ማክሮን፡ "ፈረንሳያዊው አንገቱን የተቀላው በሽብር ጥቃት ነው"

የፎቶው ባለመብት, EPA
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን ከመዲናዋ ፓሪስ አቅራቢያ አንገቱ ተቀልቶ የተገደለው መምህር "በእስላማዊ የሽብር ጥቃት ነው" አሉ።
በጥቃቱ የተገደለው መምህር አወዛጋቢ የሆኑ የነብዩ መሐመድን ካርቱን ምስሎች ለተማሪዎቹ ያሳይ ነበር ተብሏል።
ጥቃት አድራሹ በፖሊስ ተመትቶ ተገድሏል።
ፕሬዝደንት ማክሮን በስም ያልተገለጸው መምህር የተገደለው "ሃሳብን በነጻነት መግለጽን በማስተማሩ ነው" ብለዋል።
ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ ተገኝተው፤ "አያሸንፉም. . . ፈጣን እርምጃ እንወስዳለን" ብለዋል ፕሬዝደንት ማክሮን።
ስለጥቃቱ እስካሁን የሚታወቁ
ጥቃቱ የተፈጸመው ትናንት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 2 ሰዓት አከባቢ ትምህርት ቤት አቅራቢያ ነበር።
ጥቃት አድራሹ በመንገድ ላይ በትልቅ ቢላዋ የመምህሩን አንገት ቆርጧል። ፖሊስ እንደሚለው ማንነቱ ይፋ ያልተደረገው ጥቃት አድራሽ ጥቃቱን ሲያደርስ "አላሁ አክበር" ሲል የአይን እማኞች ሰምተውታል።
ግለሰቡ ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ከስፍራው ለመሰወር ቢጥርም ጥሪ የደረሰው ፖሊስ በፍጥነት በስፍራው ተገኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፖሊስ ጥቃት አድራሹ እጁን እንዲሰጥ ቢጠይቀውም ዛቻ በማድረሱ ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት ተገድሏል።
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ አራት ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ኤኤፍፒ ዘግቧል። በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦች ከጥቃት አድራሹ ጋር ዝምድና ሳይኖራቸው አይቀርም ተብሏል።
ምንም እንኳ ፖሊስ የጥቃት አድራሹን ማንነት ይፋ ባያደርግም፤ ቢኤፍኤምቲቪ የተሰኝ የፈረንሳይ የቴሌቪዥን ጣቢያ ጥቃት አድራሹ ሩሲያ ሞስኮ ውስጥ የተወለደ የ18 ዓመት ወጣት ነው ሲል ዘግቧል።
አንገቱ ተቀልቶ የተገደለው መምህር ማነው?
እንደ ሌሞንድ ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ የታሪክ መምህሩ በክፍል ውስጥ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ ጋር በተያያዘ አወዛጋቢ የነብዩ መሐመድ የካርቱን ስዕሎችን በመጠቀም ያስተምራል።
መምህሩ በዚህ ደስተኛ የማይሆኑ ተማሪዎች ካሉ ክፍሉን ለቀው መውጣት እንደሚችሉ ይናገር ነበር ብሏል ዘገባው።
ከሳምንታት በፊት ሙስሊም ወላጆች የመምህሩን ተግባር በመቃወም ለትምህር ቤቱ ቅሬታ አቅርበውም ነበር።
በፈረንሳይ መሰል ጥቃት ሲፈጸም ይህ መጀመሪያው አይደለም። ከሶስት ሳምንት በፊት ትውልደ ፓኪስታናዊ የ18 ዓመት ወጣት በስጋ መከትከቻ ትልቅ ቢላ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር።
እአአ 2015 ላይ ሁለት ሙስሊም የፈረንሳይ ዜጎች የቻርሊ ሄብዶ መጽሔት ቢሮን ሰብረው በመግባት በሰራተኞቹ ላይ ተኩስ ከፍተው ሰራተኞቹን ጨምሮ በጠቅላላው 12 ሰዎች ገድለው ነበር።














