ኮሮናቫይረስ ፡ ቻይና ሰራሹ ክትባት አመርቂ የሚባል ውጤት አስመዘገበ

ክትባት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቻይና በሙከራ ላይ የሚገኘው የኮቪድ-19 ክትባት አመርቂ የሚባል ውጤት እያስገኘ ነው ተባለ።

ሆኖም ክትባቱ አመርቂ ውጤት ያስገኘው በረዥም የሙከራ ሂደት ውስጥ የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ ሳይሆን፣ መካከለኛ ምዕራፍ በሚባለው ክፍል ነው።

በዓለም ላይ በአሁኑ ጊዜ የቻይናውን ክትባት ጨምሮ በርካታ ምርምሮች እየተደረጉ ሲሆን የተወሰኑት ብቻ ወደ መጨረሻ ምዕራፍ ተሸጋግረዋል።

አንዳንዳንዶቹ ደግሞ ከወዲሁ ለሕዝብ በድፍረት መታደል ተጀምረዋል።

ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ከቻይና ሰራሽ ክትባቶች አንዱና ታዋቂ እየሆነ የመጣው በሲኖቫክ ባዮቴክ የተመረተው ሲኖቫክ ክትባት በ700 ሰዎች ላይ ተሞክሮ ሰዎቹ ይበል የሚያሰኝ ውጤት አስገኝቷል።

ክትባቱ የተሞከረባቸው ሰዎች በሽታን የመከላከያ ህዋሳቸውን አንቅቶ ቫይረሱን መመከት እንደቻለ ተደርሶበታል።

በቅርብ ጊዜ በአውሮፓና አሜሪካ በግዙፍ መድኃኒት አምራቾች እየወጡ ያሉ አዳዲስ የኮቪድ-19 ክትባቶች ከዚህ ቀደም ባልተሰማ መልኩ አመርቂ ውጤት እያስገኙ ነው።

ዓለምን ላለፉት 11 ወራት ያመሳት ተህዋሲ መጥፊያው የተቃረበ ይመስላል።

በተለይ በአሜሪካ፣ በጀርመንና በሩሲያ የተመረቱ መድኃኒቶች የስኬት ልኬታቸው 90 ከመቶና ከዚያ በላይ ሆኖ ተመዝግቧል።

የሚመረቱት የክትባት ቅንጣቶች ተህዋሲውን ተከላካይነታቸው በዚህ ደረጃ ከደረሱ በስፋት ለሕዝብ መሰራጨት የሚችሉበት ደረጃ ደርሰዋል ማለት ነው።

ነገር ግን የትኛው ክትባት ተመራጭ ይሆናል የሚለው በመከላከል የስኬት ምጣኔ ብቻ አይወሰንም። ከዚህ በሻገር መድኃኒቱን ተመራጭ እንዲሆን የሚወሰኑ ሌሎች ነገሮች አሉ።

ከእነዚህም መካከል ክትባቱ በሚኖረው የአቅርቦት ዋጋ፣ ለማምረት በሚወስደው ጊዜና ውስብስብነት፣ በአንድ ጊዜ ለአንድ ሰው የሚሰጠው የክትባት ጠብታ መጠን፣ ምርቱን ከቦታ ቦታ ለማጓጓዝ አመቺነቱ፣ በክምችት ጊዜ የሚፈልገው የቅዝቃዜ መጠን ሁሉ ከግምት ውስጥ ይገባል።

እነዚህ በሦስቱ አገሮች የተመረቱት ክትባቶች በ10 ሺዎች በሚገመቱ ሰዎች ላይ ተሞክረው ውጤት ያሳዩና የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ነው ዓለም በአንክሮ እየተከታተላቸው ያለው።

እንደተቀረው ዓለም ሁሉ ቻይናም እጅግ ስኬታማ የሚባሉ አራት ክትባቶችን እያመረተች ሲሆን ሁሉም በመጨረሻውም ምዕራፍ የደረሱና ናቸው።

በተለይ በሲኖቫክ ባዮቴክ እየተመረተ ያለው ክትባት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረስ ብቻ ሳይሆን ቻይና ፍቃደኛ ለሆኑና ፍላጎት ላላቸው ዜጎች እያደለችው ትገኛለች።

