ኢትዮጵያ፡ ማንነትን ማሳያ የሆኑት የባህል አልባሳት

የፎቶው ባለመብት, Elias Badhaasaa
በርካቶች በባሕል አልባሳቶቻቸው ተውበው ለመታየት ዳተኛ የነበሩበት ዘመን ሩቅ አይደለም። ለዚህ ደግሞ የተለያየ ምክንያት ቢሰጡም ዋናው ግን አልባሳቶቹ ለሥራ ምቹ ተደርገው አለመሸመናቸው አንዱ ነው።
የኦሮሞ ባሕል አልባሳትም ተዘውትረው ሲለበሱ ከማይታዩ በርካታ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች አልባሳት መካከል ውስጥ ነበሩ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የብሔር ማንነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማእከላዊ ማጠንጠኛ እየሆነ ሲመጣ እና የፋሽን ኢንዱስትሪው አልባሳቱን በተለያየ ስልት ሸምኖ ሲያቀርብ በርካቶች እንደ ፍላጎቶቻቸውና እነደምርጫቸው መልበስ ጀምረዋል።
በቅርቡም በዓመታዊው የኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ በእነዚህ ባሕል አልባሳት ተውበው የታዩ የተለያዩ ግለሰቦች ተስተውለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Elias Badhaasaa
አልባሳቱን በማዘመን ረገድ ከሚጠቀሱት መካከል አንቲኮ ዲዛይን አንዱ ነው።
ቀይ፣ ጥቁርና ነጭ ቀለማት ያላቸው አልባሳት በአንድ ላይ በህብር ሆነው ሲመጡ በፍጥነት ለኢትዮጵያዊ ተመልካች የኦሮሞ ባህል አልባሳት ቀለማትን ምስል ይከስታሉ። እነዚህ ሶስት ቀለማት በተለያዩ አልባሳት ላይ በአንድ ላይ ተጋምደውና ውበት ሰርተው ይገኛሉ።
የባሕል አልባሳቱን ለማጀብ የሚያገለግለው ሌላው ደግሞ ሲንቄ የተሰኘው ባህላዊ በትር ነው።

የፎቶው ባለመብት, Elias Badhaasaa
እነዚህ በኩሽ ዲዛይን የተሰሩ አልባሳት ደግሞ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳት ላይ ተዘውትረው የሚታዩ ቀለማትና መስመሮችን በአዲስ መንገድ ያስቀመጡ ናቸው። እነዚህ መስመሮች በልብሱ ወርድና ቁመት ላይ በመሆን ለባሱን በቁመትና በዙሪያው ተጨማሪ ግርማ ሞገሥ እንዲላበስ ያደርጉታል።
ይህንን ምስል ያነሳው ባለሙያ ኤልያስ በሻዳ ለቢቢሲ ሲያስረዳ "የሌሎች ባሕሎች በምስል ተሰንደው ሲቀሩ አስተውላለሁ፤ የእኛ [የኦሮሞ] ግን በአግባቡ አልተሰነደም" ይላል።
"ስለዚህ ራሴን ስለምን ባህላችንን አናስተዋውቅም ስል መጠየቅ ጀመርኩ? በአፍሪካ ቀንድና ከዚያም ባሻገር እንድንታወቅ ፈለግሁ" ሲል ያክላል።

የፎቶው ባለመብት, Dagim Getachew
የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያለው ሲሆን በባሕልም እንዲሁ ዝንቅ የሆነ ማህበረሰብ ነው።
ከላይ የሚታው ምስል ሴቶች እርቦ ጭንቅላታቸው ላይ ይዘው የሚታይ ሲሆን፣ የለበሱት ቀሚስ ደግሞ የምስራቅ አገሪቱ ክፍል የሚኙትን የሀረር ኦሮሞዎች ይወክላል።
በርግጥ ቀሚሱ እና ጭንቅላታቸው ላይ ያስቀመጡት እርቦ የምስራቁን የአገሪቱ ክፍል የሚወክል ቢሆንም ወገባቸው ላይ ያሰሩት መቀነት ግን የደቡብ የአገሪቱን ክፍል ባህል እነደሚወክል ዩሚዮ የባህል አልባሳት ይናገራል።
የኢሬቻ ፌስቲቫል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉበት በዓል ቢሆንም፣ በዚህ ዓመት ግን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት በውስን ሰዎች ብቻ እንዲከበር ተደርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Dagim Getachew
በኦሮሞ ባህል አልባሳት ላይ በተደጋጋሚ የሚስተዋለው የኦዳ ዛፍ ምልክት ነው። ይህ የኦዳ ዛፍ ምልክት በቀሚሶች፣ ሱሪዎችና ኮቶች ላይ በሕትመት መልክ ገብቶ ተጨማሪ ፈርጥ በመሆን ሲያገገለግልም ይስተዋላል።

የፎቶው ባለመብት, Dagim Getachew
ከአራት ዓመታት በፊት በቢሾፍቱ የኢሬቻ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ በነበረ ተቃውሞ ፖሊስና ተቃዋሚ ሰልፈኞች አለመግባበት ተፈጥሮ በደረሰ መረጋገጥ ቢያንስ 55 ሰዎች ሞተዋል።
የመብት ተሟጋች ድርጅቶች የሟቾቹን ቁጥር ወደ መቶዎች ያስጠጉታል።
በተደጋጋሚ የኦሮሞ ወጣቶች በፖለቲካ እና ምጣኔ ሀብት መገለላቸውን በማንሳት ተቃውሞ ካሰሙ በኋላ ለውጥ ተደርጎ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መጥተዋል። ነገር ግን አሁንም ውጥረቱ በአንዳንድ ሥፍራዎች ይታያል።

የፎቶው ባለመብት, 9adhii
ስለ ኦሮሞ ሕዝብ መብት የሚከራከሩ ወገኖች አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ይገኛሉ።
ይህ ምስል የተወሰደውም በአሜሪካዋ የሚኒሶታ ግዛት በሬድፎክስ አፓረል (RedFox Apparel) ነው።

የፎቶው ባለመብት, Senakebeki Girma
የ27 ዓመቷ ዲዛይነር ሴናክቤኪ ግርማ በኦሮሞ ባህል አልባሳት ላይ ያየችውን ለውጥ "ማይታመን" ስትል ትገልፀዋለች።
"ሰዎች የበለጠ በማንነታቸው እየኮሩ መምጣት ጀምረዋል' ስትልም ታክላለች።
እነዚህ ባህል አልባሳትም ከበዓላት ቀናት ውጪ ሰርክ የሚለበሱ እንዲሆኑ ምኞቷ ነው።
All images subject to copyright.















