ሳይንስ፡ ፅንስን ከማህፀን ውጪ በማሳደግ ፈር የቀደደችው ሳይንቲስት

ሚሪያም መንኪን

የፎቶው ባለመብት, Emmanuel Lafont

ፅንስን ከማህፀን ውጭ እንዲዳብር በማድረግ ኢንትሮ ፈርትላይዜሽን የሚባለውን የሥነ ተዋልዶ ዘዴ ለዓለም ያስተዋወቀች የመጀመሪያ ሴት ሳይንቲስት ብትሆንም ስሟን የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው።

ወቅቱ በጎርጎሳውያኑ 1944 ነበር፤ የአርባ ሦስት ዓመቷ የላብራቶሪ ቴክኒሺያን ሚሪያም መንኪን የስምንት ወር ልጇን ስታባብል እንቅልፍ በአይኗ አይዞርም ነበር። ልጇ ጥርስ እያወጣች በመሆኑ ህመሙ እየጠዘጠዛት ህፃኗ መተኛት በመቸገሯ ነው እናቷን ያስቸገረቻት።

ሚሪያም ቀደም ባሉት ስድስት ዓመታት እንዳደረገችው ሁሉ ሲነጋ ወደ ላብራቶሪ አቀናች።

ዕለቱ ረቡዕ ነበር፤ እንደ ቀድሞው የሴት እንቁላልና የወንዱን ዘር ዘርጋ ባለ የብርጭቆ ሳህን ላይ አዋሃደችውና አንድ እንዲሆኑም ጸለየች።

የሃርቫርድ የሥነ ተዋልዶ ባለሙያው ጆን ሮክ እንደሚለው የሚርያም ሙከራ ከማህፀን ውጭ እንቁላሉና ዘሩ ተዋሕዶ ፅንስ የሚሆንበትን ለማየት ነበር። መውለድ ላልቻሉ መካን ሰዎችም መፍትሄ የተጠነሰሰውም በዚህ ወቅት ነው ይላል።

በጎርጎሳውያኑ 1944 ከማሕፀን ውጭ የዳበረው ፅንስ

የፎቶው ባለመብት, Center for the History of Medicine, Harvard

የምስሉ መግለጫ, በጎርጎሳውያኑ 1944 ከማሕፀን ውጭ የዳበረው ፅንስ

አብዛኛውን ጊዜ እንቁላሉንና የወንዱን ዘር ለሰላሳ ደቂቃ ያህል አንድ ላይ በማድረግ ውህደት እንዲፈጥሩ ትጠብቃለች።

በዚህች ቀን ግን እንዲያ አልነበረም።

ከዓመታት በኋላ ምን እንዳነሳሳት ተጠይቃ በተናገረችበት ወቅት "በጣም ድካም ተጫጭኖኝ ነበር፤ እንቅልፍ እንቅልፍ እያለኝ የነበረ መሆኑንም አስታውሳለሁ። የወንዱ ዘር በእንቁላሉ አካባቢ የሚያደርገውን ምልልስ በማይክሮስኮፑ እያየሁ ሰዓቱን ማየት ዘነጋሁ። ለካ ከአንድ ሰዓት በላይ አልፏል። እናም በሌላ አነጋገር ከስድስት ዓመታት ሙከራ በኋላ የተሳካልኝ ድንገተኛ ዘዴን ፈጥሬ ሳይሆን በሥራ ላይ እንቅልፌ ስለመጣ የተፈጠረ አጋጣሚ ነው" ብላለች።

አርብ ዕለትም ወደ ላብራቶሪው ስትመጣ ተአምር የሆነውን ክስተት ተመለከተች። ህዋሳቱ አንድ ላይ ተዋህደው የብልቃጥ ፅንስ ምን ሊመስል እንደሚችልም አየች።

የሚሪያም ግኝት በሥነ ተዋልዶ ቴክኖሎጂ ላይ አብዮትን በማምጣት መውለድ ላልቻሉ ሴቶች ፅንስ በብልቃጥ ውስጥ እንዲዳብር እንዲሁም ሳይንቲስቶች የሰውን ልጅ ጥንስስ ከጅምሩ እንዲመለከቱ ፈር ቀዷል።