ሆኖም የምርመራ ሂደቱ ገና መቶ በመቶ አልተጠናቀቀም።

ላንሴት በሚባለው ሥመ ጥር የሳይንስ ጆርናል ላይ ይህንን ክትባት በተመለከተ የተዘገበው፤ ክትባቱ ለጊዜው በምዕራፍ አንድና ሁለት ያስመዘገበው ውጤት እንጂ አሁን ያለበትን ደረጃ አይገልጽም።

በተጨማሪም የስኬት ምጣኔው ምን ያህል እንደሆነ ይፋ አልተደረገም።

በዚህ ጆርናል ላይ ስለዚህ ቻይና ሰራሽ ክትባት ከጻፉት ተመራማሪዎች አንዱ የሆኑት ዙ ፋንቻይ እንደሚሉት፤ በምዕራፍ አንድ እና በምዕራፍ 2 ሙከራዎች 600 ሰዎች ላይ ጥናት ተደርጎ ክትባቱ ለአስቸኳይ ሕክምና አገልግሎት ላይ መዋል ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል።

ነገር ግን ወሳኝ በሚባው በምዕራፍ ሦስት ሙከራ ላይ ይህ የቻይና ክትባት ስላስገኘው ውጤት በተጨባጭ ተአማኒ ሳይነሳዊ ጆርናል ላይ የተጻፈ ዘገባ የለም።

በቻይና በአሁን ሰዓት ሙሉ በሙሉ ሊባል በተቃረበ ደረጃ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በቁጥጥር ሥር የዋለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ሆኖም ቻይና ለዜጎቿ ይህንን ክትባት መስጠቷን ቀጥላበታለች።

ክትባቱ አሁንም የምርምር ሂደቱን ያልጨረሰ ሲሆን ከቻይና ውጭ ብራዚል፣ ሩሲያ፣ ኢንዶኒዢያና ሳዑዲ አረቢያ በዜጎቻቸው ላይ እየሞከሩት ነው።

የቻይና ባለሥልጣናት እንደሚሉት እስከያዝነው ኅዳር ወር ድረስ 60 ሺህ ሰዎች ይህንን ክትባት ወስደዋል።

እስከአሁን ከተሰሙ የክትባት ዜናዎች መካከል በጀርመንና አሜሪካ ፋይዘርና ባዮንቴክ ጥምረት የተሞከረው ክትባት ተስፋ ሰጪ ሆኗል።

90 ከመቶ የስኬት ልኬት አለው የተባለው ይህ ክትባት 43 ሺህ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ድንቅ የሚባል ምላሽ አስገኝቷል።

ይህ የብስራት ዜና በተሰማ በቀናት ውስጥ ደግሞ የአሜሪካው ሞደርና ያመረተው ክትባት የስኬት ልኬቱ 95 ከመቶ ሆኖ ሌላ የብሥራት ዜና ለዓለም አሰምቷል።

ሆኖም ሁለቱም ክትባቶች ገና ሙሉ እውቅና አላገኙም።

በርካታ አገሮች ግን እነዚህ ክትባቶች እንዲሰጧቸው ወረፋ ይዘዋል።

ሩሲያ በበኩሏ የእኔ ክትባት በ16 ሺህ ሰዎች ላይ ተሞክሮ የስኬት ልኬቱ 92 ከመቶ ደርሷል ብትልም ምዕራባዊያን በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም በሚል ፊት ነስተውታል።

አሁን ዓለም በጉጉት እየጠበቀው ያለው የትኛው ክትባት መቼ ሙሉ ዕውቅና እና የምርት ፍቃድ አግኝቶ ወደ ምርት ይገባል የሚለው ነው።

ያደጉት አገራት ከፍ ያለ የስኬት ልኬት ያስመዘገቡትን ክትባቶች በአስቸኳይ ለሕዝባቸው ለማድረስ መሠረተ ልማቱን አሰናድተው እየጠበቁ ናቸው።

ድሀ አገራት ክትባቱ መቼ ይደርሳቸዋል የሚለው ግን አሁንም ያልተመለሰው ጥያቄ ነው።