብ ትኩረት የምንሰጠው ጉዳይ ነው ይሄ ከተማ ላይ ያለ የድህነት ቅነሳ አካል ነው።

እነኚህ ጉዳዮች መልክ ከያዙ ከተማዋ ወደተሻለ ህይወት ውስጥ የምንገባበት አጋጣሚ ስለሚኖር እነዚህ ላይ አተኩረን ብንሰራ የሚል እሳቤ ይዤ ነው ወደ ስራ እየገባሁ ያለሁት። እንግዲህ ቀጣዩን ከእግዚአብሔር ጋር ከህብረተሰቡ፣ ከቅርብ አመራር ጋር በመሆን የምንችለውን ሁሉ በቅንነት ግልፅ (ትራንስፓረንት) በሆነ መንገድ፣ ህዝቡን አሳታፊ በሆነ መንገድ የከተማ አገልግሎት ለመስጠት ፍላጎቱ አለኝ። ያው ውጤቱን የምናየው ይሆናል።

ቢቢሲ፡ የጠቀሷቸውን ተግባሮች ለማከናወን ምን አይነት ተግዳሮት ይገጥመኛል ብለው ያስባሉ?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ በባለፉት ሶስት አመታትና ከዚያ በላይ ከአመራር ስርአት ውጭ ብሆንም በተለምዶ የሚታወቁ የከተማ ስራን ለመስራት የሚገዳደሩ ችግሮች አሉ።

እኛንም ትንሽ ይፈትነናል ብለን የምናስበው ከተማ የተለያዩ ፍላጎቶች አሉት። ግማሹ ህጋዊ በሆነ መንገድ ከተማ እንዲለማ የመፈለግ፤ ግማሹ ደግሞ በህገወጥ ወይም በአቋራጭ መንገድ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተቃራኒ ፍላጎቶች የሚሳተፉበት መድረክ ነው።

ፖለቲካዊ ፍላጎቱ ብዙና የተለያዬ የሆነበትና ሌሎች እንዲሁም ውስብስብ ችግሮች ያሉበት ነው- የከተማ ስራ። ስለዚህ እነዚህን ችግሮች አጣጥሞ ለመምራት የሚያስችል ብቁና ቅቡልነት ያለው በስነ ምግባር የታነፀ አመራር የመፍጠር፣ የማሰማራትና ከህብረተሰቡ ጋር አዋህዶ የማሰራት ሂደት ፈታኝ ሊሆን ይችላል።

እዚህ ላይ እኛም አተኩረን እንረባረባለን። ነገር ግን የሰው ልጅ ፍላጎት የተወሰነ ባለመሆኑ ህጋዊ ስርአት ተከትሎ በሚሰራበት ጊዜ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ሊነኩ ይችላሉ። በዚያን ጊዜ ማማረር ሊከሰት ይችላል።እኛ እነዚህን አስቀድመን ስለምናውቅ በተቻለ መጠን ከአመራሩ ጋር ተነጋግረን የሁሉንም ዜጎች ፍላጎት አጣጥሞ ከህግና ስርአት ውጭ ሳይሆን ከተማዋን በከተማ እቅድ (ፕላን) ማስተዳደር።

በዚያም መሰረት እንድትመራ የማድረግ ስራ እንሰራለን። እንግዲህ እዚህ ላይ ህብረተሰቡም ያግዘናል ብዬ ተስፋ የማደርገው ህጋዊነትን ብቻ ተከትለን ስንሰራ ከጎናችን የሚሆን ከሆነ ለውጥ እናመጣለን። ነገር ግን በመሃል አንዳንድ መንጠባጠቦች፤ ከዚህ ባፈነገጠ መንገድ መጠቀም የሚፈልጉ ኃይሎች ትንሽ ያስቸግሩን ይሆናል፤ በውይይት እየፈታን እንሄዳለን።

እንሻገራለዋን የሚል ተስፋ እንዲሁም እምነት አለኝ። በመወያየት የማይፈታ ችግር የለም ተብሎ ስለሚታሰብ ዋናው ነገር አመራሩንም ህዝቡንም ያሳተፈ የአመራር ዘይቤን መከተል፤ እነዚህን ተግዳሮቶች እናልፋቸዋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ከዚህ በዘለለ በስራ ሂደት የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ እንደዬ አፈጣጠራቸውና እንደ አመጣጣቸው እንመልሳለን ብዬ አስባለሁ።

