ትግራይ፡ የፌደራል ፖሊስ በ96 ሲቪልና ወታደራዊ ግለሰቦች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ መውጣቱን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Federal Police Commision
የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተፈላጊ ናቸው ባላቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችንና አባላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በ96 ግለሰቦች ላይ ማውጣቱን አስታወቀ።
ፖሊስ መያዣ ትዕዛዙን ያወጣው ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል ያላቸውን ግለሰቦች አድኖ በመያዝ ለሕግ ለማቅረብ መሆኑን ገልጿል።
በተጨማሪም የእስር ማዘዣው የወጣባቸው ሲቪልና ወታደራዊ ግለሰቦች "ከኦነግ ሸኔ እና ከሌሎች ፀረ-ሰላም ኃይሎች ጋር በመቀናጀት አገርን የማፍረስ ተልዕኮ ያለቸውን ኃይሎች በመመልመል በትግራይ ክልል ውስጥ ስልጠናዎችን፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን" ያደረጉ ናቸው ብሏል።
እንዲሁም "በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ብሔርን ከብሔር በማጋጨት እና በሐይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር በማድረግ በርካታ ንጹሐን ዜጎች እንዲገደሉ፣ በአካልና በንብረት ላይም ከባድ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውን" የፌደራል ፖሊስ የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸውን ሰዎች ዝርዝር ይፋ ባደረገበት መግለጫው ላይ አመልክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በትናንትናው ዕለት ባካሄደው አራተኛ መደበኛ ስብሰባ የህወሓት ከፍተኛ አመራር አባላትን ጨምሮ የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ የሰላሳ ስምንት (38) ግለሰቦችን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱ ይታወቃል።
ዐቃቤ ሕግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የጠየቀባቸው ግለሰቦች በተለያዩ ወንጀሎች ስለተጠረጠሩ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ እነዚህም "ከፍ ያለ የአገር ክህደት በመፈጸም፣ በሕገ-መንግስቱና በሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ በተደረገ ወንጀልና የጦር መሳሪያ ይዞ ማመፅ" ተጠቅሷል።
በተጨማሪም "የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት በሚፈጸም ወንጀል፣ የአገር መከላከያ ኃይልን በመጉዳት እና በሽብር ወንጀል በመሳተፍ እንዲሁም ዋና የሽብር አቅራቢ በመሆን" በመጠርጠራቸው መሆኑ ለምክር ቤቱ ተገልጿል።
በፌደራል ፖሊስ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ግለሰቦች አጠቃላይ ብዛት 96 ሲሆን ከእነዚህም መካከል 64ቱ ሲቪሎች ሲሆኑ 32ቱ ደግሞ ወታደራዊ መኮንኖች ናቸው። ከመካከላቸውም ሰባት በቁጥጥር ስር የዋሉ እንዳሉበት ተገልጿል።
ፖሊስ በከባድ ወንጀል እንደሚፈልጋቸው ገልጾ የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣባቸው 64 ግለሰቦች መካከል ከፍተኛ የህወሓት ባለስልጣናት አመራሮች የሚገኙበት ሲሆን ከእነሱም መካከል የትግራይ ክልል ፕሬዘደንትና የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር)፣ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሄር፣ የቀድሞው የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የቀድሞው የገንዘብና ሚኒስትር ዲኤታ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ስማቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ኪሪያ ኢብራሂም፣ የቀድሞው የደኅንነት ኃላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ስዩም መስፍን፣ የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ አባይ ፀሐዬ የቀድሞ የብሮድካስት ባለስልጣን ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስጎዶም፣ የህወሓት መስራችና በኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የሰላምና የልማት ኢንስቲቲዩት የቀድሞ ዳይሬክተር አቶ ስብሀት ነጋ ይገኙበታል።
የፌደራል ፖሊስ የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣባቸው የሲቪል አመራሮች በተጨማሪም በተመሳሳይ ወንጀሎች ውስጥ ተሳትፈዋል ብሎ የጠረጠራቸው የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የፖሊስ አባላት ላይም የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ገልጿል።
በዚህም መሠረት ሌ/ጀኔራል ታደሰ ወረደ ተስፋዬ፣ ሜ/ጄኔራል ዮሐንስ ወ/ጊዮርጊስ ተስፋይ፣ ሜ/ጄኔራል ብርሃነ ነጋሽ በየነ፣ ብ/ጄኔራል ኃ/ሥላሴ ግርማይ ገ/ሚካኤል፣ ብ/ጄኔራል ምግበ ኃይለ ወ/አረጋይ፣ ሜ/ጄኔራል ኢብራሂም አብዱልጀሊል፣ ብ/ጄኔራል ገ/ኪዳን ገ/ማርያም፣ ሜ/ጄኔራል ገብረ ገ/አድሃና ስማቸው ተጠቅሷል።
በተጨማሪም ሜ/ጄኔራል ገ/መስቀል ገ/ዮሐንስ፣ ብ/ጄኔራል አብርሃ ተስፋይ በርሄ፣ ብ/ጄኔራል ፍስሃ በየነ፣ ሜ/ጄኔራል ህንፃ ወ/ጊዮርጊስ ዮሐንስ፣ ብ/ጄኔራል አለፎም አለሙ፣ ብ/ጄኔራል ገ/መስቀል ገ/እግዚአብሄር፣ ብ/ጄኔራል ተ/ብርሃን ወ/አረጋዊ፣ ሜ/ጄኔራል አታክልቲ በርሄ ገ/ማርያም የተባሉት ከአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ መኮንኖች ይገኙበታል።
ከእነዚህ በተጨማሪም በፌደራልና በትግራይ ፖሊስ ኮሚሽኖች ውስጥ ከኮሚሽነርነት ጀምሮ በተለያዩ የኃላፊነት ደረጃዎች ላይ ያሉ ከፍተኛ አመራሮች ላይም የእስር ማዘዣ መውጣቱን የፌደራል ፖሊስ በመግለጫው አመልክቷል።
የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸው መኮንኖች መካከል ሰባቱ ቀድም ብሎ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ትናንት ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው ከተሰማ በኋላ ቀጠሮ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሏል።
በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይን ክልል በሚያስተዳድረው ህወሓት መካከል የነበሩት አለመግባባቶች ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በክልሉ የተካሄደውን የተናጠል ምርጫ ተከትሎ እየተካረረ በመምጣት በአሁኑ ጊዜ ወደ ወታደራዊ ግጭት መሸጋግሯል።
የፌደራል መንግሥቱ ትግራይ ውስጥ ባለው ሠራዊቱ ላይ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ሕግ ማስከበር ባለው ዘመቻ በህወሓት አመራሮችና በሚመሩት ታጣቂ ኃይል ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን ገልጿል።















