ከፓሪሱ ጥቃት ጋር በተያያዘ 7 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በፓሪስ ከተማ ከቀድሞ የቻርሊ ሄብዶ መጽሔት ቢሮ አቅራቢያ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ 7 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ።
ትናንት አንድ ግለሰብ በስጋ መከትከቻ ትልቅ ቢላ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር።
ትውልደ ፓኪስታናዊ የሆነው እና ድርጊቱን ሳይፈጽም አይቀርም የተባለው የ18 ዓመት ወጣት የወንጀል ድርጊቱ በተፈጸመበት ቦታ ላይ በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ከወጣቱ በተጨማሪ 6 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንደሚገኙ እና ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነ የፈረንሳይ ፖሊስ አስታውቋል።
ጥቃቱ የሽብር ጥቃት ተደርጎ ምርመራው እየተከናወነ እንደሆነ የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስትሩ ጄራልድ ዳርማኒን “ይህ በግልጽ ጽንፈኛ ኢስላማዊ ሽብርተኝነት ነው” ካሉ በኋላ፤ ፖሊስ በቀድሞ መጽሔት ቢሮ አካባቢ የነበረውን የጸጥታ ስጋት በቸልታ አልፎታል ብለዋል።
እአአ 2015 ላይ ሁለት ሙስሊም የፈረንሳይ ዜጎች የቻርሊ ሄብዶ መጽሔት ቢሮን ሰብረው በመግባት በሰራተኞቹ ላይ ተኩስ ከፍተው ሰራተኞቹን ጨምሮ በጠቅላላው 12 ሰዎች ገድለው ነበር።
ከዚያም ከፖሊስ ሲሸሹ የነበሩት ጥቃት አድራሾቹ በፖሊስ ተገድለዋል።
ቧልት ቀመስ የሆነው ቻርሊ ሄብዶ በቀኝ አክራሪዎች ላይ በመዘባበት በርካታ ስራዎችን የሚያቀርብ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ በካቶሊክ፣ አይሁድና እስልምና እምነቶችም ላይ ፌዝና ቀልድ ማቅረቡ አወዛጋቢ አድርጎታል።
በአንደኛው ካርቱን ላይ ነብዩ መሐመድ በተርባን ጥምጥም ፈንታ ቦምብ ጭንቅላታቸው ላይ አድገው ይታያል።
ከአምስት ዓመታት በፊት በመጽሔቱ ሰራተኞች ላይ ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ መጽሔቱ የሚዘጋጀው ስፍራው ከማይታወቅ ቦታ ነው።

የፎቶው ባለመብት, EVN/DAVID COHEN
ትናንት የፈጠረው ምንድነው?
የአገሪቱ ባለስልጣናት እንደሚሉት ትናንት ከሰዓት ጥቃት የደረሰባቸው ሁለቱ ግለሰቦች የአንድ የዜና ወኪል ሰራተኞች ሲሆኑ ከመስሪያ ቤታቸው ደጃፍ ላይ ሆነው ሲጃራ እያጨሱ ነበር።
“የሰዎች ጩኸት ሰምቼ ወደ መስኮቱ ጠጋ ብዬ ስመለከት ትልቅ ቢላ የያዘ ሰው ሁለት ባልደረቦቼን ሲያባርር ተመለከትኩ” ብሏል የዜና ወኪሎቹ ባልደረባ።
ጥቃቱ የደረሰባቸው ሁለቱ ግለሰቦች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ተጠርጣሪው ወንጀሉ በተፈጸመበት ቦታ በቁጥጥር ሥር ከዋላ በኋላ ከሚኖርበት ቤትም አምስት ፓኪስታናውያን ተይዘዋል።














