የልጁን 'ድንግልና' በየዓመቱ የሚያስመረምረው ራፐር ውዝግብ አስነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታዋቂው አሜሪካዊ አቀንቃኝ ቲአይ የ18 ዓመት ልጁን በየዓመቱ የማህጸን ሐኪም ጋር እየወሰደ 'ድንግልና' ዋ መኖር አለመኖሩን እንደሚያረጋግጥ ከተናገረ በኋላ ተቃውሞና ውዝግብን እያስተናገደ ነው።
ራፐሩ ጨምሮም ምርመራውን ያደረገውን ዶክተር "ውጤቱን በፍጥነት ነበር" የሰጠኝ ሲል አድናቆቱን ገልጿል።
ይህንን ተከትሎም የኒው ዮርክ ግዛት ሕግ አውጪዎች፤ ሴቶች ቀደም ብሎ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽመው እንደሆነ ለማወቅ የሚደረገው የ 'ድንግልና' ምርመራ እንዲከለከል ጥሪ እያቀረቡ ነው።
ጾታዊ ጥቃት ነው
ምርመራው እንዳይደረግ የሚከለክለው ሕግ እንዲወጣ ከሚጥሩት የኒው ዮርክ ምክር ቤት አባላት መካከል የዲሞክራቲክ ፓርቲ ወኪል የሆኑት ሚሼል ሶላጅስ "ድርጊቱ በሴቶች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶች መካከል አንደኛው ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
"ቲአይ በሴት ልጁ ላይ ያስደረገው የ 'ድንግልና' ምርመራና የሰጠው አስተያየት ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው። በዚህም ድርጊቱ ሴቶችን እንደ ቁስ የሚቆጥር የተሳሳተ መልዕክት አስተላልፏል" ብለዋል የምክር ቤት አባሏ።
እንዲወጣ የተጠየቀውን ሕግ የሚደግፍ ተመሳሳይ ረቂቅ ለግዛቲቱ ምክር ቤት ቀርቦ ደንቦችን የሚመረምረው ኮሚቴ እንዲወያይበት እንደሚደረግ ይጠበቃል።
ሕጉ ምን ይዟል?
ሕጉ ተቀባይነት አግኝቶ ከጸደቀ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውም አይነት የ 'ድንግልና' ምርመራ ሕገ ወጥ የሚደረግ ሲሆን፤ ምርመራውን ፈጽመው የተገኙ ሐኪሞችም የሥራ ፈቃዳቸው እንዲሰረዝ የሚያደርግ እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
በተጨማሪም ምርመራውን የፈጸሙ ሐኪሞች ላይ ቅጣትና የወንጀል ክስ የሚቀርብባቸው ሲሆን፤ ምርመራው ከህክምና ተቋም ውጪ ከተከናወነ ደግሞ ድርጊቱ እንደ ወሲባዊ ጥቃት ይቆጠራል።
በአሁኑ ወቅት 'ድንግልና' ምርመራን በተመለከተ በመላዋ አሜሪካም ሆነ በየትኛውም ግዛት ውስጥ የሚከለክል ሕግ የለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'ምርመራው አስፈላጊ አይደለም'
'ድንግልና' ምርምራ ቢያንስ 20 በሚሆኑ አገራት ውስጥ የሚፈጸም ሲሆን፤ የዓለም የጤና ድርጅት ግን ድርጊቱ ምንም አይነት የጤና ጠቀሜታ የሌለው ከመሆኑ ባሻገር በአብዛኛው በሴቶች ላይ ህመምንና ስቃይን የሚያስከትል አዋራጅ ተግባር ነው ይላል።
