ኮሮናቫይረስ፡ በፈረንሳይ ከተሞች የሰዓት እላፊ ታወጀ

ከፍቴሪያ ውስጥ ያሉ ተጠቃሚዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፈረንሳይ መዲና ፓሪስን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የሰዓት እላፊ ታወጀ።

የሰዓት እላፊ የታወጀው እየጨመረ የመጣውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር ነው። ፈረንሳይ ከአውሮፓ የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ከሆኑባቸው አገራት መካከል አንዷ ናት።

የሰዓት እላፊ በታወጀባቸው ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ከምሽቱ 3 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ ከቤት መውጣት አይችሉም።

የሰዓት እላፊው ከታወጀባቸው ከተሞች መካከል ፓሪስ፣ ማርሴል፣ ሊዮን እና ሊል ይገኙበታል። 20 ሚሊዮን ፈረንሳውያን የሰዓት እላፊው አዋጅ ይተገበርባቸዋል።

የፈረንሳይ መንግሥት የሰዓት እላፊ አዋጁ መተግበሩን የሚያረጋግጡ 12ሺህ የፖሊስ አባላት እንደሚያሰማራ አስታውቋል።

ከምሽቱ 3 ሰዓት በፊት ምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ካፊቴሪያዎች እና ሲኒማ ቤቶች መዘጋት ይኖርባቸዋል።

የሰዓት እላፊውን ተላልፎ የሚገኝ ሰው 135 ዩሮ የሚቀጣ ሲሆን፤ ዳግም ተላልፎ የተገኘ ደግሞ የስድስት ወራት እስር እና የ3ሺህ 700 ዩሮ ቅጣት ይጠብቀዋል።

እንደ ሰርግ ያሉ ማህበራዊ ሰብስቦች ክልክል ናቸው።

በፈረንሳይ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ከ32ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው አልፏል።

ኮሮናቫይረስ በሌሎች የአውሮፓ አገራት

የስፔን መንግሥት በማድሪድ እና አካባቢዋ ለ15 ቀናት የሚዘልቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል። 7ሺህ ፖሊስ አባላት አዋጁን ያስፈጽማሉ።

መሠረታዊ ላልሆኑ ጉዳዮች ከማድሪድ መውጣትም ሆነ መግባት ክልክል ነው። ሆቴሎች እና ምግብ ቤቶች መያዝ ከሚችሉት አቅማቸው ግማሹን ብቻ ነው ማስተናገድ የሚችሉት።

በኔዘርላንድስ የቫይረሱ ስርጭት ዳግም እያገረሸ ይገኛል። በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍልም በከፊል የእንቅስቃሴ ገደቦች እየተጣሉ ይገኛሉ።

በአምስተርዳም መጠጥ ቤቶች እና ምግብ ቤቶች እየተዘጉ ነው።

በጀርመንም በተመሳሳይ የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ ይገኛል። በቀን ከ7ሺህ በላይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየተመዘገቡ ይገኛል።

ጀርመን አንዳንድ ጎረቤት አገራትን የቫይረሱ ስርጭት ከፍተኛ ደረጃ ደርሶባቸዋል ስትል አውጃለች።

ከእነዚህም መካከል ፈረንሳይ እና ኔዘርላንድስ ተጠቃሽ ናቸው። ከእነዚህ አገራት ወደ ጀርመን የሚገባ ተጓዥ ራሱን ለይቶ የማቆየት ግዴታ ይኖርበታል።

አየርላንድ በበኩሏ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የተለያዩ ገደቦችን ከጣለች አራት ሳምንታት አልፈዋታል። በመኖሪያ ቤት ሄዶ ወዳጅ ዘመድ መጠየቅ ከተከለከለ ሰነባብቷል።