በጎርጎሳውያኑ 1978ም የመጀመሪያዋ የብልቃጥ ልጅ ሊውስ ብራውን በኢንቪትሮ ፈርቲላይዜሽን መንገድ ህይወት ዘራች።

ሚርያም ከአስራ ስምንት በላይ ሳይንሳዊ ፅሁፎችን በግሏ እንዲሁም በጋራ አበርክታለች። ከእነዚህም መካከል በመጀመሪያው ከማህፀን ውጪ የሚደረግ ፅንስን በተመለከተ ሁለት ታሪካዊ የሚባሉ ሪፖርቶችንም በሳይንስ ጆርናል ላይ አሳትማለች። ነገር ግን አብሯት ፅሁፉን እንደፃፈው ጆን ሮክ ምንም አይነት እውቅና አልተቸራትም።

በሩትገርስ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁርና 'ዘ ፈርቲሊቲ ዶክተር፤ ጆን ሮክ ኤንድ ዘ ሪፕሮደክቲቨ ሪቮሊዩሽን' የፃፉት ማርጋሬት ማርሽ ሚርያም ለጆን ሮክ ከረዳት በላይ እንደነበረች ይናገራሉ።

"ጆን ሮክ የህክምና ዶክተር ነው የነበረው። ሚርያም ግን ሳይንቲስት ነበረች። የአዕምሮዋ ምጡቅነት፣ አስተሳሰቧ እንዲሁም እንደ ሳይንቲስት ፕሮቶኮሎች ያላቸውን ጠቀሜታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተከትላለች" ብለዋል።

ደይሊ ሜይልን እያነበበች ያለች ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ትውልድና እድገት

ሳይንቲስቷ ሚርያም በጎርጎሳውያኑ ነሐሴ 8/1901 በላቲቪያ ዋና ከተማ ሪጋ ተወለደች።

ገና በጨቅላነቷ ነው ቤተሰቦቿ ወደ አሜሪካ የተሰደዱት። አባቷም ዶክተር ሆነው አገልግለዋል።

በሳይንሱ ላይ ከፍተኛ ዝንባሌ በህፃንነቷ ያሳየችው ሚርያም ከኮርኔል ዩኒቨርስቲ በህዋሳት ጥናት እና በሰው ልጅ አካላት አፈጣጠር ዙሪያ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በ1922 አገኘች።

በቀጣዩም ዓመት በዘረ መል ጥናት ከኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ የማስተርስ ዲግሪዋን ሰርታለች። በኒውዮርክም ባዮሎጂ እና የአካላት ጥናትን ትምህርቶችን በኒውዮርክ አስተምራለች።

የህክምና ትምህርቷን ለመከታተል በወሰነችበት ወቅትም የመጀመሪያው መሰናክል አጋጠማት። ከፍተኛ ስም ያላቸው ሁለት ዩኒቨርስቲዎች አልቀበልም አሏት። ይህም የሆነው ሴት በመሆኗ ነበር።

በወቅቱ ሴቶችን ተቀብለው የሚያስተምሩ በጣም ጥቂት ዩኒቨርስቲዎች ሲሆኑ እነሱም ጥብቅ ኮታ ነበራቸው።

ትዳር

ትምህርቱንም ወደ ጎን በመተው የቀድሞ የክፍል ጓደኛዋና በወቅቱም በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የህክምና ተማሪ የሆነውን ቫሊ መንኪንን አገባች።

ሚሪያም ባሏን ጥናቱን እስኪያጠናቅቅ ለመደገፍም በፀሐፊነት ተቀጥራ ትሰራ ነበር።

ከአካዳሚው ጋር ቀረብ ብላም በባክቴሪያዎች ላይ እንዲሁም ከሥነ ተዋልዶ ጋር የተያየዙ ኮርሶችን ወስዳለች። ባለቤቷም በሚያደርገው ሙከራም ላይ በላብራቶሪ ሥራዎች ትደግፈው ነበር።

በዚህም ወቅት ነበር የሃርቫርዱን የባዮሎጂ ምሁር ግሪጎሪ ፒንከስ የተዋወቀችው። ግሪጎሪ ከጆን ሮክም ጋር ፈር ቀዳጅ የተባለውን የእርግዝና መከላከያን ሰርቷል።

ግሪጎሪ ከፒቱታሪ ከተባለው ዕጢ ላይ ሁለት መሰረታዊ ሆርሞኖችን በመውሰድ ሴት ጥንቸሎችን እንድትወጋቸው ትዕዛዝ ይሰጣታል።

ይህም ጥንቸሎቹን ተጨማሪ እንቁላሎችን ለውፃት (ovulate) እንዲያዘጋጁ ያስችል እንደሆነም ለማየት ነበር።

የፅንስ ማዳበር ሙከራዎች

በዚህም ወቅትም ነበር የሥነ ተዋልዶ ስፔሻሊስት ነኝ በሚል ጆን ሮክ የግሪጎሪን ጥናት ወደ ክሊኒክ ምርምር ለማድረግ ሃሳብ ያቀረበው።

