ኢትዮ-ኤርትራ፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ጉብኝቶች ምን ፋይዳ አላቸው?

የፎቶው ባለመብት, Office of the prime minister twitter page
በድንበር ይገባኛል ምክንያት ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል ተፋጠው የነበሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም መድረኩ መምጣታቸውን ተከትሎ የሁለቱ አገራት መሪዎች በርካታ የሥራ ጉብኝቶችን አካሂደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን መጥተው በአገራቱ መካከል ሰላም ከወረደ በኋላ ባሉት ጊዜያት የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂቢያንስ ለአራት ጊዜያት ያህል ከልዑካኖቻቸው ጋር ወደ ኢትዯጵያ በመምጣት ይፋዊ ጉብኝትና ውይይቶችን አድርገዋል።
እነዚህ ጉብኝቶች በተካሄዱባቸው ጊዜያት ሁሉ መሪዎቹ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ በደፈናው ከመጥቀስ በዘለለ የተደረጉ ውይይቶች ርእስና የደረሱባቸው ስምምነቶች እነዚህ ናቸው የሚሉ ዝርዝር መረጃዎች እስካሁን አልተሰጠም።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሰኞ ጠዋት ለሦስት ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በቀጥታ ወደ ጅማ ያመሩ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድም እዚያው በመገኘት ተቀብለዋቸዋል።
የፕሬዝዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ከአካባቢያዊና አገራዊ ሁኔታዎች አንጻር ያለውን አንድምታ የዓለም አቀፍና የፖለቲካ ተንታኙ አቶ አብዱራሕማን አቡ ሀሽም "አዲስ ነገር የሌለው" ሲሉ ይገልፁታል።
በአሜሪካ ጆርጂያ ጉኔት ኮሌጅ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ዮሐንስ ገዳሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው "እንዲህ አይነት ጉብኝት ቢያንስ በከፍተኛ ባለስልጣናት እና በሁለቱ መሪዎች መካከል በሚገባ ታስቦበት የተደረገ ነው" ሲሉ ይሞግታሉ።
አቶ አብዱርሃማን መጀመሪያ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ስምምነት ሲደረስ በኤርትራውያን ዘንድ የተለያዩ ጥያቄዎች እንደነበሩ በማንሳት፤ አስተዳደራዊና ሕጋዊ መሰረት መያዝ የነበረባቸው ጉዳዮች ሳይዙ መቅረታቸውን ጠቅሰው ስምምነቱ ለኤርትራውያን ያመጣው ለውጥ እንደሌለ ያስረዳሉ።
የሁለቱ አገራት ስምምነት ተስፋ አጭሮባቸው የነበሩ ወገኖችም ከዕለት ወደ ዕለት ተስፋቸው እየከሰመ መሄዱን የሚያነሱት አቶ አብዱርሃማን ስምምነቱ የሁለት አገራት ሳይሆን የሁለት ወዳጆች ይመስላል ሲሉ ተቋማዊ መልክ እንደሚጎድለው ይተቻሉ።
እንዲህ አይነት ግንኙነት ደግሞ ከዚህ ቀደምም በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል እንደነበር የሚያስታውሱት ምሁሩ፤ ነገር ግን ለሁለቱም አገራት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደተሳነው በመግለጽ የሁለቱን አገራት ሰላም በሁለት ግለሰቦች መካከል ብቻ ማድረጉ "ትክክል አይደለም፤ ዘላቂ ሊሆን አይችልም" ሲሉ ይገልጻሉ።
አቶ አብዱርሃማን "የአሁኑ የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት ምንም ልዩ የሚያደርገው ነገር የለም" በማለትም ይደመድማሉ።
ዮሐንስ ገዳሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው የሁለቱ አገራት መሪዎች መገናኘት በአጋጣሚ የተደረገ፣ ግጥምጥሞሽ ተደርጎ የሚታይ ሳይሆን ታቅዶበት የሚደረግ መሆኑ መታየት አለበት ሲሉ ይገልጻሉ።
ለዮሐንስ (ዶ/ር) የፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጉብኝት በሁለቱ አገራት በከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም በርዕሳነ መንግሥታቱ መካከል ቢያንስ አስቀድሞ የታሰበ ሊሆን ይችላል።
ሁለቱ አገራት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ግንኙነታቸው ወደተሳለጠ የኢኮኖሚ፣ የንግድ ትስስር፣ ልዩ ወደ ሆነ ትብብር አድጎ ባይታይም የውስጥ ለውስጥ ንግግሮች እንደሚኖሩ በተዘዋዋሪ እንደሚሰማ ያነሳሉ።
ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውንና ትብብራቸውን ወደዚያ ለማሳደግ መተማመን ማሳደግ እንደሚኖርባቸው የሚያነሱት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ ላለፉት 20 ዓመታት በግጭትና በፍጥጫ ውስጥ የነበሩ አገራት ከመሆናቸው አንጻር ብዙ መተማመን ብዙ መነጋገር የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አንዳሉ ያነሳሉ።
የሁለቱ አገራት ተደጋጋሚ ጉብኝት ያመጣው ለውጥ በኤርትራ ዘንድ እንደሌለ የሚያነሱት አቶ አብዱርሃማን በበኩላቸው አሁንም የኤርትራ መንግሥት "አምባገነን ሆኖ እንደቀጠለ ነው" ሲሉ ይገልፃሉ።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ላለፉት 30 ዓመታት ተቃዋሚዎቻቸውን በማፈን፣ በማሰር ስልጣን ላይ መቆየታቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያም ብትሆን ከኤርትራ ኢመደበኛ ጉብኝቶች ታተርፋለች ብለው እንደማያምኑ ይናገራሉ።
ግንኙነቱ የፓርቲ እንኳ ነው ብሎ ለመናገር እንደሚቸግር የሚገልፁት አቶ አብዱርሃማን በኤርትራ ፓርቲ አለ ለማለት እንደማያስደፍር ጠቅሰው፤ የአዲስ አበባው ብልጽግና ፓርቲም አንደኛ ጠቅላላ ጉባዔውን እንኳ አለማካሄዱን አንስተው የግለሰቦች ግንኙነት መሆኑን ያሰምሩበታል።
ዮሐንስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ይህ የሁለትዮሽ ግንኙነት የበለጠ እንዲዳብር ሁለቱ ርዕሳነ መንግሥታት አንዳቸው በሌላኛቸው አገር እየተገኙ መወያየት የመረጡ ይመስላል ሲሉ አክለዋል።
ሁለቱ አገራት የጋራ የሆነ ባህል ታሪክ የነበራቸው መሆኑን የሚያነሱት ዮሐንስ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚከሰት ማንኛውም ነገር ኤርትራ ውስጥ የራሱ ተጽዕኖ እንዳለው ሁሉ፤ ኤርትራ ውስጥም የሚከሰት ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የራሱ ተጽዕኖ አንደሚኖረው ያስረዳሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ችግር መኖሩን በማንሳትም የኤርትራ መንግሥት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን ጉዳይ በቅርበት ቢከታተል ሊያስደንቅ እንደማይገባም ይጠቅሳሉ።
ኤርትራ ውስጥም ቢሆን በርካታ ችግሮች መኖራቸውን የሚያነሱት ዮሐንስ ገዳሙ (ዶ/ር)፤ ነገር ግን ውጥረቱ የሚታየው በዲያስፖራው ዘንድ ስለሆነ ለኢትዮጵያ በቀጥታ አስተያየት ለመስጠትም ሆነ ለመሳተፍ ከባድ መሆኑን ይገልጻሉ።
እነዚህ ሁለቱ አገራት ግንኙነታቸውን እያደሱ ባለበት ሁኔታ በኢትዮጵያ ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት በቀጠናው ላይ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ተመልክቶ እንዲሁም የአገራቸውን ጥቅም ከግንዛቤ በማስገባት ተጽዕኖ ቢፈጥሩ ተጠባቂ መሆኑን ይገልጻሉ።
ጥያቄው መሆን ያለበት ከቀጠናው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ገንቢ በሆነ መልኩ ተሳትፈዋል ወይ? የሚለው መሆን እንዳለበትም ያስረዳሉ።
የኤርትራ እና የኢትዮጵያ መንግሥት የሰላም ስምምነት መካከል ተቋማዊ መልክ የያዘ ነገር ተሰምቶ እንማይታወቅ የሚተቹ ወገኖችን በተመለከተ ሲናገሩም "የሁለት መሪዎች መጨባበጥ ራሱ ተቋማዊ ቅርጽ አለው" ብለዋል።
ተቋማት ሲባሉ ግዑዝ ሕንጻዎች ወይንም የተለያዩ ሕጋዊ ሰነዶች ላይ ያረፉ ነገሮች ብቻ አለመሆኑን በማንሳትም የሚሰጡትና የሚያሳዩት ምላሽ እንዲሁም መሪዎች አንዳቸው ሌላኛቸውን የሚያዩበት መንገድንም እንደሚጨምር ይገልጻሉ።
በተደጋጋሚ የሚደረጉ ግንኙነቶች የሚመሰረቱ ተቋማት ላይ የራሳቸው የሆነ ተጽዕኖ እንደሚኖራቸው በማንሳትም፤ የዚህም ትልቁ ፋይዳ መተማመንን ማዳበር መሆኑን ጠቅሰው ቸል ሊባል የሚገባው አለመሆኑን ዮሐንስ (ዶ/ር) ያብራራሉ።
የመሪዎቹ የአሁን ግንኙነት ተቋማዊ ቅርጽ እየያዘ በሚመጣበት ወቅት የሁለቱ አገራት ሕዝቦች ብዙ እምርታ እንደሚያሳዩም በመግለጽ ተስፋቸውን ያስቀምጣሉ።
አገራዊ ነባራዊ ሐቆች በተለይ ደግሞ ኤርትራ ውስጥ ያለውን ሁኔታም በማንሳትም ከተመሰረተችበት ጊዜ አንስቶ ዝግ መሆኗን ማስተዋል እንደሚገባ ይነገራሉ።
ይህ ዝግ የነበረ የፖለቲካ ምህዳር በዚህ የሰላም ስምምነት ምክንያት ክፍት ወደ መሆን ሊሄድ መሆኑ ኤርትራውያኑ ራሳቸውንም ስጋት ውስጥ ሳይከታቸው እንዳልቀረም ያነሳሉ።
ከዚያ አንጻር ደረጃ በደረጃ ኢኮኖሚያዊና የሕዝብ ለሕዝብ ትስስር እንዲሄድ መፈለጋቸውን በማንሳት ከፌሽታና ከሆይ ሆይታው ረጋ ባለ መልኩ ጉዳዮችን እንደገና ለማጤን መፈለግ በእነርሱ ስፍራ መታየቱን ይገልጻሉ።
ሁለቱ አገራት የነበራቸውን ቁስል በአንድ ጊዜ አክመውና ረስተው ግንኙነታቸውን በፍጥነት ይጀምሩ ማለት አስቸጋሪ መሆኑን በማንሳትም የመረጡት መንገድ ተገቢ ነው ብለው እንደሚያስቡ ዮሐንስ ገዳሙ (ዶ/ር) ይናገራሉ።















