ትግራይ ፡ በማይካድራ ከ600 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ

ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች
የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች

በማይካድራ ከተማ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ቢያንስ 600 ሰዎች መገደላቸውንና ቁጥሩም ከዚህ እንደሚበልጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።

ኮሚሽኑ ይህንን የገለጸው በማይካድራ ከተማ የተከሰተውን ጥቃት ተከትሎ በከተማዋና በአካባቢው ባሉ ሌሎች ስፍራዎች ያካሄደውን ምርመራ ይፋ ባደረገበት የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ ነው።

ከሁለት ሳምንት በፊት በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ክፍል በምትገኘው የማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና 'ሳምሪ' በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን መፈጸሙንም ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።

በዚህም መሰረት የአካባቢው መስተዳድርና 'ሳምሪ' በተባለው ቡድን የተፈጸመው ጥቃት፤ ግድያ፣ ጉዳትና ውድመት፤ ጠቅላላ ድርጊቱና ውጤቱ "ግፍና ጭካኔ የተሞላበት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸመ የጭፍጨፋ ወንጀል" ነው ሲል ኮሚሽኑ ገልጾታል።

ኮሚሽኑ ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት "በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል" ያመለከተ ሲሆን፤ ለዚህም ኢሰመኮ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል።

ይህ ድርጊት በማይካድራ የነበረው የሚሊሽያና የፖሊስ መዋቅር የፌዴራሉ ሠራዊትን እርምጃ ሸሽቶ አካባቢውን ለቆ ከመውጣቱ በፊት "ሳምሪ ከተባለ መደበኛ ያልሆነ የትግራይ ወጣቶች ቡድን ጋር በመተባበር በተለይ "አማሮችና ወልቃይቴዎች" ያሏቸው በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት" መፈጸማቸውን አመልክቷል።

በዚህም ቡድኑ "ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ ያገኙትን ሰው በገመድ በማነቅ፣ በስለት፣ በመጥረቢያ፣ በዱላ በመደብደብ ገድለዋል፣ የአካል ጉዳት አድርሰዋል፣ እንዲሁም ንብረት አውድመዋል" ሲል ኮሚሽኑ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ጨምሮም "'ሳምሪ' የሚባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በዚህ ከባድ ወንጀል ላይ ቢሰማራም፤ በአንጻሩ የትግራይ ብሔረሰብ ተወላጆች የሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂው ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታ ደብቀው እንዳተረፏቸው" ኢሰመኮ ምስክሮችን ጠቅሶ በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።

በተጨማሪም የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) "በማይካድራ በአነስተኛ ጽንፈኛ ቡድን የተፈጸመው በማንነት ላይ የተመሰረተ እጅግ ዘግናኝ ወንጀል ልብ ሰባሪ ቢሆንም፤ በአንጻሩ ኢትዮጵያውያን በብሔር ሳይለያዩ አንዱ የሌላው ጠባቂ ሆነው መታየታቸው ልብ ይጠግናል" በማለት ለወደፊቱ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም በዚህ ጥቃት የተጎዱ ሰዎችንና አካባቢዎችን መልሶ ከማቋቋምና በተጨማሪ፤ "በዚህ ከባድ ወንጀል በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የተሳተፉ በየደረጃው ያሉ ጥፋተኞችን በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በማይካድራ ከተማ የተፈጸመውን ጥቃት በተመለከተ ያደረገውን ምርመራ በተመለከተ ያወጣው ባለስድስት ገጽ ዘገባ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሆነ አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጥቃቱን የፈፀሙት የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው ቢሉም የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው በግድያዎቹ እጃችን የለበትም በማለት ውድቅ አድርገውታል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ውንጀላው "መሰረት" የሌላው ነው በማለት፤ ጥቃቱ በገለልተኛ ወገን ይጣራ ማለታቸው የሚታወስ ነው።

ከሳምንት በፊት ስለክስተቱ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ አምነስቲ ኢንትርናሽናል በማይካድራ ስለተፈጸመው ጥቃት ተመሳሳይ ሪፖርት ማውጣቱ ይታወሳል።

ክስተቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ሚሼል ባችሌት በማይካድራ ከተማ ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል የሚለው ሪፖርት እንዲጣራ መጠየቃቸው የተዘገበ ሲሆን በተጨማሪም "ግድያዎቹ መረጋገጥ ከቻሉ እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል" በማለት ድርጅቱ ማስጠንቀቁ ይታወሳል።

በጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊትና የትግራይ ክልል ኃይሎች ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገቡ ከሳምንት በኋላ በምዕራብ ትግራይ የተካሄደውን ግጭት ተከትሎ ነበር በማይካድራ ከተማ ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የሚያመልክቱ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ፎቶግራፎች መታየት የጀመሩት።

አምነስቲ ኢንትርናሽናልም የእነዚህን ምስሎች እውነተኝነት በማረጋገጥና የዓይን እማኞችን በማነጋገር በከተማዋ ውስጥ ማንነትን መሰረት ያደረገ አሰቃቂ ጥቃት መፈጸሙን ከሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ ማሳወቁ ይታወሳል።