ትግራይ፡ ኢሰመኮ ወደ ማይካድራ የምርመራ ቡድን መላኩን አስታወቀ

ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች
የምስሉ መግለጫ, ጥቃቱ ተፈጸመ የተባለበት ማይካድራ ከሁመራ ከተማ በቅርብ እርቀት ላይ ትገኛለች

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በማይካድራ የተፈጸመውን ሰብአዊ ቀውስ በአፋጣኝ ለማጣራት የምርመራ ቡድን ወደ ቦታው ማሰማራቱን ገለፀ።

ኮሚሽኑ ባወጠው በትናንትናው ዕለት በትግራይ ክልል እተካሄደ ስላለው ጦርነት እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫው እንዳለው በግጭቱ በተሳተፉ ማንኛውም ወገኖች የተፈጸሙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶችን በመመርመር እና ማስረጃ በማሰባሰብ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ ገልጿል።

የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ትናንት ባወጣው መግለጫ ላይ የትግራይ ክልልን በተመለከተ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት የተቋቋመው የአስቸኳይ ጊዜ ግብረ ኃይል በአፋጣኝ፣ የሰብአዊ ዕርዳታ ጉዳይ ዴስክ እንዲያቋቁም እና ከሰብአዊ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ጋር ምክክር እንዲጀመርም ጥሪ አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ጥሪውን ያቀረበው በትግራይ ክልል እየተካሄደ የሚገኘው ውጊያ የሚያስከትለውን ዘርፈ ብዙ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት አደጋን በሚመለከት በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን በገለፀበት በዚሁ መግለጫው ላይ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ እና የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ካትሪን ሶርዚ (ዶ/ር) ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለምልልስ ፤ ድርጅቱ በግጭት ቀጠና የቴሌኮም አገልግሎቶች መቋረጣቸው እና መንገዶች ዝግ መሆናቸው የሰብዓዊ እርዳታ ለማደረግ በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እንደሆነበት ገልፀው ነበር።

"ቀድሞውንም ቢሆን በትግራይ ከ600ሺህ በላይ የሚሆኑ በቋሚነት የምግብ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ይገኙ ነበር" ያሉት ካትሪን (ዶ/ር)፤ በአራት የስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ከ96ሺህ በላይ ኤርትራውያን ስደተኞች መኖራቸውን ጠቀሰው የሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ለስደተኞቹ የዕርዳታ ድጋፍ የሚሰጠው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካል ያለው የመሠረታዊ ፍጆታዎች ክምችት በቅርቡ ሊሟጠጥ እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ኢሰመኮ በመግለጫው በተጨማሪም ቀይ መስቀል ማህበር ሰብአዊ አገልግሎቶችን ማከናወን እንዲችል በውጊያው ተሳታፊ የሆኑ አካላት ተፈፃሚነት ባላቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች መሰረት የቀይ መስቀል አርማ እንዲያከብሩና ተገቢውን ትብብር እንዲያደርጉ አሳስቧል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም ከሁመራ ዳንሻ ባለው መስመር ሶስት አምቡላንሶች በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቶባቸው ጉዳት እንደደረሰባቸው ለቢቢሲ መግለፁ ይታወሳል።

በተጨማሪም ኮሚሽኑ በአሁኑ ሰዓት በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍሎች መንግሥት እየወሰደ ባለው እርምጃ የታሰሩ ሰዎችን በሚመለከት ከደረሱት ጥቆማዎችና መረጃዎች በመነሳት በብሄራቸው ማንነት በመለየት ለጥርጣሬ እና መድልዎ እንዲጋለጡ የሚያደርግ "ምክንያታዊ ስጋት" መፈጠሩን መረዳቱን በመግለጽ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል።

