"የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ዕጣፈንታ የተያያዘ ነው" አምባሳደር ዲና

የፎቶው ባለመብት, MFA - Ethiopia
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በኢትዮጵያ ያደረጓቸው ተደጋጋሚ የስራ ጉብኝቶች አገራቱ መተባበር የሚችሉባቸውን መስኮች ያሳየ መድረክ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ዲና ሙፍቲ ገልፀዋል።
ለሁለት አስርት አመታት ሰላምና ጦርነት በሌለበት ሁኔታ ተፋጠው የነበሩትን ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ሰላም መድረኩን መምጣት ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ምን ይመስላል? እንዲሁም በተደጋጋሚ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ይዘቱ ምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ከጋዜጠኞችም ቀርቦላቸው ነው ይህንን ገለፃ የሰጡት
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በየሁለት ሳምንቱ ለጋዜጠኞች በሚያደርገው መግለጫም የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነትን ጨምሮ፣ በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጉዳይ፣ የኮሮናቫይረስና ሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮችን አስመልክተውም ቃለ አቀባዩ በዛሬው ዕለት፣ ጥቅምት 6/ 2013 ዓ.ም ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በሚመለከቱ ጉዳዮች ምላሽ የሰጡት ቃለ አቀባዩ ሁለቱ አገራት ደም አፋሳሽ በሆነው ጦርነት በርካታ ዜጎቻቸውን እንዳጡና ለሁለት አስርት አመታትም ያህል ጦርነትና ሰላም በሌለበት ሁኔታ የተፈጠረውን የሁለቱ የተሳሰሩ ህዝቦችን ግንኙነት ለማስቀጠልም እየተሰራ ነው ብለዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የአየር በረራ፣ ቀጥታ የስልክ መስመሮች መቀጠላቸው የአገራቱንም ሆነ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን የማስቀጠል ስራ እንደሆነ አስምረው ግንኙነቱ የሁለቱም ህዝቦች በሚፈልጉት መጠን ላይሆን ይችላል ተብሏል።
"የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ ህዝብ በሚፈልገው መጠን ባይሆንም፤ የአየር በረራ፣ የስልክ መስመሮች በቀጥታ መስራታቸው፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ ቀጥሏል። የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝብ ዕጣፈንታ የተያያዘ ነው።" ብለዋል
በቅርቡ በኢትዮጵያ የሶስት ቀናት የስራ ጉብኝታቸውን ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ስድስት ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል፤ ይህንንም ተከትሎ ጥያቄ ማጫሩንም ከጋዜጠኞቹ ጥያቄ ተወርውሯል።
ፕሬዚዳንቱ በአሁኑ ጉብኝታቸውም የህዳሴ ግድብን ጨምሮ የልማት አካባቢዎችንም ጎብኝተዋል።
የፕሬዚዳንቱ የስራ ጉብኝት ሁለቱ አገራት አብረው መስራት የሚችሉበትን ዘርፎች ከመቀየስ በተጨማሪ በመሪዎች መካከል የሚፈጠረው ቅርበትም ጠቃሚ እንደሆነ አምባሳደሩ ይናገራሉ።
"በተደጋጋሚ በመሪዎች መካከል የሚፈጠረው ቅርበትና መቀራረብ በአገሮች መካከል ለሚፈጠረው መቀራረብ መሰረት ፣ መደላደል ይሆናል።" በማለትም በሁለቱ አገራት የተጀመረውን ግንኙነት የማስቀጠል ስራም መሆኑን አፅንኦት በመስጠት በቀናነት መታየት አለበት ብለዋል።
የአለም ስጋት በሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በሁለቱ አገራት መካከል ያሉ በረራዎችና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱም እንደተቋረጠ የገለፁት ቃለ አቀባዩ ሆኖም ለወደፊት ችግሩ ሲቀረፍ የበለጠ የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝብ ግንኙነትም እንደሚዳብርም እምነታቸውን አስቀምጠዋል።