በየቀኑ ማክሰኞ ጥዋት ሁለት ሰዓትም ሚርያም ማሳቹስተስ፣ ቦስተን በሚገኘው ለሴቶች የነፃ ህክምና አገልግሎት በሚሰጠው ሆስፒታል ቀዶ ጥገና በርም ላይ ታንዣብብ ነበር።

እድለኛ ከሆነችም ጆን ሮክ ከህመምተኞች ላይ በቀዶ ጥገና ያስወገደውን የእንቁልጢ አካል (የእንቁላል ከረጢት) ይሰጣት ነበር። እንደምታስታውሰውም በጣም ደቃቃ ከመሆናቸውም አንፃር "ትንሽዬ የኦቾሎኒ ፍሬ ያክላሉ" ትላለች።

ከዚያም እንቁልጢውን በመውሰድ ትቀደውና እንቁላል ትፈልጋለች።

በየሳምንቱም ማክሰኞ እንቁላል ትፈልጋለች፣ ረቡዕ ከወንዴው ዘር ጋር ትቀላቅለዋለች፣ ሐሙስ ትፀልያለች፣ አርብ ደግሞ ውጤቱን ትከታተላለች።

ስድስት መት በሙከራ

በየሳምንቱ አርብም ውህዱን የምታስቀምጥበትን መቀፍቀፊያውን ስትመለከት የምታየው ነገር ቢኖር አንድ ህዋስ ብቻ ነው - ያልዳበረ እንቁላልና የሞቱ በርካታ የወንድ ዘሮች። ይህንንም ሙከራ ለስድስት ዓመታት ያህል ለ138 ጊዜ ያህል አከናውናለች።

የ1944 የካቲት ወር እድለኛ አርብ ግን ሁኔታዎችን ቀየረች። መቀፍቀፉፊያውን ስታይ ያልጠበቀችው ውህድ ተፈጥሮ አየች፤ በድንጋጤና በደስታ ተውጣም የጆን ሮክን ስም ጠራች።

ጆን ሮክ ብቻ ሳይሆን ላብራቶሪው ይህንን ተአምር ለመመልከት በመጡ ሰዎች ተሞላች "ሁሉም ይሄንን ከማህፀን ውጪ የተፈጠረውን ፅንስና የሰው ልጅ ጥንስስ ለማየት እየተሯሯጡ መጡ" ትላለች።

ሚርያም በኋላም እንደፃፈችው "ይህንን ድንቅ የሆነ ግኝት፣ ፅንስ ከአይኔ ለደቂቃም ቢሆን ዘወር እንዲል አልፈለግኩም። ለስድስት ዓመታት ያህል የደከምኩበት፤ ብዙ ያልተሳኩ ህልሞችና ቀናት ማስታወሻዬ ነው" በሚል አስፍራለች።

ይህ የዳበረ ዕንቁላልም እንዳይበላሽ በሚል ፈሳሽ ጠብ እያደረገች ነበር። ለሰዓታትም ያህል በእንቁላሉ ፈሳሽ ጠብ ከማድረግ ወደኋላ አላለችም። ሲርባትም በአንድ እጇ ሳንድዊች እየበላች በሌላ እጇ ሳታቋርጥ ጠብ እያደረገች ሙሉ ሌሊቱን አደረች።

እንዲህ ተግታ ብትሰራም የመጀመሪያዋ ሙከራ ግን አልተሳካም። እሷ እንደምትለው "በብልቃጥ ውስጥ የተከናወነ የመጀመሪያ የፅንስ መጨንገፍ" በማለትም በፀፀት ታስታውሰዋለች። ከዚያ በኋላ ግን ሙከራዋን ሦስት ጊዜ ሞክራዋለች።

በዚህም መካከል ድንገትም ያልተጠበቀ ነገር ተከሰተ። ባለቤቷ ሥራውን አጣ። እናም ተከትላው በሰሜን ካሮላይና ወደሚገኘው ዱክ ዩኒቨርስቲ አቀናች። በዚህ ዩኒቨርስቲ ፅንስን ከማህፀን ውጪ ማዳበር እንደ ትልቅ ነውር የሚታይ በመሆኑ ሥራዋን መቀጠል አልቻለችም።

ያለ ሚርያምም አስተዋፅኦ በቦስተን የሚገኘው በብልቃጥ ውስጥ የሚደረገው ምርምር ፍሬ ሳያፈራ ቀጥ አለ። የጆን ሮክ ሌሎች ረዳቶች ከማሕፀን ውጪ ፅንስ ማዳበር አልቻሉም።