ኢሰመኮ ከዚህ ጋር በተያያዘም በቅርቡ የጸደቀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈጻሚነቱ ወሰን በትግራይ ክልል ውስጥ መሆኑን በመጥቀስ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች የሚደረግ የሕግ ማስከበር ሂደት መደበኛውን የሕግ ማስከበር ሥነ ሥርዓት ደንቦች ተከትሎ የሚፈጸም መሆን እንዳለበት በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

በተመሳሳይ ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሂውመን ራይትስ ዋች በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥትና በጦርነቱ የንፁኀን ዜጎችን ሕይትና ንብረት መጠበቅና መከላከል እንዳለበት አሳስቧል።

ተቋሙ አክሎም የሰብዓዊ እርዳታ እና አገልግሎቶች አቅራቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች ማቋረጥ እንዲቆምና በክልሉ የስልክ ግንኙነት እንዲከፈት ጥሪ አቀርቧል።

የድርጅቱ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ላይቲታ ባደር በትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እና አገልግሎቶችን መገደብ ማለት በጦርነቱ እየተጎዳ ያለው በሚሊየን የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብን ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል ሲሉ ገልፀዋል።

አክለውም "የፌደራልና የትግራይ ክልል መንግሥታት የመኖር መብትን እንዲያከብሩና ሕዝቡን ለመደገፍና ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርጉ" አሳስበዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይም በትግራይ ክልል ማይካድራ ከተማ በርካታ ዜጎች ተገድለዋል የሚል ሪፖርት መውጣቱን ተከትሎ በትናንትናው እለት (አርብ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "ግድያዎቹ መረጋገጥ ከቻሉ እንደ ጦር ወንጀል ይቆጠራል" ሲል አሳስቧል።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በትግራይ ክልል ውስጥ ሰኞ ምሽት በርካታ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እንዳገኘም ገልጾ ነበር።

አምንስቲ እንዳለው በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በምትገኘው ማይካድራ ከተማ ውስጥ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ቁጥራቸው በመቶዎች ሊቆጠሩ የሚችሉ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ በስለት ተገድለዋል።

የሰብዓዊ መብቶች ተቆርቋሪው ድርጅት ግን በትግራይ ክልል ደቡብ ምዕራብ ዞን በምትገኘው ማይካድራ ግድያውን ማን እንደፈጸመው ለማረጋገጥ አለመቻሉን አመልክቷል።

ነገር ግን ድርጅቱ ያነጋገራቸው የአይን እማኞች ከፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ጋር የሚዋጉትን የህወሓት ታማኝ ኃይሎች ጥቃቱን እንደፈጸሙ ይከስሳሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ጭፍጨፋውን የፈፀሙት የህወሓት ታጣቂዎች ናቸው ቢሉም የትግራይ ክልል ባለስልጣናት በበኩላቸው በግድያዎቹ እጃችን የለበትም በማለት ውድቅ አድርገውታል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ውንጀላዎቹ "መሰረት" የሌላቸው ናቸው ማለታቸውንም አጃንሰ ፍራንስ ፕሬስ እርሳቸውን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በበኩላቸው የፌደራል መንግሥት የምዕራብ ትግራይን "ነፃ ካወጣ" በኋላ የህወሓት ታጣቂዎች በማይካድራ ከተማ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን "በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል" ብለዋል።

የፌደራል መንግስት በኮሮናቫይረስ ምክንያት አገራዊ ምርጫ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑን ተከትሎ ባለፈው ዓመት በትግራይ ምርጫ መካሄዱ በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያለው ውጥረት እንዲባባስ መባባስ መንስኤ ሆኗል።

የትግራይ ክልልና የፌደራል መንግሥት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ከገቡ በኋላ የተለያዩ ወገኖች ግችቱ እንዲቆና ውይይት እንዲደረግ ጥሪ እያቀረቡ ቢሆንም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግሥት በትግራይ ክልል የሚያደርገውን ወታደራዊ እርምጃ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች እስኪፈፀሙ ድረስ እንደሚቀጥል ማስታወቁ ይታወሳል።