በዚሁ መግለጫም ላይ በተደጋጋሚ ጥያቄ ከጋዜጠኞች የተነሳው በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በተመለከተ ነው።
በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ኢ-ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ በእስር ቤት ታጉረው ለተለያዩ በሽታዎችና ሞቶች መዳረጋቸው አሳዛኝ መሆኑንም በወቅቱ ቃለ አቀባዩ ገልፀዋል።
ዜጎቿን ወደ አገራቸው ለመመለስም ከፍተኛ ጥረት እያደረገች ያለችው ኢትዮጵያም በባለፉት ሳምንታት 993 ኢትዮጵያውያን ዜጎች መልሳለች። ከነዚህም ውስጥ 955 ከሳዑዲ አረቢያ፣ 5 ከታንዛንያ 5፣ 35 ከጂቡቲ መሆናቸውንም አምባሳደር ዲና ጠቅሰዋል።
ምንም እንኳን መንግሥት በፈታኝ ሁኔታ ያሉትን ዜጎች ለመመለስ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖርም የስደተኞችን የማንነት ሁኔታ የማጣራትና ደህንነት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የመዘግየት ችግር እንዳለም ጠቅሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ እዚህ ከመጡ በኋላ በገፋቸው ችግር ተመልሰው እንዳይሄዱም የሚሰሩ ስራዎች እንዳሉም ጠቁመዋል።
የህገ ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ሚና እንዳለ ሆኖ በአገሪቷ ላይ የሰፈነው ዜጎችን ከአገር እንዲወጡ የሚገፉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የስራ አጥነትና የመሳሰሉት ምክንያቶች በዋነኝነት መቀረፍ እንዳለባቸውና መሰረታዊ መፍትሄ የሚባለውም ችግሩ ሙሉ በሙሉ ሲወገድ መሆኑንም አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, MFA - Ethiopia
"የመመለሱ ስራ እሳት የማጥፋት ስራ ነው ሆኖም አሁን ባለው ሁኔታ ዜጎችን የመመለሱ ጉዳይ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።
ባለፉት ሳምንታት የእንግሊዙ ጋዜጣ ቴሌግራፍ በማጎሪያ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ታሳሪዎች በስልካቸው ከላኳቸው ፎቶዎች መካከል ከመስኮት ላይ ራሱን የገደለ ግለሰብና በብርድ ልብስ የተጠቀለለ አስከሬን መታየቱ ስደተኞቹ ያሉበትን ሰቆቃ አስደንጋጭ አድርጎታል።
ያሉበት መከራና ስቃይ የምድር ሲኦል የሆነባቸው እነዚህ ስደተኞች ራሳቸውን ለማጥፋት የተገደዱና በመተፋፈጋቸውም ሞተዋል ተብሏል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው ስደተኞች ምግብ፣ ውሃ እጥረትና ከሰው በታች ሆነው ህይወታቸውን ለመግፋት በመገደዳቸው ስቃያቸውን ለመግለፅ ቃል አጥተዋል። በስቃይ ያሉት ሰደተኞች ለባለፉት ስድስት ወራት በዚህ መልኩ ማሳለፋቸውን በምሬት ተናግረዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በውጭ ጉዳይ የተመራው ቡድን ወደ ሱዳን አቅንቶ በጎርፍ ለተጎዳችው ሱዳን የመድኃኒትና የምግብ እርዳታ መለገሱንም ቃለ አቀባዩ አውስተዋል። በዛሬው መግለጫ ላይ ከጋዜጠኞች በተጨማሪ ቀርቦላቸው የነበረው ጥያቄ የውጭ ጉዳይና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በኢትዮጵያ ተቀማጭነታቸውን ላደረጉ የውጭ አገራት አምባሳደሮች የተሰጠውን መግለጫ በተመለከተ ነው።
በውጭ ጉዳይ አማካኝነት ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከከፍተኛ መንግሥት አካላት ጋር የተውጣጡ የስራ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ምርጫ ለምን እንደተላለፈ እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ትግራይ ክልል ያደረገችውን ምርጫ ያሳለፋቸውን ውሳኔዎች በሚመለከት ለአምባሳደሮቹ ማብራያ ተሰጥቷል።
"አምበሳደሮቹ ስለ አገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ሪፖርት ሲያደርጉ የተሳሳተ መረጃ ያቀብላሉ ያም በኢትዮጵያና በአገራቱ መካከል ግንኙነት ስለሚያበላሽ ያንንም ለማስተካከል ነው" መግለጫው እንደተሰጠ ጠቅሰዋል።
አምባሳደሮቹም በማጠቃለያቸው የኢትዮጵያ ሰላም፣ መረጋጋት፣ ብልፅግናና የኢትዮጵያ እድገትን እንደሚደግፉና የእነሱም ፍላጎት እንዳለበት መጥቀሳቸውን አምባሳደሩ ተናግረዋል።