የኑሮ ትግል

ላብራቶሪ ማግኘትም ባትችልም ከሩቅ ሆና ከጆን ሮክ ጋር አብራ መስራቷን ቀጠለች።

በጎርጎሳውያኑ 1948ም የተገኘውን ግኝት ሚርያም መሪ ፀሐፊ በመሆን ሙሉ ሪፖርቱን በጋራ አሳተሙ።

ነገር ግን ምርምሯን ለመቀጠል መሰናክሎች ገጠሟት።

ለዓመታት ባለቤቷን ልትፈታ ብታስብም በይደር አቆይታው የነበረ ቢሆንም ችግሮች መጥናት ጀመሩ።

ገንዘብ ይከለክላት ነበር ልጆቿ ሉሲና ገብርኤል ፊትም እደበድብሻለሁ እያለ ያስፈራራት ነበር። የባለቤቷን ባህርይ መቋቋም ሲያቅታትም ቤቷን ትታው ወጣች።

ነገር ግን ህይወት ቀላል አልነበረም፤ ብቸኛ እናትም ሆና ልጆቿን ማሳደግና ሌሎች ወጪዎችንም መሸፈን ነበረባት።

ወደ ቦስተን መልስ

በ1950ዎቹ ሚርያም የሚጥል በሽታ ያለባትን ልጇን የተለየ ፍላጎት ትምህርት ቤት ለማስገባት በሚል ወደ ቦስተን ተመለሰች።

በቦስተንም ከቀድሞ የላብራቶሪ አጋሯ ጆን ሮክ ጋር ተገናኘች። ነገር ግን ባለፉት አስር ዓመት ብዙ ነገር ተቀይሮ ጠበቃት።

የሥነ ተዋልዶ ዋና ትኩረቱ ልጆች እንዲወለዱ መስራት ሳይሆን በርካታ ልጆች እንዳይወለዱ መከላከል ላይ ነበር።

ጆን ሮክም ዋና ትኩረቱንም ለሴቶች በቀላሉና ምቹ በሆነ ሁኔታ የሚወስዱትን የእርግዝና መከላከያን መስራት ነበር።

የየእርግዝና መከላከያን መጠቀምም በጎርጎሳውያኑ 1960 ፈቃድ አገኘ።

ሚሪያም መንኪንና ልጇ ሉሲ

የፎቶው ባለመብት, Center for the History of Medicine, Harvard

የምስሉ መግለጫ, ሚሪያም መንኪንና ልጇ ሉሲ

ጆን ሮክ ትኩረቱን በሙሉ በሙከራው ውጤት ላይ አድርጎ ሲሰራ ሚርያም ደግሞ ከጀርባ ሆና "እንደ ረዳት" ትሰራ ነበር።

የተለያዩ የምርምር ርዕሶችን በማምጣትም በጃፓን የሚደረገውን የወንድ ዘርን በማቀዝቀዝ መካንነትን ለማስቀረት የሚሰራው ሥራም ላይ ፅሁፎችን አበርክታለች።

የሴቶች የወር አበባ ዑደት በብርሃን መረጋጋት ይችል ይሆ? እንዲሁም ጠበቅ ያሉ የወንድ ሙታንታዎች በወንዶች ላይ ጊዜያዊ መካንነት ያስከትላሉ በሚሉ ርዕሶችም ላይ ሳይንሳዊ ፅሁፎችን ፅፋለች።

ምንም እንኳን እነዚህ ርዕሶች መጀመሪያ ትመራመርበት ከነበረው ፅንስን ከማህፀን ውጪ ማዳበር ራቅ ያለ ቢመስልም የመጨረሻ ግቡ ግን ተመሳሳይ ነው። እንደ ጆን ሮክ በሥነ ተዋልዶ ላይ ያሉ ምስጢራዊ ነገሮችን የሳይንስን ልህቀት በመጠቀም ለመፍታት ሞክራለች።

ሚሪያም መንኪን ህይወቷ በተለየ አቅጣጫ ቢሄድ ለምሳሌ ጨቋኝ ባለቤቷን ባታገባ፣ ዶክትሬቷን ለመማር እድል ብታገኝ ከዚህ በበለጠ ማበርከት ትችል ነበር የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ባይቻልም፤ ሳይንቲስቷ የነበራትን የአዕምሮ ምጥቀት በጊዜው በነበረው የሴቶች ቦታ ሊረዷት እንዳልቻሉ ማርጋሬት ይናገራሉ።