ቢቢሲ፡ባህርዳር ከተማን የተለያየ ከንቲባዎች መርተዋታል፤ ባለን መረጃ ቶሎ ቶሎ የመቃየየር ሁኔታም አለ። ከዚህ ቀደም የነበሩት ከንቲባ በውበት፣ በፅዳት ጋር ተያይዞም ይወደሳሉ። እርስዎስ በየትኛው በኩል እወደሳለሁ ብለው ያስባሉ?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ ከዚህ በፊት የነበሩ ከንቲባዎች ባህርዳር ዛሬ ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ የየበኩላቸውን አሻራ ጥለው አልፈዋል። በርካታ ጥሩ ጥሩ የሚባሉ ከተማዋን ወደፊት ያራመዱ ተግባራትን ፈፅመዋል። ይሄም የሚያስመሰግናቸው ነው።

በዚያኑ ልክ ግን የሰው ልጅ ወደ ስራ በሚሰማራበት ወቅት ጥንካሬዎች እንዳሉ ድክመቶችም ሊኖሩ ይችላሉ። እኛ መከተል የምንፈልገው እነሱ ሰርተውት በሄዱት ላይ ተጨማሪ ስራ እየሰራን ጥሩውን እያስቀጠልን ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ መቀጠል።

ድክመት ነበሩ ተብለው የሚታሰቡ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ደግመው እንዳይፈፀሙ እያስተካከልን ነው ለመሄድ ያሰብነው። በቅርብ ከለቀቁት ከንቲባ ጋር ተያይዞ በርካታ ተስፋ ሰጭ ብዙ ደስ ደስ የሚሉ ስራዎችን ጀምረው የሄዱ መስሎ ነው የሚሰማኝ። እርሳቸው የጀመሯቸውን በጎ ተግባራት አጠናክረን እንቀጥላለን።

ከዚህ ውጭ ደግሞ ክፍተት በምንላቸው ነገሮችን እንሞላለን። እሱ በምን ይሳካልዎታል ለሚለው? እሱን በቀጣይ በተግባር ብናየው ይሻላል። ምክንያቱም አሁን ወደ ስራ ባልተገባበት ሰዓት ላይ በዚህ ስራ የተሳካልኝ እሆናለሁ ማለት የአካባቢውን ሁኔታ በደንብ ሳላይ፣ ገምግሜ ክፍተቱን በጥሩ ሁኔታ ለይቼ ባልገባሁበት ወቅት ላይ ይሄ ውጤታማ ያደርገኛል፣ አያደርገኝም ብሎ ለመናገር የሚያስቸግረኝ ይመስለኛል።

አዲሱ የባህርዳር ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Amhara mass media agency

ቢቢሲ፦ ሹመቱ ያልጠበቁት ይመስላል። በርግጥ እሾማለሁ ብለው ላያስቡ ይችላሉ። ለዚህ ሹመት የሚታጩ ሰዎች አካባቢውን በደንብ የሚረዳ ፣ ከተማውን በደንብ የሚያውቅ፣ ክፍተት ሊሞላ የሚችል፣ ጎዶሎውን ሊያውቅ ይችላል ተብሎ የሚታሰብ ሰው ነው ብዬ አስባለሁ….

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ ልክ ነው፤ ሹመት በሚሰጥበት ጊዜ በበለጠ አካባቢውን የሚያውቅ ሰው ቢሆን ይመረጣል። አካባቢውን በማወቅ ብዙ ችግር ያለብኝ አይመስለኝም። ከዚህ በፊት ባህርዳር ላይ የተወሰነ ጊዜ ሰርቻለሁ። ባህርዳር ዩኒቨርስቲ እንዲሁም አሁን ካለው አመራር ጋር በመቀናጀት በአመራርነት ብዙ ጊዜ ስላሳለፍኩኝ መረጃዎቹም አሉኝ። እውነት ለመናገር እሾማለሁ ብዬ አልጠበቅኩም። እኔ ትምህርቴን ጨርሸ ስመጣ፤ በድርጅታችን አሰራር መሰረት የፖለቲካ ሹመት የሚሰጠው ተነግሮ አይደለም። የትምህርት እድል ተሰጥቶኝ ተምሬ ስመጣ አመራር ቦታ ላይ እንደምመደብ አውቃለሁ፤ የትኛው ቦታ እንደሆነ የሚወስነው የፓርቲው ፅህፈት ቤት ነው። አንድ ሰው ካለው የትምህርት ዝግጅት፣ የስራ ባህርይና ሌሎችም ጉዳዮች ከግምት ውስጥ ገብተው ነው ሹመት የሚሰጠው።

