በፈረንሳይ አንገቱን ለተቀላው መምህር በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ድጋፋቸውን አሳዩ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በመላው ፈረንሳይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንገቱን ተቀልቶ ለተገደለው መምህር ድጋፋቸውን ለመስጠት አደባባይ ወጡ።
ሳሙኤል ፓቲይ የተባለው መምህር በክፍሉ ውስጥ አወዛጋቢ የነብዩ መሐመድ የካርቱን ስዕሎችን ለተማሪዎቹ ካሳየ በኋላ ከትናንት በስቲያ አንድ የ18 ዓመት ወጣት ትምህርት ቤት አቅራቢያ አንገቱን መቅላቱ ይታወሳል።
ሳሙኤል ፓቲይ የሚያስተምርበት ትምህርት ቤት መምህራንን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች “እኔም መምህር ነኝ” “እኛ ፈረንሳይ ነኝ” የሚሉ መፈክሮችን ይዘው አደባባይ ወጥተዋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን መምህሩ አንገቱ ተቀልቶ የተገደለው "በእስላማዊ የሽብር ጥቃት ነው" ብለው ነበር። ጥቃት ያደረሰው ሩሲያ ውስጥ የተወለደው ወጣት አብዱላክ ሲሆን ጥቃቱን ባደረሰበት ስፍራ በፖሊስ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል።
ከዚህ ጥቃት ጋር በተያያዘ የፈረንሳይ ፖሊስ 11 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ይፋ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል 4ቱ ከጥቃት አድራሹ ጋር የቅርብ ዝምድና የነበራቸው ናቸው።
ለ47 ዓመቱ መምህር ድጋፋቸውን ለመግለጽ አደባባይ ከወጡት መካከል “ለሪፐብሊኩ ጠላቶች ትዕግስት አያስፈልግም” “እኔም መምህር ነኝ፤ ፓቲይ አንተን አስብሃለሁ” የሚሉ መፈክሮችም ታይታዋል።
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚንሰትር ጄን ካስቴክስ በትዊተር ገጻቸው ላይ “እኛ ፈንሳይ ነን። . . . አታሸብሩንም” ሲሉ ጽፈዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
አርብ ዕለት የሆነው ምን ነበር?
ጥቃቱ አድራሹ ከሚኖርበት ከተማ 110 ኪ.ሜትር ተጉዞ ትምህር ቤቱ ጋር ከደረሰ በኋላ ሳሙኤል ፓቲይ የተባለው መምህር የትኛው እንደሆነ እንዲጠቁሙት ተማሪዎችን ጠይቋል።
ጥቃት አድራሹ ከዚህ ቀደም ከትምህር ቤቱ ጋርም ይሁን ከመምህሩ ጋር ግንኙነት አልነበረውም። መምህሩ ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤቱ ሲጓዝ ጥቃት አድራሹ ሲከተለው ነበር።
ከዚያም በቢላዋ ጭንቅላቱን መትቶ ከጣለው በኋላ አንገቱን ቀልቶታል። ፖሊስ እንደሚለው ጥቃቱን ሲያደርስ "አላሁ አክበር" ሲል የአይን እማኞች ሰምተውታል።
ጥቃቱን ካደረሰ በኋላ ለመሰወር ቢጥርም ጥሪ የደረሰው ፖሊስ በፍጥነት በስፍራው ተገኝቷል። ከዚያም 12 ጊዜ በጥይት ተመትቶ ተገድሏል። ፖሊስ 30 ሴንቲ ሜትር የሚረዝም ቢላዋ ከጥቃት አድራሹ ጎን ማግኘቱንም አስታውቋል።
በፈረንሳይ መሰል ጥቃት ሲፈጸም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሶስት ሳምንት በፊት ትውልደ ፓኪስታናዊ የ18 ዓመት ወጣት በስጋ መከትከቻ ትልቅ ቢላ ሁለት ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር።
እአአ 2015 ላይ ሁለት ሙስሊም የፈረንሳይ ዜጎች የቻርሊ ሄብዶ መጽሔት ቢሮን ሰብረው በመግባት በሰራተኞቹ ላይ ተኩስ ከፍተው ሰራተኞቹን ጨምሮ በጠቅላላው 12 ሰዎች መግደላቸው የሚታወስ ነው።