የጤና ባለሙያዎች ድርጊቱን ሳይንሳዊ ያልሆነ፣ ጎጂና የሴቶችን ሰብአዊ መብት የሚጋፋ ከመሆኑ ባሻገር ጥቅም አልባ ነው ይላሉ። አክለውም በምርመራው 'ድንግልና' መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ አይቻልም፤ ምርመራውም ጎጂ አካላዊና አዕምሯዊ ጉዳትን የሚያስከትል ውጤት ሊኖረው ይችላል።
የዓለም የጤና ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብትና የሴቶች ተቋማት ድርጊቱን "በህክምና አስፈላጊ ያልሆነ" በሚል በዓለም ዙሪያ ክልከላ እንዲደረግበት ጥሪ አቅርበዋል።
ዓመታዊ 'ድንግልና'ምርመራ
ምርመራው በአባቷ አማካይነት እንዲደረግባት የተገደደችው የራፕ ሙዚቀኛው ቲአይ ሴት ልጅ፣ ዴይጃህ ሃሪስ ጉዳዩ ይፋ ከተደረገ በኋላ በተለያዩ ማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃኖች ላይ አባቷን መከተል አቁማ እራሷን እንዳራቀች ተዘግቧል።
የ39 ዓመቱ ቲአይ ትክክለኛ ስሙ ክሊፎርድ ሃሪስ ሲሆን፤ ሦስት ግራሚ ሽልማቶችን አግኝቷል። በልጁ ላይ ያስደረገውን የ 'ድንግልና' ምርመራን በተመለተ አወዛጋቢውን ነገር የተናገረው በአንድ የፖድካስት ስርጭት ላይ ቀርቦ ነው።
ዘፋኙ በውይይቱ ላይ ለልጆቹ ስለ ጾታዊ ጉዳዮች የሚሰጠውን ትምህርት በተመለከተ ተጠይቆ ሲመልስ "ግልጽ የሆነ ውይይት ብቻ ሳይሆን በየዓመቱ ሴት ልጄን ሃኪም ጋር በመውሰድ 'ድንግልና' አስመረምራለሁ። አብሪያት ነው የምሄደው 18 ዓመቷ ነው አስካሁን ምንም ለውጥ የለም" ብሏል።
ባለሙያዎች የሴቶች 'ድንግልና' መለያ ነው ተብሎ የሚነገርለት ተፈጥሯዊው ስስ አካል [ሃይመን] ከግብረ ሥጋ ግንኙነት ውጪ በሆኑ አጋጣሚዎች ሊጠፋ እንደሚችል ይናገራሉ።
ዘፋኙ እንዳለው ዶክተሩ ብስክሌትና ፈረስ በመጋለብ፣ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በሌሎች ከባድ ሥራዎች ሳቢያ 'ድንግልና' ሊጠፋ እንደሚችል ቢነግረውም "የተባሉትን ከባድ እንቅስቃሴዎችን አድርጋ አታውቅም። ስለዚህ ምርመራውን አድርጉና በቶሎ ውጤቱን ስጡኝ" እንዳለቸው ተናግሯል።
በተጨማሪም ሁሉም ሴቶች ሲወለዱ 'ድንግልና' ን ያመለክታል የተባለው ስስ አካል በተፈጥሮ ይኖራቸዋል ተብሎ እንደማይጠበቅ አሜሪካው ውስጥ የሚገኝ አንድ ኮሌጅ ጠቅሷል።
ከውዝግብ የማይርቀው
ከሦስት ሴቶች ስድስት ልጆችን የወለደው ቲአይ በተለያዩ ጎዳዮች ላይ ውዝግቦችን በመቀስቀስ በኩል አዲስ እንዳልሆነ ዘገባዎች ያመለክታሉ።
አቀንቃኙ ከዚህ ቀደም የጦር መሳሪያዎችንና ዕጾችን ይዞ በመገኘት ተይዞ ሁለት ጊዜ ለእስር ተዳርጓል።
ቲኒ ተብላ የምትታወቀው አሜሪካዊት ዘፋኝና የሙዚቃ ጸሐፊ የሆነችው ባለቤቱ፤ ታማኝ ባለመሆንና አክብሮት የጎደለው ነው በሚል ክስ አቅርባበት ነበር።
ከአራት ዓመት በፊት ሒላሪ ክሊንተን ለምርጫ በተወዳደሩበት ጊዜ በእጩዋ ላይ ተገቢ ያልሆነ አስተያየት በመሰንዘሩ ከፍተኛ ውዝግብና ውግዘት ገጥሞት ነበር።