እንግዲህ ፓርቲው በዚህ ቦታ ላይ ሲመድበኝ ለዚህ ስራ ይመጥናል የሚል እምነት ይዟል ማለት ነው። እኔ ግን እንደ አንድ አመራርና አባል የተሰጠኝን ተልእኮ ስፈፅም ቆይቼ፣ ትምህርቴን አጠናቅቄ መምጣቴንና ሌላ ተጨማሪ ተልዕኮ ፓርቲዬ እንዲሰጠኝ እየጠበቅኩ ስለነበር የባህርዳር ከተማ ከንቲባ ሆኜ እሾማለሁ ብዬ አልጠበቅኩም።

ይሄ ተልእኮ ሲሰጠኝ ግን ህዝቡን ከማገልገል በላይ ሌላ ክብር ስለሌለ ፤ ህዝብን ማገልገል ኩራት ስለሆነ፤ ከዚህም በላይ ኃላፊነት ስለሌለ ከታመነብኝና ይህንን ስራ ይሰራል ብሎ ሹመቱን የሰጠኝ አካል አለ።

ምክር ቤቱም ይህንን የቤት ሰራ ወስዶ ተቀብሎ ካፀደቀው በኔ በኩል ባገለግል ምንም ችግር የለውም። የተማርኩትም ህዝቡን ለማገልገል ነው።

ቢቢሲ፡ ነፃ ሆኜ እስራለሁ፤ ነፃ ሆኜ ያሰብኳቸውን ነገሮች አሳካለሁ ብለው ያስባሉ?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ ፈተናዎች ይኖራሉ። ይሄ ግልፅ ነገር ነው። ከተማ ላይ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች አሉ። ያንን ሁሉ ፍላጎት ለሟሟላት ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ጠንቅቄ አውቃለሁ። ነገር ግን አቅም በፈቀደ መጠን ህሊናዬ የሚገፋኝን ለመስራት ዝግጁ ነኝ። ከዚህ በፊትም የአመራር ህይወቴ ልምዱም ስላለኝ የምችለውን ሁሉ ለመስራት እሞክራለሁ። የፓርቲ አመራሮችም ድጋፍ እንደሚያደርጉልኝም ሙሉ ቃል ገብተውልኛል። በተቻለ መጠን ህሊናዬ የሚያምንበትን ነገር ለመስራት እንቅስቃሴ አደርጋለሁ፤ እታገላለሁ። ከአቅም በላይ ሲሆን ደግሞ ብዙ አማራጮች አሉ ማለት ነው። ግን እኔ ከአቅም በላይ የሚሆን ነገር ይገጥመኛል ብዬ አላስብም።

በአሁኑ ሰዓት ፓርቲውም ሆነ መንግሥት የሚፈልገው የህብረተሰቡን ፍላጎት ማሟላት ነው። የህብረተሰቡን ፍላጎት ተረድተን በምንቀሳቀስበት ወቅት የሚመጣውን እንቅፋት የሚታገል በርካታ ኃይል ከጎን አለ።ይህንን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የምሞክረው ይሆናል ማለት ነው።

ቢቢሲ፡ ነፃ ሆነው እንዳይሰሩ ችግር ሊገጥምዎት ይችላል በስራ አጋጣሚ የሚገጥም ነው። እነዚህ ችግሮች ከየት በኩል ይመጣል ብለው ያስባሉ?

ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር)፡ ወደ ስራ ሳይገባ እንደዚህ አይነት ትንበያዎች (ፕሪዲክሽን) መስጠት ያሳስታል (ሚስሊድ ያደርጋል)። ምክንያቱም እኔ ዛሬ ተንብዬ ከዚህ አካባቢ ችግር ይመጣብኛል ብዬ ብናገር፤ ይመጣብኛል ብለሽ የምታስቢውን አካባቢ ማሳሰብም ስለሚሆን ወደ ስራ ገብቶ በተግባር ላይ የሚገጥም ችግርን ፊት ለፊት መጋፈጥ አማራጭ የሌለው መፍትሄ ይመስለኛል። ችግር የሌለው ስራ የለም። ህዝብን መምራት ትልቅ ከባድ እና አስቸጋሪ ነው። እያንዳንዱ አመራር ይህንን አውቆ ነው የሚገባው ።

ምንጊዜም ወደ ስራ ስንገባ ችግሮች እንደሚኖሩ አውቃለሁ። እንደየአመጣጣቸው ለመመለስ ራሴን አዘጋጅቻለሁ።