የሴቶች መብት፡ ፈረንሳይ "ድንግልና" የሚመረምሩ ዶክተሮችን እቀጣለሁ አለች

ሴት ዶክተር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፈረንሳይ አወዛጋቢ የሚባለውን "የድንግልና ምርመራና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት" የሚሰጡ ዶክተሮችን በእስር እቀጣለሁ ብላለች።

"የድንግልና ሰርቲፊኬት" አብዛኛውን ጊዜ የሚጠየቀው ጋብቻቸውን በባህላዊ መንገድ ለሚያከናውኑ ነው።

ህጉ ገና በረቂቅ ደረጃ ላይ ያለ ሲሆን ከሰሞኑ ከእምነት ነፃ የሆነ የፈረንሳይ እሴቶችን መመለስ በሚል ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን "ኢስላማዊ ተገንጣይነትን" መዋጋት ብለው ካቀረቡት ኃሳብ ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።

የፈረንሳይ የፅንስ ማቋረጥ ቡድን በበኩሉ "የድንግልና ምርምራ" እንዲህ ዝም ብሎ ማስቀረት የማይቻል ሲሆን ሰፋ ያለ ትምህርትም ያስፈልገዋል ብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ቢሆን ይህንን ምርመራ በፅኑ ይቃወማዋል።

ረቂቅ ህጉ ገና ፓርላመንቱ ተወያይቶ ሊያፀድቀው የሚገባ ሲሆን በዚሁ ደረጃ ግን "የድንግልና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት" ለሰጠ ማንኛውም የጤና ባለሙያ አንድ አመት እስርና 15 ሺህ ፓውንድ ቅጣት ይጠብቀዋል።

የፈረንሳይ 3 ቴሌቪዥን ጣቢያ ከሰሞኑ እንደዘገበው 30 በመቶ የሚሆኑ ዶክተሮች "የድንግልና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት" እንደሚጠየቁና አብዛኛዎቹም በእምቢተኝነታቸው ይፀናሉ ብሏል።

የአለም ጤና ድርጅት የሴቶችንና ታዳጊዎችን ወሲብ መፈፀም አለመፈፀማቸውን በእይታም ሆነ በጣት ለማረጋገጥ መሞከር አንዲት ሴት ወሲብ ፈፅማለች የሚለውን አያረጋግጥም።

የሰብዓዊ መብታቸውንም የሚጥስና የሚገረስስ ነው በማለትም ያወግዛል።

የማህፀን ሃኪም የሆኑት ዶክተር ጋዳ ለፈረንሳዩ ኢንተር ኒውስ እንደተናገሩት "በፈረንሳይ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ላይ ተፅእኖ አያደርስም።

በየአመቱ ቢያንስ ሶስት ሴቶች "የድንግልና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት" የሚጠይቁኝ ሲሆን አብዛኛዎቹም ከሰሜን አፍሪካ የሚመጡ ናቸው" ብለዋል።

ሴቶቹ የቤተሰብ ክብር አዋርዳችኋል በሚል አካላዊ ጥቃት ይደርስብናል በሚል ፍራቻ ዶክተሯ ጋር የሚመጡ ሲሆን እሳቸውም ቢሆን "የድንግልና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬቱን" ይሰጣሉ።

"ወንድሜ ይደበድበኛል፤ አባቴ ያንቀኛል። አማቾቼ ስሜን ያጠፉታል ይህንን ሰርቲፊኬት ካላገኘሁ ይሉኛል። ላለማመን ምክንያት የለኝም" በማለትም ተናግረዋል።

"የድንግልና ምርመራ" በበርካታ አገራት እንደሚፈፀም የተባበሩት መንግሥታትና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርት ያሳያል። ምርመራው የሚፈፀመው ከእምነት ጋር በተገናኘ ብቻ ሳይሆን ከመደፈር ምርመራ እንዲሁም የፀጥታ ኃይሎችን ምልመላም ጋር በተያያዘም እንደሚከናወንም መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሙስሊም ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, AFP

በተለይም በሰሜን አፍሪካ፣ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ ህንድ፣ አፍጋኒስታን፣ ባንግላዴሽና ደቡብ አፍሪካ ይሄ ተግባር ተንሰራፍቶ ይገኛል።

ከሁለት አመት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መንግሥታት ይህንን ኢሰብዓዊ ተግባር እንዲያግዱት ጥሪ አድርጓል።

ከዚህም በተጨማሪ "የድንግልና ምርመራና" ኋላ ቀር የስርዓተ ፆታ ልምዶችም ምን ያህል የሴቶችንና ታዳጊዎችን ማንነትም ሆነ ሰውነት መቆጣጠሪያነትም እንደሚውሉ ተመልክቶም ሰፋ ያለ ዘመቻና ትምህርት አስፈላጊ ነው ብሏል።

ረቂቅ ህጉ በያዝነው አመት ታህሳስ ወር የሚቀርብ ሲሆን የጤና ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን "የድንግልና ማረጋገጫ ሰርቲፊኬት" የሚጠይቁ ቤተሰቦችን ወይም እጮኛዎችንም የሚቀጣ ህግ ማካተት አለበትም ተብሏል።

በርካታ ሙስሊም ሴቶች ከጋብቻ በፊት ወሲብ በመፈፀማቸው መገደልን ጨምሮ በርካታ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል።